Clicky

ሪፖርተር አውጥቶት የነበረው ዜና የተዛባ በመሆኑ ተስተካክሎ እንዲዘገብ ኢዴፓ ጠየቀ

በህዳር 18/2009 በወጣው የሪፖርተር እትም ኢዴፓ አውጥቶት የነበረው መግለጫ በተዛባ መልኩ በመቅረቡ፤ ተዛብቶ የወጣው ዜና በአስቸኳይ ተስተካክሎ እንዲወጣ ኢዴፓ በደብዳቤ ጠይቋል።
የደብዳቤው ይዘት ከታች እንደሚታየው ነው።

 

 

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክ ጉባኤ ተሳትፈው ተመለሱ

Photo ALN

Photo ALN

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በሞሮኮ በተካሔደው የ11ኛው የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው ተመለሱ፡፡ ከህዳር 18 – 202007 .. በተካሄደው ጉባኤ ከ90 የሚበልጡ ተሳታፊዎች በጉባኤው ተስተናግደዋል፡፡

በጠቅላላው ጉባዔው የቀጣዩን 2 አመታት ስራ አስፈጻሚ የተመረጡ ሲሆን ኦሊቨር ካሚታቱ በድጋሚ ለሁለት አመታት የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክን እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡ በኔትወርኩ ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሴት ስራ አስፈጻሚ መካተቱ ይህንን ጉባኤ ታሪካዊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም ከ44 በላይ ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ መሳተፋቸው ጉባኤውን ታሪካዊ ከሚያደርጉት ክስተቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ተሳታፊ ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ ሲገኙ ይህ የመጀመርያው ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኔትወርኩ ለመጀመርያ ጊዜ በሊበራል ዲሞክራሲ እይታ የተቃኘ የአፍሪካ ሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የራሱን ሰነድ ያረቀቀ ሲሆን፤ ሰነዱም በዋናነት የሴት ልጅ ግርዛት፤ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና የፖለቲካ ነጻነት ላይ በትኩረት ይተነትናል፡፡

/ር ጫኔ ከበደ በዚህ ስብሰባ ላይ ኢዴፓን ወክለው የኢዴፓን ሀሳብ እና አመለካከት ለጉባኤው ተሳታፊዎች በማካፈል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ኢዴፓ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ እንደማይቆርጥ አስታወቀ

ኢዴፓ ለግንቦት አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ካለፈው አመት ጀምሮ ቢሆንም ነገር ግን የዝግጅቱ ዋናው አካል የሆነው በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሊያካሂዳቸው ያሰባቸው ህዝባዊ  ስብሰባዎች በተለያዩ የመንግስት ቢሮክራሲ ችግሮች ምክንያት እንደተሰናከሉበት ይታወቃል፡፡ የባለፈው ወር የባህር ዳር ስብሰባ እና የባለፈው አመት የሐምሌ ወር የአዲስ አበባው ህዝባዊ ስብሰባዎች ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ መምጣታቸው የሰላማዊ ትግሉን በእጅጉ የሚያዳክሙ እርምጃዎች ቢሆኑም ኢዴፓ አሁንም ከሰላማዊ ትግል መርሁን እንደማይለቅ እና የአገሪቷ ብቸኛ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን እንደሚያምን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ባልከው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ፓርቲው ባለፈው ወር ጥቅምት 22 ቀን በባህርዳር የተሰናከለበትን ስብሰባ በድጋሚ ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በከተማው በሚገኘው ሙሉአለም አዳራሽ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

በመቀጠልም እሁድ ታህሳስ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የመቀሌውን ስብሰባ እንደሚያደርግ ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከሚነሱ ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል በግንቦት ወር የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት ላይ ሰለሚኖረው ፋይዳ ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ እየተባባሰ የመጣው የአገራችን የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መዳከም፤ እንዲሁም እያደገ በሚገኘው የአገራችን ኢኮኖሚ ዙርያ የሚታዩት ከኑሮ ውድነት፣ ከሙስና፣ ከመዋቅራዊ ሽግግርና ከነፃ የገበያ ኢኮኖሚ መዳከም ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ ኢዴፓ በመቀጠልም ህዝባዊ ስብሰባዎቹ በሌሎች ከተሞችም እንደሚካሄዱ አስታወቋል፡፡

