Clicky

አቶ ልደቱ ከአዲስ አድማስ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

አሁን የጠቀስኳቸው ሶስቱ የአገራችን ችግሮች ካልተፈቱ፤ ኢትዮጵያም እንደዛ አይነት ቀውስ የምታስተናገድበት አደጋ ይኖራል፡፡ በግብጽ፣ በሶሪያ፣ በሊቢያ ያየነው አይነት ቀውስ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢፈጠር፤ ውጤቱ ከእነሱም የከፋ አውዳሚ ሊሆን ይችላል፡፡ በአገራችን ውስጥ የሚታዩ ችግሮች፣ ብዙ አቀጣጣይ ነገሮችን ያቀፉ ናቸው፡፡ ስሜታዊ ሃይሎች በቀላሉ የሚያግለበልቧቸው የብሔረሰብ ጉዳዮች፣ እንዲሁም ፅንፍ ድረስ የተወጠሩ ጭፍን የፖለቲካ አስተሳሰቦች በበረከቱባት አገር ውስጥ ቀውስ ተጨምሮበት ምን ያህል ውድመት እንደሚፈጠር ለማሰብ ይከብዳል፡፡

ግብፅ ውስጥ፣ ጐዳና የወጣው ጦር ሰራዊትና ጐዳና የመጣው ወጣት፣ በሰላምታ ሲጨባበጥ አይተናል፡፡ ቀውሱን ሙሉ ለሙሉ ለማስወገድ ባይችልም፤ ያረግበዋል፡፡ በኛ አገር ግን እንደዚያ አይነት ማርገቢያ ነገር የሚፈጠር አይመስለኝም፡፡ ቀውሱ ውስጥ ከገባን ማብቂያና መመለሻ የምናገኝ አይመስለኝም፡፡ መፍራትና መጠንቀቅ ያለብን፣ ይህቺ አገር ወደዛ ዓይነት ቀውስ እንዳትገባ ነው። አንዳንድ ሰዎች እንደዛ ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሚናፍቁ አውቃለሁ፡፡ ግን ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው፡፡ ለማንኛችንም አይጠቅምም፡፡

አገራችንን እንወዳታለን ካልን፤ አገራችን ችግሯ ተፈቶ ወደተሻለ ውጤት እንድትሄድ ከፈለግን፤ የዚያ ዓይነት ቀውስና አብዮት እዚህ አገር ላይ መከሰት የለበትም፡፡ ስላልፈለግን አይመጣም ማለት አይደለም፡፡ ቀውስ እንዳይከሰት መመኘት ብቻውን በቂ አይደለም፡፡ የአገራችንን ዋና ዋና ችግሮች ለመፍታት መጣደፍ አለብን፡፡ የዲሞክራሲ ሂደትን ማነቃቃት፤ በሙስና የሃብት ቅርምት መኳንንትን መግታት፣ መዋቅራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ማፋጠን ያስፈልጋል፡፡
በሌላ በኩል፤ ከዓባይ ጋር በተያያዘ፤ ከሱዳንና ግብጽ ጋር ያለው የፖለቲካ ግንኙነት ለአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ፖለቲካና ሠላም ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ከቅርብ ጊዜ አንፃር ካየነው፤ ኢትዮጵያ የምትሠራው ግድብ፣ ሱዳንንና ግብጽን ይጠቅማቸዋል እንጂ አይጐዳቸውም፡፡ በዚህ ረገድ፣ መንግስት የሚያራምደው አቋም እውነት ነው ብዬ እቀበላለሁ፡፡ ግድቡ እንደማይጐዳቸው እነሱም አያጡትም፡፡ ግብፅ እና ሱዳን ከኢትዮጵያ በሚሄድ የአፈር ደለል ግድቦቻቸው እየሞላ በጣም እየተቸገሩ ነው፡፡ ይሄ ችግር ይቃለልላቸዋል – ኢትዮጵያ በምትሰራው ግድብ፡፡ በክረምት ወራት በጐርፍ ይጐዳሉ፤ በበጋ ወራት ደግሞ የውሃ እጥረት ይገጥማቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ የምትሰራው ግድብ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማመንጨት እንጂ ለመስኖ አይደለም፡፡ ውሃው የኤሌክትሪክ ተርባይኖችን እያሽከረከረ ወደ ሱዳንና ግብጽ አመቱን ሙሉ ሳያቋርጥ ይሄዳል፡፡ ከክረምቱ ጐርፍና ከበጋው የውሃ እጥረት እፎይ ይላሉ፡፡

