Clicky

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት (አብሮነት) የሕዳሴውን ድርድር አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ

ቀን 30/5/2012 ዓ.ም
ቁጥር አብሮነት/005/12

የህዳሴ ግድብ የመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻ መሆን የለበትም!

በቅርቡ በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ አደራዳሪነት በዋሽንግተን ዲሲ የህዳሴውን ግድብ አጠቃቀም አስመልክቶ ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሶስትዮሽ ድርድር በከፍተኛ ፍጥነት እያካሄዱ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይህ ድርድር በቅርብ ግዜ ስምምነት ላይ ሊደርስ እና በፊርማ ሊቋጭ እንደሚችል በተደራዳሪ አካላቱ በኩል እየተገለፀ ይገኛል፡፡

ይህ የህዳሴ ግድብ ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ያለው በዋጋ ሊተመን የማይችል የኢትዮጵያ ህዝብ እጅግ ጠቃሚ ፕሮጀክት ስለመሆኑ አብሮነት ይገነዘባል፡፡ በዚህ ግድብ ላይ የሚደረገው ይህ የሶስትዮሽ ድርድርም የዛሬውን ብቻ ሳይሆን የወደፊቱን ትውልድ ጥቅም የሚወስን፣ የኢትዮጵያን ብቻ ሳይሆን ከአስር የማያንሱ የአፍሪካ አገሮችን ጥቅም የሚመለከት ድርድር እንደሆነ አብሮነት ይገነዘባል፡፡

በህዳሴ ግድብ ላይ የሚካሄድ ድርድር ይህንን ያህል ከፍተኛ የሆነ አገራዊና አህጉራዊ ፋይዳ ያለው ጉዳይ መሆኑ እየታወቀ፣ የግብፅ የቅርብ ወዳጅ የሆኑት አሜሪካ እና ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት አሸማጋይ ለመሆን የፈለጉበትን የድርድር ጥያቄ ኢትዮጵያ ከመጀመሪያውም መቀበል አልነበረባትም፡፡ ከዚህ ድርድር ጀርባ ያሉ አገራት እና ተቋማት በሙሉ ከኢትዮጵያ ይልቅ የግብፅ ወዳጅ የሆኑና ይህንን ድርድር ለመካከለኛው ምስራቅ ችግር መፍቻነት ሊጠቀሙበት የሚፈልጉ መሆኑ ግልፅ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ሃይላት የአደራዳሪነቱን ሚና በወሰዱበት ሁኔታም የኢትዮጵያን ጥቅም ሊያስጠብቅ የሚችል የድርድር ውጤት ሊገኝ እንደማይችል አስቀድሞ የታወቀ ነው፡፡
ይህ ድርድር መጀመሪያውኑ ከአፍሪካ ማዕቀፍ ወጥቶ በእነዚህ የሩቅ እና ገለልተኛ ያልሆኑ ሃይሎች አደራዳሪነት እንዲካሄድ ስምምነት ላይ መደረሱ ትልቅ ታሪካዊ ስህተት ነው ብሎ አብሮነት ያምናል፡፡

ስለሆነም ይህ ከአገር ብሔራዊ ደህንነት ጋር የተያያዘ ትልቅ አገራዊ ጉዳይ በጥድፊያ እና ግልፅነት በጎደለው ሁኔታ መወሰን ስለሌለበት-
የድርድሩን ሰነድ በስምምነት ለመቋጨት የተያዘው ግዜ ላልተወሰነ ግዜ እንዲራዘም፤
በዚህ በሚራዘመው ግዜም በቂ መድረክ ተፈጥሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት፣ ከህዝብ እና ከአፍሪካ ወዳጅ አገሮች ጋር ጭምር ግልፅ ውይይትና ምክክር እንዲካሄድ፤
የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብም ይህንን ጉዳይ በትኩረት እንዲከታተልና ይህ ስምምነት ከእሱ ዕውቅና ውጭ በጥድፊያ እንዳይፈረም በመንግስት ላይ የራሱን ተፅዕኖ እንዲፈጥር አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት)
ጥር 30/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

መልዕክት ከኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ

በምርጫ ቦርድ በተደረገበት ሕገወጥ የማፍረስ ጣልቃገብነት ምክንያት ፓርቲያችን ከመደበኛ የድርጅት ስራ ለዓመታት ተስተጓጉሎ እንደነበር ይታወቃል። “በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንደሚባለው በሥርዓቱ ባህሪ ምክንያት እንደሌሎቹ ተቃዋሚዎች ሁሉ ተዳክሞ የነበረው የኢዴፓ መዋቅር በልዩ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ጣልቃ ገብቶ ያንኮታኮተው በመሆኑ መደበኛው የፓርቲው መዋቅር ዳግም ተነቃቅቶ እስኪመለስ ድረስ የአካባቢ አስተባባሪ ኮሚቴዎችን መመደብ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል። በየአካባቢው እየተቋቋሙ ያሉ ኮሚቴዎች ከ 5 እስከ 8 ዓባላት ያሏቸው ሲሆን የኮሚቴዎቹን አስተባባሪዎች አድራሻ በተከታታይ የምናሳውቅ ይሆናል።

በዚሁ መሰረት በየአካባቢያችሁ በኮሚቴ አባልነትም ሆነ አስተባባሪነት መሳተፍ የምትፈልጉ ዜጎች ባመቻችሁ የፓርቲ አመራር የዕጅ ስልኮች በመደወል አልያም በዚህ ገጽ መልዕክት በመላክ ልታገኙን ትችላላችሁ!

