Clicky

አቶ ልደቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

በ“መድሎት” ውስጥ በገለጽኩት ሃሳብ ዙሪያ፣ አሁን እሳቸው ከሞቱ በኋላስ ትክክል ነው ወይንስ አይደለም ብዬ ነገሮችን ለማየት ሞክሬያለሁ፡፡ ግምገማዬ ትክክል እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ ያኔ ያነሳሁት ጭብጥ፤ ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቆየቱ ካልቀረ አቶ መለስ በስልጣን ላይ ቢቆዩ ይሻላል ወይስ አይሻልም የሚል ነው፡፡
የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታው የተሻለ አቅጣጫ ሊይዝ የሚችልበትን መስመር ለማየት አቶ መለስ ከሌሎቹ የኢህአዴግ አመራሮች የተሻለ እድል ነበራቸው፤ ፍላጐቱም ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡

ኢህአዴግ በስልጣን ላይ መቀጠሉ እስካልቀረ ድረስ፣ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር ብዬ አምናለሁ። ያኔም ብየዋለሁ፡፡ ለምን ቢባል፤ አቶ መለስ እሳቸውን የሚተኩና ጐልተው የሚታዩ ሰዎችን ፈጥረዋል ወይ? እዚህ ላይ ድክመት ነበረባቸው ብዬ አምናለሁ። እንደማንኛውም አምባገነን መሪ፤ በራሳቸው ስር ከፍተኛ ስልጣን አሰባስበው ነበር፡፡ እሳቸው ብቻ ነበሩ የሚደመጡበት፡፡ ከመደመጥም አልፈው የሚመለኩበት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር፡፡ ያ ሁኔታ አሁን የራሱ የሆነ ጉዳት አስከትሏል ብዬ አምናለሁ፡፡

የመልካም አስተዳደር እጦትንና ሙስናን በመዋጋት ደረጃ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ገዢው ፓርቲ እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ይገልፃል፡፡ መተካካቱ ችግር አላስከተለም ማለት ነው?

እኔ ይሄን ከምንም አልቆጥረውም፡፡ አቶ መለስ በህይወት ከነበሩበት ጊዜ የተለየ ነገር የለም። እሳቸው በነበሩበት ጊዜ አቶ ታምራት በሙስና ታስረው ነበር፡፡ ተመሳሳይ ዘመቻዎችም ታይተዋል። ሙስና የሚገታው በዚህ ዓይነት ዘመቻ አይደለም፡፡ በመሠረታዊ የአስተሳሰብና የአሠራር ለውጥ እንጂ፣ በሰሞነኛ ግርግርና ዘመቻ የሚፈታ ችግር አይደለም። ግርግር በሳቸውም ጊዜ አይተናል፤ አሁንም እያየን ነው፡፡

ይልቅስ፤ አሁን የተፈጠረ አዲስ ነገር ሌላ ነው። ከአቶ መለስ ሞት በኋላ፤ የፓርቲው የስልጣን እንብርት  የት እንደሆነ በግልጽ ወጥቶ አልታየም። አልለየለትም፡፡ ህዝቡ፤ እኛ ተቃዋሚዎች፤ የኢህአዴግ አባላትም ጭምር እቅጩን የሚያውቅ የለም፡፡ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ድርጅት ስልጣንን እንደገና የማደላደልና ዘላቂ የማድረግ ሂደት (ፓወር ኮንሰልዴሽን) ውስጥ ነው የገባው፡፡ ኢህአዴግ እንደ አዲስ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ መግባቱ የዲሞክራሲ ሂደቱን በጣም ይጐዳዋል፡፡  አቶ መለስ ባይሞቱ ኖሮ፣ የሚቀጥለው ምርጫ የተሻለ ለውጥ ይታይበት ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ግን ኢህአዴግ እንደዛ አይነት ለውጥ ለማስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ በድርጅቱ ውስጥ የስልጣንና የሃይል ድልድሉ አልጠራም፡፡

አቶ መለስ በኢህአዴግ ውስጥ፣ ሃያልና ገናና የሆኑት ባለፉት አስር ዓመታት ነው፡፡ ከዛ በፊት ገናና አልነበሩም፡፡ እንደ አቶ መለስ በሁሉም የኢህአዴግ አመራርና አባላት ዘንድ ተደማጭነት ያለው ገናና ሰው እስኪፈጠር ብዙ ዓመታት ይወስዳል፡፡ እስከዚያው ኢህአዴግ ተደላድያለሁ ብሎ ስለማይተማመን የህልውና ጉዳይ የበለጠ ያሳስበዋል፡፡ ልፈረከስ እችላለሁ ብሎ ይሰጋል። ተቃዋሚዎች ቀዳዳ ተጠቅመው ያዳክሙኛል ያፈራርሱኛል ብሎ ይፈራል፡፡ ስጋቱና ፍርሃቱም፣ የበለጠ በሩን እንዲያጠብና እንዲዘጋ ይገፋፋዋል፡፡