ውሃው በትነት እንዳይባክን በማድረግም የኢትዮጵያ ግድብ ትልቅ ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ በዚያ ላይ ሱዳንና ግብጽ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ ሃይል ችግር አለባቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚመነጨው የኤሌክትሪክ ሃይል የመጠቀም እድል ይኖራቸዋል። በአጭሩ ከኢትዮጵያ ግድብ ከፍተኛ ጥቅም እንደሚያገኙ አይጠፋቸውም፡፡ ስለዚህ ግድቡ ኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን እነሱንም ይጠቅማል በሚለው አቋም የዲፕሎማሲ ጥረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡

ነገር ግን ስጋታቸውንም በጥልቀት ማጤን ይገባል፡፡ የእነሱ ዋነኛ ስጋት፤ ኢትዮጵያ ወደፊት በኢኮኖሚ ካደገችና እንዲህ  ትልቅ ፕሮጀክቶችን መስራት ከጀመረች ወዴት ያደርሰናል የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በኢንዱስትሪ ካደገች፣ ሌሎችንም ወንዞች የመገደብና ውሃውን የመጠቀም አቅሟ ከጨመረ ምን ይፈጠራል የሚል ነው ስጋታቸው፡፡
ስለዚህ በአንድ በኩል በውሃው የመጠቀም መብታችንን እንዲቀበሉ የምንፈልገውን ያህል የእነሱንም መብት እንደምንቀበልና ጉዳት የማድረስ ሃሳብ ፈጽሞ እንደማይኖረን በቅንነት ለማስረዳት መጣር አለብን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ፤ መጠርጠርና መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ እንዳናድግ አንዳንድ የተንኮል ስራዎችን አይሰሩም ብሎ መሞኘት አይቻልም፡፡ ተንኮል  ሊሠሩ እንደሚችሉ በታሪክ እናውቃለን፡፡

ዲፕሎማሲያችንን ጤናማ ማድረግ ያስፈልጋል። የነሱንም በቅንነት ለማስተናገድ መሞከር ይገባል። ነገር ግን የዲፕሎማሲ ግንኙነት፣ ላይ ላዩ እንደሚታየው ሙሉ በሙሉ ጤናማ ነው ማለት አይደለም፡፡ ይህቺ አገር እንዳታድግ፤ ዘላቂ ሠላም አንዳይኖራት ግብጽ ብዙ ነገር ስትሰራ ኑራለች፡፡ አሁን ከግብጽ በኩል ከዚህ የተሻለ አስተሳሰብ አለ ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህ ነገሮችን በጥርጣሬ ማየት አስፈላጊ ነው፡፡ ግን ደግሞ ሁልጊዜ ነገሮችን በጥርጣሬ እያየን ግንኙነቱን ይበልጥ እንዲሻክር እድል መፍጠር የለብንም፡፡ በእኛ በኩል በጐ አመለካከት መያዝና ለእኛ ብቻ ሳይሆን ለእነሱም መብት እውቅና መስጠት ያስፈልጋል፡፡ በአጠቃላይ፣ የዲፕሎማሲውን ሚዛን ጠብቆ መጫወት ያስፈልጋል፡፡

የአባይ ውሃን መጠቀምና ግድብ መገንባቱን በተመለከተ ደስተኛ ነኝ፤ እደግፋለሁ፡፡ ግን ግድቡ የኢህአዴግ ፕሮጀክት ወይም የአቶ መለስ ራዕይ ብቻ አይደለም፤ የሚሊዮኖች ራዕይ ነው። እንደ አንድ ዜጋ የሳቸውም ራዕይ ነው፡፡ ግን የትውልዶችም ራዕይ ነው፡፡ የእኔም እና የአንቺም ራዕይ ነው፤ የአባቶቻችንና የእናቶቻችን ራዕይ ነው፡፡ ይሄን የትውልዶች ራዕይ ከአንዱ ፓርቲ ወይም ከሌላኛው ድርጅት ጋር ሳናገናኝ ሁላችንም መደገፍ መቻል አለብን፡፡

በእኔ እና በእርስዎ ትውልድ ምን ዓይነት ኢትዮጵያን አያለሁ ብለው ይገምታሉ?

የእኔ እና የአንቺ ትውልድ መሃል ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ወይ ከቀድሞዎቹ አልሆንም፡፡ ወይ ከመጪዎቹ አልሆንም፡፡ አስቸጋሪ ነው፡፡ ባለፉት ትውልዶች ዙሪያ የነበረ ድክመት በተወሰነ ደረጃ ተጋብቶብናል፡፡ ነገር ግን ከእነሱ የተሻለ በጐ ነገር አለን ብዬ አምናለሁ፡፡ መሃል ላይ ነን፤  ነገር ግን ለመጪው ጥሩ ዘመን የሚመጥን ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ለዚች አገር የበለጠ በጐ ነገር የምጠብቀው፤ ከእኔ እና ከአንቺ ትውልድ ሳይሆን፤ ከእኛ በታች ካለው ትውልድ ነው፡፡ በዩኒቨርስቲ፣ በኮሌጅ፣ በሃይስኩል ደረጃ ያለው ትውልድ ነው፤ የዚህችን አገር እጣ ፈንታ በዘላቂነት የሚለውጠው፡፡