 1. የአዲስ አበባ ከተማና አቅራቢያው አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ መንበሩ 0922452068
  1. ቂርቆስ ክፍለ ከተማና አካባቢው አቶ ተስፋዬ መንበሩ
   ስልክ፦ 0922452068
  2. ቦሌ ክፍለ ከተማና አካባቢው አቶ ግዛቸው አንማው
   ስልክ፦0910284549
  3. የካ ክፍለ ከተማና አካባቢው አቶ አብዱረህማን አራጋው ስልክ፦ 0900968353
  4. አራዳ ክፍለ ከተማና አቅራቢያው አቶ መንገሻ ወ/ሚካኤል ስልክ፦ 0912477965
  5. ን/ስ/ላፍቶ ክ/ከተማና አቅራቢያው አቶ ፈንታቢል ይደርሳል ስልክ፦ 0918483111
  6. አዲስ ከተማ ክ/ከተማ አቶ የሽዋስ ፋንታሁን
   ስልክ፦0969872435
  7. ጉለሌ ክ/ከተማና አቅራቢያው አቶ ፍቃዱ ወዳጅ
   ስልክ፦ 0983901
  8. ኮልፌ ቀራኒዮ ክ/ከተማ፦ሀ) አቶ ስናማው ተፈሪ
   ስልክ፦0908987443
 2. የጎንደር ከተማና አቅራቢያው አስተባባሪ አቶ ተስፋማሪያም ጌትነት 0918773063
 3. የሐዋሳ ከተማና አቅራቢያው አስተባባሪ
  1. አቶ ደረጄ ዘርጋው 0911428809
  2. አቶ ገነነ ጊቶሬ 0916046668
  3. አቶ ሕዝቄል ካሣ 0923478657
  4. አቶ ገብሬ ቹቾ 0916036769
  5. አቃቂ ቃሊቲ ክ/ከተማ፦ አቶ አለበል ዓለም ስልክ፦0913134316
 4. የባህርዳር ከተማና አቅራቢያው አስተባባሪ አቶ ብዙአለም ስመኝ 0913062368
 5. አለታወንዶ ከተማና አካባቢው አስተባባሪ አቶ ተሾመ ደምሴ +251916981983
 6. ደሴ ከተማና አካባቢው አስተባባሪ አቶ አስናቀ ድረስ +251 94 206 5455
 7. የዲሬዳዋ ከተማና አካባቢው አስተባባሪ አቶ ደረጄ ደበበ ስልክ 0911899404
 8. የዱራሜ ከተማና የከምባታ ጠምባሮ ዞን አካባቢዎች አስተባባሪ አቶ አድማሱ ጎታ 0916874935
 9. የደብረታቦር ከተማና የደቡብ ጎንደር ዞን አካባቢዎች አስተባባሪዎች አቶ ፍስሃ ዳምጤ 0913135960 እና አቶ ጌታነህ ብሬ 0921380913
 10. የወልቂጤ ከተማና የጉራጌ ዞን አካባቢ አስተባባሪ አቶ ገረመው አያሌው +251970633070
 11. አርባምንጭ ከተማ እና ሌሎች የጋሞ አካባቢዎች አስተባባሪ አቶ ተስፋዬ ደስታ ስልክ 0920984335
 12. በደብረ ብርሃን ከተማ እና ሌሎች የሰሜን ሸዋ አካባቢ አስተባባሪዎች አቶ ብሩክ ለይኩን ስልክ 0912315044 እና አቶ ልዑል አስናቀ ስልክ 0933197472
 13. በሶዶ፣ ሳውላ፣ ታርጫ እና ዋካ ከተሞችና በመላው የዎላይታ፣ ጎፋ እና ዳውሮ አካባቢ አስተባባሪዎች አቶ ታምራት ከበደ ስልክ 0912083832 እና አቶ ቢንያም ጴጥሮስ ስልክ 0913269771
 14. በ ደ/ማርቆስ ከተማ እና በሌሎች የ ምስ/ጎጃም ዞን አካባቢዎች አስተባባሪ አለምብርሃን ተፈራ ስልክ +251912374437
 15. በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ከተማ ክ/ከተማ አስተባባሪ ወ/ሮ ዓለም ዘውዱ +251910521717

 

 

ከአብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተሰጠ መግለጫ

ብሔራዊ ደህንነት ከምርጫ በፊት!