ፓርቲው እንደቀደሙት ህዝባዊ ስብሳባዎች አሁንም እነዚህ ስብሰባዎች እንደማይሰናከሉበት ምን ዋስትና አለው? ብለን የጠየቅናቸው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊው አቶ ኤርሚያስ ባልከው በእነዚህ ስብሰባዎች ፓርቲው ለከተሞቹ ማዘጋጃ ቤቶች እውቅና ደብዳቤ በማስገባት ብቻ ሳይወሰን ገፍቶ በመሄድ የእውቅና ደብዳቤ ከጽህፈት ቤቶች ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ደብዳቤዎች መያዝ ብቻ ስብሰባው እንደማይስተጓጎል ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ገልጸው ማናቸውም አስቸጋሪ መሰናክሎች ቢኖሩም ኢዴፓ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ እንደማይቆርጥ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ኢዴፓ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለስብሰባዎቹ መሳካት የበለጠ እንደሚጥር ገልጸው የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝቡም ከኢዴፓ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ

Ethiopian Democratic Party and Ethiopian Electionኢዴፓ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን 20 የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት አካሂዷል፡፡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ በዚህ መደበኛ ስብሰባው ላይ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሣለፍና ለስራ አስፈጻሚው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ለሙሉ ቀን የተካሄደውም ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንም በተጨማሪ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሄራዊ ም/ቤቱ ከስራ አስፈጻሚው በቀረቡ አጀንዳዎች ጥልቅ ውይይት አካሂዷል፡፡ ም/ቤቱ ለመወያያ የቀረቡለትን አጀንዳዎች ማለትም የስራ አስፈጻሚ የ4 ወር የስራ ሪፖርትና  የ2007 ዓ.ም ምርጫን አስመልክቶ ፓርቲው ሊከተለው የሚገባውን ተሳትፎ በተመለከተ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አመላክቷል፡፡

ም/ቤቱ የስራ አስፈፃሚውን ሪፖርት በመገምገም ጥንካሬና ድክመቱ ላይ አስተያየት ሰጥቶ እንዲብራሩ የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎችም አቅርቦ ከፕሬዘዳንቱ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪ የስራ አስፈጻሚ አባላትም በየዘርፉ ያከናወኑትን ተግባራት ለም/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ም/ቤቱ ሪፖርቱን በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ማፅደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመጨረሻም የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫን በተመለከተ በተደረገው ውይይት ም/ቤቱ በተቃዋሚ ፓርቲ፣ በገዢው ፓርቲ እና በህዝቡ ዘንድ ያለውን ዝግጁነትና በምርጫው ዙሪያ ስለሚኖራቸው ሚና ሀገር አቀፍ ውይይት ቢደረግ የተሻለ ነው በሚል ስራ አስፈፃሚው ይሄንን ሁሉን አሳታፊ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ፣ ኃላፊነት ወስዶ እንዲንቀሳቀስና በምርጫው ዙሪያ መነቃቃት የሚፈጠርበትን ሁኔታ እንዲያመቻች አቅጣጫ አስቀምጧል ሲሉ  ስለ ስብሰባው ያነጋገርናቸው አቶ አዳነ ታደሠ የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ መልዕክት