ቀደም ሲል በፊውዳል ስርዓት፣ ከዚያ ቀጥሎም የግራ ፖለቲካውና የደርግ አገዛዝ የተፈራረቀባቸው ትውልዶችን አይተናል፡፡ ለዘመናት የዘለቀው ነባር ባህልና አስተሳሰብ ሁሉ የራሱ ችግር አለበት፡፡ ውጥንቅጥ  ውስጥ እንድንገባ ያደረጉንም እነዚህ ነገሮች ናቸው፡፡ በተለይ የግራ ፖለቲካ (ማርክሲዝም ሌኒኒዝም) ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋቱና በደርግ አማካኝነት ለአስራ ሰባት ዓመት መንሰራፋቱ ብዙ የትውልድ አባላትን በክሏል፡፡ ከዚያ በሽታ ዛሬም አልተላቀቀንም፡፡ ከመቻቻልና ከመደማመጥ የተራራቅነው ያለምክንያት አይደለም፡፡ የተበላሸ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ስለኖርን ነው፡፡ ያ በሽታ በተወሰነ ደረጃ በእኔ እና በአንቺ ትውልድም ይታያል – ከቀድሞው ትውልድ ብንሻልም፡፡ ከኛ በታች ያለው  ትውልድ ግን ከበሽታ ነፃ የመሆን ዕድል አለው፡፡ ከመተላለቅና ከመጠላለፍ ይልቅ ነገሮችን በቀጥታ ለማየት የተዘጋጀ፣ ከቂም በቀል የፀዳ፤ ኮተት ያልተጫነበት ትውልድ እየመጣ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡  የእኛ ትውልድ ከቀድሞው ትውልድ የተጋባብን የበሽታ ቅሪት ወደ አዲሱ ትውልድ እንዳይሻገር በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦ ይኖረናል ብዬ አስባለሁ፡፡ የኛ ትውልድ ሚና ይሄ ይመስለኛል፡፡ በውርስ የመጡ በጐ ያልሆኑ ነገሮች ይሄኛው ትውልድ ላይ መቆም አለባቸው፡፡ በጐ ያልሆኑት ነገሮች ስህተት መሆናቸውን በጉልህ አውጥተን በማስተማርና ጥሩ ጥሩ ነገሮችን በማውረስ አቅጣጫውን ማሳየት ይጠበቅብናል ብዬ አስባለሁ፡፡

የጠ/ሚ አቶ ሃይለማርያምና የአዲሱ አስተዳደር አዝማሚያና ብቃት ላይ ምን ይላሉ?

አዲሱን ጠ/ሚኒስትር በግል አውቃቸዋለሁ። ፓርላማ በነበርኩበት ጊዜ እሳቸውን የማግኘትና የማናገር ብዙ እድሎች ነበሩን፡፡ በጣም በጐና ቅን ሰው እንደሆኑ በእርግጠኝነት አውቃለሁ፡፡ ቅንነት ብቻውን በቂ አይደለም ግን በጐ ሰው መሆናቸው፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃላፊነታቸው ላይ የሚኖረው ቦታና አገራዊ ፋይዳውን ስናይ የራሴ ጥርጣሬ አለኝ፡፡ ኢህአዴግ ስልጣኑን የማደላደል ጣጣ ውስጥ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አቶ ሃይለማርያም የተሻለ ነገር ለማምጣት ምን ያህል እድል አላቸው የሚለው ነገር ግልጽ አይደለም፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ፣ ለውጥ ለማምጣት ምን ያህል ፍላጐት አላቸው? ፍላጐትስ ካላቸው ምን ያህል አቅም አላቸው? አንድ መሪ በአንድ ድርጅት ወይም መዋቅር ውስጥ በአንድ ጊዜ ተደማጭነት የማግኘት እድል የለውም፡፡ ጊዜና ሂደት ይጠይቃል። አቶ ኃይለማርያም ያንን ጊዜና ሂደት ቢያገኙ፤ የለውጥ ሃዋርያ ሆነው የተሻለ ነገር ይፈጥራሉ ወይ የሚለው ወደፊት የሚታይ ነው፡፡ እድሉን ሳያገኙ ስልጣናቸውን ሊለቁ ይችላሉ ወይም እድሉን አግኝተው የተሻለ ሁኔታ ሊፈጥሩ ይችሉ ይሆናል። ወይም እድሉን ላይጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ለጊዜው በርግጠኝነት መናገር የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ጊዜ መጠበቅና ማየት ይሻላል፡፡

Pages: 1 2 3