በቅርቡ የተቋቋመው አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት (አብሮነት) የተቋቋመለትን ውስን ዓላማ መሰረት አድርጎ የተግባር እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ጀምሯል።

ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ

በምርጫ ዘመቻ ዝግጅትና ክንውን ዙሪያ ለተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት አባላት የተዘጋጀ ስልጠና ተካሄደ

The national democratic Institute for International affairs (NDI) የተሰኘ ተቋም በምርጫ ዘመቻ ዝግጅትና ክንውን ዙሪያ ለተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት አባላት ያዘጋጀው የሁለት ቀን ስልጠና ተካሄደ።

ጃንዋሪ 21 እና 22 ቀን 2020 ዓ/ም በ ቤስት ዌስተርን ሆቴል ኘላስ በተካሄደው በዚህ ስልጠና ላይ የተካፈለው የኢዴፓ ልዑክ ውጤታማ ተሳትፎ ማድረጉን ልዑኩን በመምራት የተሳተፉት የፓርቲያችን ም/ኘሬዚደንት ወ/ሪት ጽጌ ጥበቡ ገልጸዋል።

አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት!!! የመግባቢያ ሠነድ

ቀን- 21/04/2012 ዓ.ም
ቁጥር- አብሮነት/002/12
አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ አንድነት!!!
የመግባቢያ ሠነድ

በአገራችን በኢትዮጵያ ቢያንስ ላለፉት 50 ዓመታት የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገዛዝ ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመሸጋገር በተደረገ ትግል ከፍተኛ መስዋትነት ሲከፍል ቆይቷል፡፡ ይሁንና በአንድ በኩል በአገራችን ተንሰራፍቶ በቆየውና የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንን በሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመፍታት ባላስቻለን ኋላቀር የፖለቲካ ባህላችን ምክኒያት፣ በሌላ በኩል ደግሞ በአገራችን የፖለቲካ ልሂቃን ባለው ከፍተኛ የአመራር ድክመት ምክኒያት የህዝባችን የለውጥ ፍላጎትና ትግል ስኬታማ ሳይሆን ቀርቷል፡፡
ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን መምጣት ጋር ተያይዞ የዛሬ 18 ወር በአገራችን የተከሰተው የለውጥ ሂደት በህዝባችን ውስጥ ከፍተኛ ተስፋ ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም እንደአለመታደል ሆኖ ይህም የለውጥ ሂደት ወደ ስምረት ሳይሆን በከፍተኛ ፍጥነት ወደ ክሽፈት እያመራ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ የለውጥ ሂደቱን ሁሉን አቀፍ በሆነ የጋራ የሽግግር ተቋምና ከእንዲህ ዓይነቱ ተቋም የውይይትና የድርድር ሂደት በመነጨ ፍኖተ-ካርታ እንዲመራ ማድረግ ሲገባው፣ በተለምዶ አምባገነናዊ ባህሪው “እኔ አሻግራችኋለው” በሚል መታበይ በራሱ ፍላጎትና መንገድ ብቻ ሊመራው በመሞከሩ የለውጥ ሂደቱ የመክሸፍ አደጋ ገጥሞታል፡፡

አገራችን ለገጠማት የፖለቲካ ቀውስ መነሻ ምክንያት ለሆኑ መዋቅራዊ ችግሮቻችን ትርጉም ያለው መዋቅራዊ መፍትሄ ለመስጠት ሙከራ ባልተደረገበት፣ በተካረረ የፅንፍ አመለካከት ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሃይሎች ብሄራዊ እርቅ ሳያካሂዱና በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሄራዊ መግባባት ባልተፈጠረበት ሁኔታ በጥድፊያ ወደ አገራዊ ምርጫ ለመግባት እየተደረገ ያለው ሙከራ የተጀመረው የለውጥ ሂደት ተስፋ አስቆራጭ በሆነ መጠን የመክሸፍ አደጋ ውስጥ መግባቱን የሚያሳይ ነው፡፡

የተጀመረው የለውጥ ሂደት አግባብ ባለው መንገድ ባለመመራቱ ምክንያት አገራችን በአሁኑ ወቅት ህልውናዋን የሚፈታተን አደጋ ውስጥ ትገኛለች፡፡ ዛሬ በአገራችን በታሪካችን አይተነው በማናውቀው መጠን ብሄር ተኮር የሆነ የህዝብ ለህዝብ የእርስ በርስ ግጭት እየተከሰተ በብዙ ሺ ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን መሞትና በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዜጎቻችን መፈናቀልና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ አሁንም በታሪካችን አይተነው በማናውቀው ሁኔታ ለበርካታ አብያተ ክርስቲያኖችና መስጂዶች መቃጠል ምክንያት የሆነ እና ፖለቲካዊ አጀንዳ ያዘሉ ግጭቶች በተለያዩ የአገራችን አካባቢዎች እየተከሰቱ ነው፡፡ የአገራችን የጸጥታ መዋቅሮች በአግባቡ ሃላፊነታቸውን መወጣት ባለመቻላቸው በአብዛኛው የአገሪቱ አካባቢዎች ህግና ስርዓትን ማስፈን ያልተቻለበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በዚህም ምክንያት ዜጎች ከፍተኛ የህይወት ስጋት ውስጥ የገቡበትና በዕለት-ተዕለት ስራቸውና የወደፊት ህልውናቸውን በሚወስን የልማት ስራ ላይ ማተኮር የማይችሉበት ሁኔታ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በአጠቃላይም የለውጥ ሂደቱን በአግባቡ መርቶ ለስኬት እንዲያበቃ አደራ የተሰጠው ገዥው ፓርቲ በተለመደ ባህሉ የእርስ-በርስ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ በመግባቱ ምክንያት አገሪቱ ወዴት እንደምታመራ አቅጣጫ ያጣችበት እና በማንኛውም ከፊታችን ባለ አንድ አጋጣሚና ቅፅበት ወደ የእርስ-በርስ ጦርነት ወይም መንግስት የለሽነት አደጋ ልትገባ የምትችልበት ሁኔታ ውስጥ ትገኛለች፡፡