ሰሞኑን  በአዲስ አበባ   መስተዋል የጀመረው የፍጆታ ሸቀጦች  የዋጋ ንረት በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች  የሚገኘውን  ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል አስደንግጧል፡፡  በመላው አገሪቱ ላለፋት 15 ወራት ተስተውሎ የነበረው የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት በዚሁ  ይቀጥላል የሚለው እምነትም በህብረተሰቡ ዘንድ እጅጉን እየሳሳ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ለታየው የዋጋ ንረት ዋነኛው መንስኤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የዋጋ ግምት (inflation expectation) ሲሆን ለዚህ የዋጋ ግሽበት ጥርጣሬ መንስኤ ደግሞ በቅርቡ የተገለፀው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እና የ2007 ዓ.ም የባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ  በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ኢዴፓ ይህ የደሞዝ ጭማሪ የዋጋ ግሽበቱን ከማናር ባለፈ ለደሞዝተኛው እና ለጡረተኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘላቂ እና የተጨበጠ ጥቅም አያመጣም ብሎ ያምናል፡፡ መንግስት ከደሞዝ ጭማሪው በፊት ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚገኘው ስር የሰደደ ብልሹ አሰራር፣ የምንቸገረኝነት ስሜት እንዲሁም  በየመስሪያ ቤቱ የሚታየው የመንግስት እና የፓርቲ ስራ መደበላለቅ ችግሮቹ በቅድሚያ መቀረፍ አለባቸው ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመጡበት በአሁኑ ወቅት እንዲሁም የሲቪል ሰራተኛው አገልግሎት አሰጣጥና ምርታማነት ባልተሻሻለበት ሁኔታ የመንግስት ሰራተኛ የደሞዝ ስኬል መጨመሩ የዋጋ ግምቱን (inflation expectation) እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ  ያሳድራል፡፡

ኢዴፓ ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል ማገዝ የሚቻለው የደሞዝ ወለሉን (minimum wage) በማሻሻል እንዲሁም በጊዜያዊነት የስቪል ሰራተኛው ከገንዘብ ጋር ያልተገናኙ ጥቅሞችን (non-monetary incentives) በመጠቀም ሲቪል ሰራተኛውን ከኑሮ ውድነት ችግር በማውጣት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሌላው የዋጋ ግምትን (Inflation Expectation) ጥርጣሬ የሚፈጥሩ የ2007 ዓ.ም ባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ ነው፡፡ መንግስት ይህንን ጉድለት የሚሞላው በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አና በአገር ውስጥ ብድር መሆኑ ለግሽበቱ ከፍተኛ ጥርጣሬን እያሳደረ ይገኛል፡፡ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አላማ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል ሳይሆን የመንግስትን ባጀት ጉድለት መሙያ ሆኖ ማገልገሉ የማእከላዊ ባንኩን ነፃነትና ገለልተኝነት በጥያቄ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ ለዋጋ ግምት መናር የራሱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሂደት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነፃ እና ገለልተኛ ያልሆነው ብሄራዊ ባንክ ባለበት ሁኔታ መንግስት በፈለገና በፈቀደ ጊዜ  ከባንኩ መበደር መቻሉ ለዋጋ ግሽበቱ ቀጥተኛ አስተዋፆ ያደርጋል! በመሆኑም ኢዴፓ እንዲህ አይነቱን የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር የሚቻለው ባጀቱን ለተገቢው  አላማ እንደሚውል በማረጋገጥ እናም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡትን የመንግስት ብክነቶችን በማስወገድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ አንዲሁም መንግስት  ብሄራዊ ባንክን ነፃነት እና ገለልተኝነት የሚያጠናክር እርምጃዎችን በመውሰድ ባንኩ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በመጨመር ነው ብሎ ያምናል፡፡

በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩትን የኢዴፓ አመራርና አባላት በሚመለከት

ሐምሌ 10 ቀን 2006 ዓ.ም በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የኢዴፓ አመራርና አባላት ትናንት ወደ ማምሻው ላይ በነጻ ተለቀዋል፡፡ በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩበት ምክንያት ፖሊስ ሲያስረዳ ‹‹ ፍቃድ ሳይኖራቸው ግለሰቦች በቅስቀሳ ስራ ላይ በመሠማራታቸው እንደሆነ ሳጅን አንተነህ ገልጸዋል፡፡ ግለሰቦቹ የያዙት ፍቃድ የአዳራሽ ስብሰባ ፍቃድ እንደሆነና የቅስቀሳ ፍቃድ  እንደሌላቸው ፖሊስ አክሎ ገልጿል፡፡