ይህንን ነው እያየሁ ያለሁት፡፡ ከዛ አንፃር ነው፤ አቶ መለስ ቢኖሩ ይሻል ነበር የምለው፡፡ በመሪነት ሚናቸው አምባገነን ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን አቶ መለስ ዞሮ ዞሮ ያን ያህል ዓመት ገዝተውናል። የኋላ ኋላ ለታሪካቸውም ሲሉ፣ የመንግስት መሪ በመሆን ከተማሯቸው የተለያዩ ጉዳዮች በመነሳት፣ ከሌሎች የኢህአዴግ አመራሮች በተሻለ መልኩ፣ በጐ ለውጥ የማምጣት እድል ነበራቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እነዚያን እድሎች የመጠቀም አንዳንድ ምልክቶችም እያየን ነበር፡፡ በ97 ምርጫ፤ በሩን ሰፋ የማድረግ ሁኔታ ያየነውም  ከዛ ጋር የተያያዘ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ኢህአዴግ እንደ ድርጅት አምባገነን ነው፤ አቶ መለስም አምባገነን መሪ ነበሩ፤  ግን ከኢህአዴግ አመራር አባላት ውስጥ ማወዳደር ካስፈለገ፣ አቶ መለስ የተሻሉ ዲሞክራት ናቸው ብዬ አምናለሁ፡፡ እሳቸው ከስልጣን ከመውረዳቸው በፊት ለተወሰኑ አመታት በስልጣን ቢቆዩ ለአገሪቱ በዲሞክራሲ ሂደቱ የተሻለ ነገር ሊያመጡ ይችላሉ የሚል ግምት ነበረኝ፡፡ አሁን እሳቸው በህይወት የሉም፡፡ ኢህአዴግ በህልውና ስጋት ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ገብቷል፡፡ በቀጣዩ አመት ምርጫ የተሻለ ነገር ይዞ ሊመጣ ይችላል የሚል ተስፋ እንዳይኖረኝ ያደረገኝ ይኼ ነው፡፡

ከኢትዮጵያ ዋና ዋና ፈተናዎችና ትልልቅ ስጋቶች ሶስቱን ይጥቀሱ ቢባሉ የትኞቹን ያስቀድማሉ?

አንደኛው ፈተና፣ የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር ነው፡፡ ዲሞክራሲ ታፍኖ በቀጠለ ቁጥር፣ አገሪቱ አደጋ ማስተናገዷ የማይቀር ነው፡፡ ዲሞክራሲን እስከወዲያኛው አፍኖ መኖር አይቻልም፡፡ የዲሞክራሲ ጥያቄዎች እንዳልተመለሱና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ እንዳልተከበሩ ህብረተሰቡ እሮሮ እያቀረበ ነው፡፡ ይሄ በግልጽ እየታየ ነው፡፡ ሁልጊዜ የህዝብን ጥያቄ ወይም የተቃዋሚን እንቅስቃሴ በሃይል እያፈኑ መኖር አይቻልም፡፡ እመቃውና አፈናው ያለ ምንም መሻሻል ከቀጠለ፣ ኢትዮጵያን ወደ መጥፎ አደጋ ሊያስገባት ይችላል፡፡ አንዱ ስጋቴ ይህ ነው፡፡

ሁለተኛው ከሙስና ጋር የተያያዘው ስጋት ነው፡፡ በስርዓቱ ውስጥ እጅና ጓንት ሆኖ አላግባብ የሚጠቀምና የኢኮኖሚ የበላይነትን የሚቆናጠጥ ማህበረሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡ ብዙ ጦም አዳሪ ባለበት አገር፤ አንዳንድ ሰዎች ከመንግስት ጋር ባላቸው ግንኙነት፣ የአውሮፓና የአሜሪካ ዓይነት ኑሮ ሲፈጥሩ ህብረተሰቡ እየታዘበ ነው፡፡ ይሄ የፖለቲካውን ብሶት የበለጠ ተቀጣጣይ ያደርገዋል፡፡ በተለይ  እንደ ኢትዮጵያ ብዙ ብሔረሰብ ባለባትና የፖለቲካ ቅራኔ በከረረባት አገር፣ እጅግ አስጊ ነው፡፡ መፍትሔ ካልተበጀለት በቀር፣ ለአገሪቱ ትልቅ አደጋ እንደሆነ አምናለሁ፡፡

ሶስተኛው ስጋት፣ ኢኮኖሚያችን ውስጥ ያለው ችግር ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ፣ የድህነት ጥያቄ ብቻ አይደለም፡፡ የሰላም ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ጥያቄ የዲሞክራሲ ጥያቄ ነው፡፡ የኢኮኖሚ እድገት የህልውና ጥያቄ ነው፡፡ ይህች አገር ከሞላ ጐደል  የእርሻ አገር ናት፡፡ ከተማ ከገባን ደግሞ የሱቅና የቢሮ አገር ናት፡፡ የማምረቻ ኢንዱስትሪዎች አገር አይደለችም፤ መሆንም አልቻለችም፡፡ መዋቅራዊ ሽግግር ካልመጣ በቀር፤ የእስካሁን አመጣጧ ከፍተኛ አደጋ ላይ ያደርሳታል፡፡ ለምን ቢባል፤ በመዋቅራዊ ሽግግር ኢንዱስትሪ ካልተስፋፋ፣ ድህነት እጅግ ይባባሳል፣ የሰው ኑሮ ይበልጥኑ ይናጋል፡፡ ያለጥርጥርም፤ የፖለቲካ አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡
የዲሞክራሲ ሂደት አለመኖር፣ ከሙስና ጋር የተያያዘ የሃብት ሽሚያ አበጋዞች መፈጠር እና ከእርሻ በላይ የሚሄድ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር አለመኖር ናቸው ሶስቱ ትልልቅ የአገሪቱ ፈተናዎች። አስቸኳይ እርምጃ ካልተወሰደ የዚህች አገር ሁኔታ አስቸጋሪ ነው፡፡

አካባቢያዊ ጉዳዮችን ላንሳ፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት በአረብ አገራት የተፈጠረውን እንቅስቃሴ እንዴት ያዩታል? የግብፅና የሶርያ ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ ማምራት እንዴት ይመለከቱታል?

Pages: 1 2 3