ይህ የአገራችን የህልውና አደጋ በእጅጉ ያሳሰበንና አገራችንን ከዚህ የህልውና አደጋ መታደግ የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ቀዳሚ ወቅታዊ ትኩረት መሆን ይገባዋል ብለን ያመን ሶስት አገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ይህንን የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም የሚከተሉትን ተግባራት በጋራና በትብብር ለመስራት ወስነናል፡፡

በተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ በመካከላችን ያሉና የሚኖሩ ልዩነቶች እንደተጠበቁ ሆነው የአገራችንን ህልውና መቀጠል በተመለከተ ግን አንድ የጋራ ኮሚቴ አቋቁመን በትብብር ለመስራት ተስማምተናል፡፡ ኮሚቴው ከአገራዊ ህልውና ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን በተመለከተ የጋራ ምክክር በማድረግ የጋራ መግለጫዎች ያወጣል፣ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝም ህዝባዊ ስብሰባዎችንና ሰላማዊ ሰልፎችን በጋራ ያካሂዳል፡፡

የአገር ህልውናን በተመለከተ ተመሳሳይ አቋም ካላቸው ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ቀጣይ ግንኙነት በመፍጠር ይህንን በኛ የተጀመረ ግንኙነት በሂደት የበለጠ ለማስፋትና ለማጠናከር ተስማምተናል፡፡ ይህም ስምምነት በአሁኑ ወቅት እራሳቸውን በማሰባሰብ ለማጠናከር እየሞከሩ የሚገኙ የኮንፌዴሬሽን ኃይሎች በአገሪቱ ህልውና ላይ ሊፈጥሩ የሚችሉትን አደጋ ለመቋቋም የሚያስችል አንድ ጠንካራና እውነተኛ የፌደራሊስቶች ጎራ በአገሪቱ መፍጠርን ዓላማው ያደረገ ነው፡፡

ወደፊት በአገራችን በሚካሄደው አገራዊ ምርጫ (መቼም ይካሄድ መቼ) በአንድ የምርጫ ማንፌስቶ በጋራ ለመወዳደርና ምርጫውን ለማሸነፍ የሚያስችለንን ውይይትና ድርድር ከወዲሁ ለመጀመርና፣ ከምርጫው በኋላ የጥምር መንግስት ለማቋቋም የሚያስገድድ ሁኔታ ቢፈጠር ድርድርና ስምምነት ከምርጫው በፊት ለማካሄድ ተስማምተናል፡፡
ይህንን ውስን ለሆነ ነገር ግን ለታላቅ አገራዊ ዓላማ የጀመርነውን ትብብርም “አብሮነት ለኢትዮጵያ ፌደራላዊ አንድነት “(አብሮነት) ብለን ለመጥራት ተስማምተናል፡፡

በመጨረሻም አገራዊ ህልውናን በተመለከተ ከእኛ ጋር ተመሳሳይ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሳሳይ የመግባቢያ ሰነድ በመፈረም አብረውን እንዲሰሩ ጥሪያችንን እያቀረብን፣ ይህ ጥረታችን እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የአገር ህልውናን ከጥፋት ለመታደግ የሚደረግ መሆኑን በመገንዘብም አገር ወዳድ የሆነ ማንኛውም ዜጋ ሁሉ ሁለንተናዊ ትብብር በማድረግ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪያችንን በዚህ አጋጣሚ እናቀርባለን፡፡

ህብር ኢትዮጵያ ኢዴፓ ኢሀን

ኢዴፓ፤ ኢሀንና ኅብር ኢትዮጵያ በጋራ ማኒፌስቶ ለመወዳደር የመጀመርያውን ስምምነት ፈጸሙ

የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)፣ የኢትዮጵያ ሀገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢሀን) እና ኅብር ኢትዮጵያ ‹‹የኢትዮጵያ ኮንፌዴራሊስት ኃይሎች በሀገሪቱ ኅልውና ላይ ሊፈጥሩት የሚችሉትን አደጋ ለመቋቋም አልመናል›› በሚል ሦስት የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት ፈጠሩ::

 

ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠትን በሚመለከት

የአገራችን የህልውና አደጋ በእጅጉ ያሳሰበንና አገራችንን ከዚህ የህልውና አደጋ መታደግ የአገሪቱ የፖለቲካ ሃይሎች ቀዳሚ ወቅታዊ ትኩረት መሆን ይገባዋል ብለን ያመን ሶስት አገር አቀፍ ፓርቲዎች ህብር ኢትዮጵያ፣ ኢዴፓ እና ኢሀን የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በጋራ እና በትብብር ለመስራት ወስነናል። በስምነታችን ዙሪያ በአዜማን ሆቴል ማክሰኞ በ21/4/2012 ዓ.ም በጋራ ጋዜጣዊ መግለጫ እንሰጣለን ሁላችሁም የመገናኛ ብዙሃን ተጋብዛችኋል።

ከኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ

Ethiopian Democratic Party - Press Releaseቀዳሚ ትኩረት ለአገራዊ ህልውና!!