ይህ በመሆኑም የመኪናው ባለቤት በህገወጥነት ተፈርጆ የገንዘብ ቅጣት የተጣለበት ሲሆን ኢዴፓም ‹‹ ከዚህ ጀምሮ ምንም አይነት ቅስቀሳ ማካሄድ አይችልም›› ሲል ፖሊስ አዟል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፓርቲው ሃላፊዎች ወደ አዲስ አበባ መስተዳድር ህዝባዊ ስብሰባና ሰላማዊ ሰልፍ ማሳወቂያ ቢሮ ሔደው የቅስቀሣ ፈቃድ ጠይቀው ‹‹የቅስቀሳ ፍቃድ የሚባል ነገር የሌለና ሌላ ይህንን አይነት የቅስቀሣ ፈቃድ የሚሰጥ የመስተዳድሩ አካል እንደሌለ የክፍሉ ኃላፊ አቶ ማርቆስ ብዙነህ ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነቱን ፍቃድ ሰጥተው እንደማያውቁም ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው የአቶ ማርቆስን መልስ አጠናክረው ከዚህ ቀደም ኢዴፓ የህዝባዊ ስብሰባ ቅስቀሳ ሲያካሒድ እንዲህ አይነቱ ፍቃድ ወስደውም ሆነ  ተጠይቀው እንደማያውቁ ተናግረዋል፡፡ አቶ ኤርሚያስ አክለውም የህዝባዊ ስብሰባና  ቅስቀሳ ማሳወቂያ ዝርዝር ሒደቶች ውስጥ ለቅስቀሳ የሚሆን የተለየ ፍቃድ እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ በከተማ መስተዳደሩ የከንቲባው ጽ/ቤት የተሰጠው ፍቃድ ላይም ግልባጭ ለብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት፣ ለፌደራል ፖሊስ ኮሚሽንና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተላከ ሲሆን ፖሊስ ይህንን እያወቀ እንዲህ አይነቱን እስር መፈጸሙ ግራ እንዳጋባቸው ገልጸዋል፡፡   በተጨማሪም አቶ ኤርሚያስ ኢዴፓ ለህዝባዊ ስብሰባው አንድ ቀን እንደቀረው ገልጸው የቅስቀሣው ስራ እንዲቆም ፖሊስ ያዘዘበት ምክንያት አሣማኝ እንዳልሆነና እና ምንም የህግ መሠረት የሌለው እንዲሁም ፀረ- ዴሞክራሲያዊ አካሔድ በመሆኑ ኢዴፓ የቅስቀሣውን ስራ ዛሬም የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አሁን ከጥቂት ሰዓታት በፊት በደረሰን ዜና መሠረት በትናንትናው እለት በቁጥጥር ስር ውለው የነበሩት የፓርቲው ቀስቃሽ አባላት በሙሉ ዛሬም በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል፡፡ በተጨማሪም የፓርቲው የህዝብ ግንኑነት ሃላፊ  አቶ ወንደሰን ተሾመ፣ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው፣ የጥናትና ምርምር ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ እና የፓርቲው የአዲስ አበባ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዴንጎ ደሜ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ ይህ ዜና እንደደረሰን የፓርቲውን ፕሬዘዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደን በጉዳዩ ላይ አነጋግረናቸው በዚህ አይነት ሁኔታ ህዝባዊ ስብሰባውን ማካሄድ አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ለብሄራዊ የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አስቸኳይ ደብዳቤ ጽፈው ግልባጭ ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደላኩ ገልጸዋል፡፡ መንግስት አስቸኳይ መፍትሄ ካልተሰጣቸው ህዝባዊ ስብሰባውን ለመሰረዝ ፓርቲው እንደሚገደድም ገልጸዋል፡፡

የኢዴፓ ህዝባዊ ስብሰባ ቀስቃሽ አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ

ኢዴፓ ሐምሌ 12 ለሚያካሂደው ህዝባዊ ስብሰባ በቅስቀሳ ላይ የነበሩ የፓርቲው አባላትን ፖሊስ በዛሬው እለት በቁጥጥር ስር አውሏል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ከዋሉት የፓርቲው አባላት መካከል የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ አዳነ ታደሰን ጨምሮ የፓርቲው የአዲስ አበባ ኮሚቴ አባላት መንገሻ ወ/ገብርኤል፤ ወ/ሪት አለም ዘውዱ ፤ ታምራት መሀመድ፤ ሰለሞን አበበ እና ይናገር መንገሻ ናቸው፡፡