ኢዴፓ በሃያ ዓመታት የትግል ጉዞው ለሶስተኛ ጊዜ የገጠመውን የህልውና አደጋ እልህ አስጨራሽ የሆነ ትግል በማካሄድ አክሽፎታል፡፡ በገዥው ፓርቲ፣ በኢትዮጵያ የምርጫ ቦርድ፣ በግንቦት 7 እና በአራት የራሳችን የፓርቲ አባላት ትብብርና ቅንጅት የፓርቲያችንን ህልውና ለማጥፋት ላለፉት ሶስት ዓመታት የተካሄደብንን ዘመቻ በማያዳግም ሁኔታ አክሽፈን ወደ ትግሉ ጎራ እነሆ ተቀላቅለናል፡፡

የኢዴፓ አመራር አባላት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አምስት አባላት ጋር ህዳር 29 ቀን 2012 ዓ.ም ሰፊ ውይይት ካደረግን በኋላ ቦርዱ ታህሳስ 6 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ እነ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ከኢዴፓ አመራርነታቸው በፓርቲው ህገ-ደንብ መሰረት የተነሱ መሆኑን በማመን፣ እነ ዶ/ር ጫኔ አካሄድነው ያሉት ጠቅላላ ጐባኤና ከኢዜማ ጋር አደረግነው ያሉት ውህደትም ህገ-ወጥና በተጭበረበረ መንገድ የተፈፀመ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በአሁኑ ወቅት በስራ ላይ ያለው የኢዴፓ አመራርም በፓርቲው ህገ-ደንብ መሰረት የተመረጠ መሆኑን በማረጋገጥ፣ በአጠቃላይም ኢዴፓ ቀድሞውንም ቢሆን ያልፈረሰና አሁንም ህጋዊ እውቅና ያለው ፓርቲ መሆኑን ቦርዱ በሙሉ ድምፅ ተቀብሏል፡፡ የምርጫ ቦርዱ ይህንን ውሳኔውንም ለተለያዩ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት በደብዳቤ አሳውቋል፡፡

ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በፓርቲያችን ላይ ላለፉት ሶስት ዓመታት የፈፀመው ደባ እጅግ አሳዛኝና ከአንድ ትልቅ አገራዊ ሃላፊነት ከሚጠበቅበት የዲሞክራሲ ተቋም የማይጠበቅ አሳፋሪ ተግባር ቢሆንም በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተሾሙት አምስቱ የቦርዱ አባላት በመጨረሻ የወሰኑት ይህ ውሳኔ ግን ትክክለኛና በሴራ የተቀማነውን ፍትህ ወደ ቦታው የመለሰ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ለዚህ ውሳኔያቸውም ኢዴፓ ለአምስቱ የምርጫ ቦርድ አባላት ያለውን ልባዊ ምስጋና በዚህ አጋጣሚ ያቀርባል፡፡

በግፍ የተቀማችሁትን ፍትህ በእልህ አስጨራሽ ትግላችሁ መልሳችሁ ለማግኘት ለበቃችሁ የኢዴፓ አባላት፣ የኢዴፓን ሃቀኛ አቋሞችና ምክንያታዊ አስተሳሰቦች ስትናፍቁ ለኖራችሁ ደጋፊዎቻችን እንኳን ደስ አላችሁ! እያልን ከዛሬ ጀምሮ በሙሉ ትኩረትና አቅም ወደ ትግሉ ሜዳ መመለሳችንን በከፍተኛ ደስታ እንገልጻለን፡፡ በዚህ አስቸጋሪ ሂደት የተጓደለብን ፍትህ ወደ ቦታዉ እንዲመለስ ሁለንተናዊ እገዛ ላደረጋችሁልን በውጭ የምትኖሩ የድጋፍ ሰጪ ኮሚቴዎች፣ ጋዜጠኞችና የሚድያ ተቋማት በሙሉ ያለንን አክብሮትና ልባዊ ምስጋና በዚህ አጋጣሚ እንገልፃለን፡፡

ከዚህ አስደሳች የምርጫ ቦርድ ውሳኔ በኋላ አስቸኳይ ስብሰባ ያካሄደው የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴና የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት በተለያዩ የፓርቲው ውስጣዊ ጉዳዮችና በአገሪቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አካሂደው የወሰዷቸውን አቋሞችና የደረሱባቸውን ውሳኔዎች እንደሚከተለው እንገልፃለን፡፡

የፓርቲውን ውስጣዊ ሁኔታ በተመለከተ

ኢዴፓ የዕለት-ተዕለት ስራውን በአግባቡ ማካሄድ እንዲችል በቅድሚያ በህገ-ወጥ መንገድ በኢዜማ እጅ የሚገኙትን ቢሮዎቹን፣ የተለያዩ ኃብትና ንብረቶቹን የማስመሰል ስራ ለመስራት ወስኗል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሰረትም የፓርቲው ምክር ቤት በቅድሚያ በጤናማ የመግባባት መንፈስ የኢዜማ አመራሮችን ቀርቦ በማነጋገር ችግሩ እንዲፈታ ጥረት እንዲደረግ፣ በዚህ መንገድ ችግሩን መፍታት ካልተቻለ ግን በአስተዳደራዊና ህጋዊ መንገዶች ንብረቶቹን ለማስመለስ ወስኗል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ውሳኔ በኋላ የኢዜማ አመራሮችን አግኝተን ለማነጋገርና ችግሩን በመግባባት ለመፍታት ያደረግነው ጥረት በኢዜማ በኩል በጐ ምላሽ ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ በኛ ዕምነት አገራችን እጅግ አሳሳቢ የህልውና አደጋ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት ከኢዜማም ሆነ ከማንኛውም ፓርቲ ጋር በትብብር እና በመከባበር መንፈስ የመስራት እንጂ አላስፈላጊ ቅራኔና ግጭት ውስጥ የመግባት ፍላጐት የለንም፡፡

ስለሆነም አላስፈላጊ የሆነ ጊዜና ጉልበት ሁለታችንም ከማባከናችን በፊት በኢትዮጵያ ማህበራዊ ፍትህ አመጣለሁ ብሎ የሚታገለው ኢዜማ በህገ-ወጥ መንገድ የያዛቸውን ንብረቶቻችንን በሰላምና በመግባባት መንፈስ በማስረከብ ፍትህን እንዲያከብር በዚህ አጋጣሚ ይፋዊ ጥያቄያችንን እናቀርባለን፡፡ በኛ እምነት ብልህ ፓርቲ ጠቃሚ አስተሳሰቦቻችንን እንጂ ሃብትና ንብረታችንን በመቀማት የሚያገኘው ጥቅም አይኖርም፡፡ በዚህ ረገድ የገጠመንንም ችግር ተከታትሎና አጣርቶ ሃቁን ለህዝብ በማሳወቅ ረገድ መገናኛ ብዙሃን አስፈላጊውን ትብብር እንድታደርጉልን በዚህ አጋጣሚ በአክብሮት እየጠየቅን በእኛ በኩል በወቅታዊና በወደፊቱ የአገራችን አሳሳቢ ችግሮች ላይ የማተኮር እንጂ ከእንግዲህ ወደ አሳለፍነው አስቸጋሪ ሂደት ተመልሰን የመግባት ፍላጐት የሌለን መሆኑንም ለማሳወቅ እንወዳለን፡፡

ፓርቲው በአሁኑ ወቅት የሚጠበቅበትን ከፍተኛ አገራዊ ሃላፊነት በአግባቡ ለመወጣት የሚያስችል ምንም አይነት ቢሮም ሆነ ሃብትና ንብረት በእጁ የሌለ መሆኑን በመገንዘብም የኢዴፓን አላማ የምትደግፉ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ኗሪ የሆናችሁ አገር ወዳድ ዜጐች አቅማችሁ በፈቀደ መጠን የገንዘብና የቁሳቁስ እርዳታ እንድታደርጉልን በዚህ አጋጣሚ እንጠይቃለን፡፡
የፓርቲዉን ጠቅላላ ጉባኤ በተመለከተ

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ከአምስት ወራት በፊት የፓርቲው 7ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ እንዲካሄድ ወስኖ የነበረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቢሆንም ከህልውናው ጋር በተያያዘ በገጠመው ችግር ምክንያት ባለፉት አምስት ወራት ለጉባኤው መሳካት የሚያግዙ በቂ ስራዎችን መስራት ሳይችል ቀርቷል፡፡ ይህንን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የፓርቲው 7ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባኤ አስፈላጊ ቅድመ-ሁኔታዎችን በፍጥነት በማከናወን ከአሁን ጀምሮ ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ እንዲካሄድ ብሔራዊ ምክር ቤቱ በድጋሚ ወስኗል፡፡ ከአምስት ወራት በፊት ጉባኤውን እንዲያዘጋጅ ተመርጦ የነበረው ኮሚቴም ባለበት ሁኔታ ስራውን እንዲቀጥልና ለጉባኤው ስኬታማነት አስፈላጊ የሆኑትን ስራዎች በፍጥነት እንዲጀመር ወስኗል፡፡