የኢዴፓ አባላት በፖሊስ ቁጥጥር ስር የዋሉት ከጠዋቱ 4 ሰአት ጀምሮ እንደሆነ እና በቅስቀሳው ላይ ፓርቲው ተከራይቶት የነበረው መኪና ህገወጥ መሆኑ፤ ታርጋውም ተነቅሎ እንደተወሰደ አቶ አለማየሁ ባልዳ የፓርቲው ብሄራዊ ምክር ቤት አባል ገልጸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ያነጋገርናቸው የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው እንደገለጹት ኢዴፓ የህዝባዊ ስብሰባውን ፈቃድ በህጋዊ መልኩ አውጥቶ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቅሰው እንዲህ አይነቱ ሁኔታ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲ እየተጠናከረ ከመሄድ ይልቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸረ መምጣቱን ማሳያ ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የሕዝባዊ ስብሰባ ጥሪ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሐምሌ 12 ቀን 2006 ዓ.ም. ከቀኑ 7 ሰአት ጀምሮ ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የመብራት ኃይል አዳራሽ ከአዲስ አበባ ነዋሪዎች ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ሕዝባዊ ስብሰባ ያካሂዳል፡፡ በመሆኑም በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲሳተፉ ኢዴፓ ደጋፊዎቹን እና የአገር ጉዳይ የሚያሳስባቸውን መላው የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ይጋብዛል፡፡

ኢዴፓ የዛሬውና የወደፊቱ ትውልድ ፓርቲ!!!

ኢዴፓ በመቐለ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው

ኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ ባስቀመጠው የሦስተኛ አማራጭነት ሚናውን ወደ ህዝብ የማስረጽ እቅድ አንዱ አካል የሆነው ህዝባዊ ስብሰባ በማካሄድ ከህዝብ ጋር የመወያያ መድረክ ማዘጋጀት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ አካል የሆነው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባ እንደተጠናቀቀ ስራ አስፈጻሚው ወደ መቀሌ ጉዞ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡  ስራ አስፈፃሚው የህዝባዊ ስብሰባውን በሌሎች ክልል ከተሞች ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከጽ/ቤቱ እንዳገኘነው መረጃ ሌሎች ህዝባዊ ስብሰባው የሚካሄድባቸው የክልል ከተሞች መካከል ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣  ናዝሬት፣ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2007 ምርጫ ፓርቲውን ይረዳው ዘንድ በአፋር ክልል አምስቱ ዞኖች በቤንሻንጉል ጉምዝ ስምንት ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም በአገሪቱም አራቱም አቅጣጫዎች ድርጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የኢዴፓ አመራሮች ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ቦርድ ከundp ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩንና በምርጫ 2007 ፓርቲዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ ዙርያ ለማወያየት ለሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ መሰረት ኢዴፓን ጨምሮ 8 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በቦታው ላይ የተገኙትም የፓርቲ ተወካዮች በጋራና በተናጥል ስለ ፖለቲካ ምህዳሩና ስለ ምርጫ 2007 ተሳትፎአቸው ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ሲሆኑ በቦታው የተገኙት የፓርቲው የጥናትና ምርምር ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የፓርቲውን አቋም ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርምያስ ባልከው ለ5 ቀናት ደብረ ዘይት በሚገኘው የስራ አመራር ኢንስቲትዩት በግጭት አፈታት (conflict management) ዙርያ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመልሰዋል፡፡ በስልጠናው ላይ ኢህአዴግን ጨምሮ 23 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡  ፓርቲዎቹ በግጭት አፈታት ዙርያ ያላቸውን ተሞከሮ በውይይትና በቡድን ስራ ላይ እርስ በርስ የተለዋወጡ ሲሆን  ችግር እንዳይፈጠርና ችግር ተፈጥሮም ቢገኝ  ፓርቲዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችን መዳበር እንዳለበት መጠቆማቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያም የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ለስልጠናው ተካፋዮች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡ ይሄ ስልጠና ለ2ኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን በመጀመርያ ዙር በተካሄደው ስልጠና ላይ የፓርቲው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ አዳነ ታደሰ ተካፍለው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