Ethiopian Democratic Party - Press Release

ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ
በዚህ አጀንዳ ላይ በተደረገው ውይይት በቅድሚያ ትኩረት የተሰጠው የወቅቱን “የለውጥ ሂደት” መገምገም ነበር፡፡ ምክር ቤቱ ባካሄደው ሰፊ ውይይትና ግምገማም- ላለፉት 18 ወራት በአገራችን ሲካሄድ የነበረውና በህዝብ ውስጥ ከፍተኛ የለውጥ ተስፋ ፈጥሮ የነበረው “የለውጥ ሂደት” በሚያሳዝን ሁኔታ ወደ መክሸፍ ደረጃ መቃረቡን ምክር ቤቱ ተገንዝቧል፡፡
“የለውጥ ሂደቱ” ሁሉን አቀፍ በሆነ የሽግግር ተቋምና ከእንዲህ አይነቱ የጋራ አገራዊ ተቋም ድርድርና ስምምነት በመነጨ ፍኖተ-ካርታ መመራት ሲገባው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለመደ አምባገነናዊ ባህሪው ሂደቱን በራሱ መንገድና ፍላጐት ብቻ ሊመራው በመሞከሩ “የለውጥ ሂደቱ” የመክሸፍ አደጋ ገጥሞታል፡፡ “የለውጥ አመራር” ነኝ የሚለው ኃይል ላለፉት 28 ዓመታት በአገርና በህዝብ ላይ የፈፀመውን ግፍና በደል የወቅቱን የለውጥ ሂደት ህዝቡ በሚጠብቀው መጠን ስኬታማ በማድረግ መካስ ሲገባው ይባስ ብሎ ወደ የእርስ-በርስ የስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ራሱን በማስገባት ህዝቡ በድጋሜ የሰጠውን አደራ እና ዕድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ ገዥው ፓርቲ የለውጥ ሂደቱን ስኬታማ ሊያደርጉ የሚችሉ ተግባራትን ሳያከናውን ምርጫው እንዲካሄድ መወሰኑ የሚያሳየን ከእንግዲህ “በለውጥ አመራሩ” አማካኝነት ሊሳካ የሚችል የለውጥ ሂደት አለመኖሩ ነው፡፡ ይህም ሁኔታ ከዚህ ቀደም ኢዴፓ የሽግግር መንግስት ማቋቋም ሳያስፈልግ አንድ ሁሉን አቀፍ የሆነ የሽግግር ኮሚሽን በማቋቋም የለውጥ ሂደቱን ማሳካት እንደሚቻል ሲያራምድ የነበረውን አቋም እንደገና እንዲመረምር አስገድዶታል፡፡

የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ባካሄደው ሰፊ ውይይት ከአሁን በኋላ “የለውጥ አመራር” ነኝ የሚለው ገዥ ፓርቲ ወይም አዲሱ ብልፅግና ፓርቲ ይህንን ከፍተኛ የህዝብ አደራ የመወጣት ፍላጐትና አቅም እንደሌለው ተገንዝቧል፡፡ ከአሁን በኋላም ይህ የመክሸፍ አደጋ የገጠመው የለውጥ ሂደት ከአጠቃላይ ክሽፈት ተርፎ ወደ ስኬት ሊሸጋገር የሚችለው አንድ ሁሉን አቀፍ የእርቅና የሽግግር መንግስት በአስቸኳይ በማቋቋም ብቻ መሆኑን አምኖበታል፡፡ ስለሆነም በህዝብ ትግል አሸናፊነት ምክንያት ተጀምሮ የነበረው የለውጥ ሂደት ስኬታማ የመሆኑና መሆን ያለመቻሉ ጉዳይ የአገራችንን አጠቃላይ ህልውና የሚወስን አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ መንግስት የፊታችን ግንቦት ወር ሊካሄድ የታሰበውን አገራዊ ምርጫ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ በማራዘም ሁሉን አቀፍ የእርቅና የሽግግር መንግስት በአጭር ጊዜ የሚቋቋምበትን ሁኔታ እንዲያመቻች እንጠይቃለን፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብም ከእንግዲህ ስልጣን ላይ ባለው ገዥ ፓርቲ አገራዊ ህልውናችንን አስጠብቆ ለማስቀጠል የሚያስችል ዘላቂ መፍትሄ ሊመጣ እንደማይችል ተገንዝቦ እያቀረብነው ያለውን የእርቅና የሽግግር መንግስት የማቋቋም ጥያቄ እንዲደግፍ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ በእርግጠኝነት ከምናውቀው የገዥው ፓርቲ ማንነትና ባህሪ አንፃርም ይህንን አገራዊ ጥያቄ እንዲሁ ጥያቄ በማቅረብ ብቻ ማሳካት ስለማይቻል ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አገር-ወዳድ ኢትዮጵያዊያን በአስቸኳይ አንድ በአገር ህልውና ላይ የሚመካከር ጊዜያዊ መድረክ ፈጥረው ህዝቡን በማስተባበርና በመንግስት ላይ ተፅዕኖ በመፍጠር ይህ ጥያቄ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያስችል ትግል እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ ኢዴፓ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ አገር ወዳድ ዜጐች ይህንን ዓይነቱን መድረክ እንዲያቋቁሙ የበኩሉን ጥረት የሚያደርግ ሲሆን ሊቋቋም የሚገባው የእርቅና የሽግግር መንግስትም መቼ? እንዴት? በማንና ለምን? አላማ መቋቋም እንዳለበት የውይይት መነሻ የሚሆን ሰነድ በአጭር ጊዜ አዘጋጅቶ ለውይይት የሚያቀርብ መሆኑን ይገልፃል፡፡

በአጠቃላይ የኢዴፓ ወቅታዊ ትኩረት አገራዊ ህልውናን በመታደግ /National Salivation/ ላይ የሚያተኩር እንዲሆን የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት ወስኗል፡፡ ይህንን አሣሣቢ አገራዊ ሃላፊነት ለመወጣት እንዲቻልም የአገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች ትኩረት በእርስ በርስ የፖለቲካ ሽኩቻ ላይ መሆን እንደሌለበት በማመን ኢዴፓ ከማንኛውም የአገሪቱ ህልውና ከሚያሳስበው የፖለቲካ ፓርቲ ጋር በመቀራረብና በትብብር መንፈስ መስራት እንዳለበት አጠቃላይ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ በዚህ ረገድ የፓርቲው አመራር ከሌሎች ፓርቲዎች ጋር ቀደም ሲል የጀመራቸው አንዳንድ ግንኙነቶችን አጠናክሮ እንዲቀጥልባቸው ምክር ቤቱ አሳስቧል፡፡

ከዚህ ውሳኔ ጋር በተያያዘም የኢዴፓ አመራር በአሁኑ ወቅት ከበርካታ ፓርቲዎች ጋር ግንኙነት እያደረገ የሚገኝ ሲሆን ከተወሰኑት ፓርቲዎች ጋር የጋራ የመግባቢያ ሰነድ የመፈራረም ደረጃ ላይ በቅርቡ ሊደርስ እንደሚችል ያለውን ግምትም በዚህ አጋጣሚ ለመግለፅ ይወዳል፡፡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ ይህንን ተልዕኮውን ለማሳካት ከሌሎች ፓርቲዎች እና ሶስተኛ ወገኖች ጋር የሚደረግን ግንኙነትና ድርድር በሃላፊነት የሚመራ አንድ ኮሚቴ ያቋቋመ ሲሆን ይህንን ኮሚቴ እንዲመሩም አቶ ልደቱ አያሌውን መርጧቸዋል፡፡

በአጠቃላይም በአሁኑ ወቅት እየተሰባሰቡና እየተጠናከሩ ያሉ የኮንፌዴሬሽን ሃይሎችን መቋቋም የሚችል አንድ እውነተኛ የፌደራል ጎራ የሆነ የፖለቲካ ሃይሎች ስብስብ በመፍጠር የአገሪቱን ህልውና ለመታደግ የሚያስችል እንቅስቃሴ እንዲደረግ ብሄራዊ ምክር ቤታችን አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
ከወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ምክር ቤታችን ባደረገው ውይይት በአሁኑ ወቅት አገሪቱን እየመራ ባለው ገዥ ፓርቲ ውስጥ እየታዬ ያለው የዕርስ-በርስ ክፍፍልና ፍጥጫ የአገሪቱን ችግሮች የበለጠ የሚያባብስ ውጤት የሚያስከትል አሣሣቢ ጉዳይ እንደሆነ ተገንዝቧል፡፡ ቀደም ሲል በአዴፓና በህወሃት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በአዴፓ ከፍተኛ አመራሮች መካከል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ በአሁኑ ወቅት በአዲሱ ብልፅግና ፓርቲና በህወሃት መካከል የሚታየው ቅራኔ ለአገራችን ህልውና ከፍተኛ ጣጣ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ችግር መሆኑ ታምኖበታል፡፡ ይህ በገዥው ፓርቲ ውስጥ የተፈጠረ ቅራኔም ለአገራችን ህልውና የመጨረሻ ደጀን የሆነውን የአገራችንን የመከላከያ ሰራዊት ችግር ውስጥ እንዳይከተው ከፍተኛ ስጋት ፈጥሮብናል፡፡ ኢዴፓ ገዥው ፓርቲ ከስልጣን ሽኩቻ ይልቅ የአገርን ህልውናና ጥቅምን በማስቀደም አሁንም ውስጣዊ ችግሮቹን ቅድሚያ ትኩረት ሰጥቶ የመፍታት ጥረት እንዲያደርግ ጥሪውን እያቀረበ፣ ኢዴፓ ከሚታወቅበት የሚዛናዊነትና የምክኒያታዊነት ሚና አኳያም በገዥው ፓርቲ ዙሪያ ያሉ ቅራኔዎች በሰላም እንዲፈቱ የበኩሉን አስተዋፅኦ የማበርከት ፍላጐት ያለው መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ይገልፃል፡፡

ከአገር ህልውናና ጥቅም አንፃር በአሁኑ ወቅት በአገራችን እየታዬ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታም በዙሪያው አንዳንድ አሳሳቢ ክስተቶች እየታዩበት እንደሆነ ፓርቲያችን ተገንዝቧል፡፡ በተለይም የኮንስትራክሽን ሴክተሩ በተቀዛቀዘበት በአሁኑ ወቅት እየታዬ ያለው ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከኢኮኖሚው አልፎ ፖለቲካዊ አለመረጋጋቱን የሚያባብስ ውጤት እንዳያስከትል ስጋት አድሮብናል፡፡ በከፍተኛ ጥድፊያ የመንግስት የንግድ ተቋማትን ለመሸጥ የሚደረገው ሙከራም ወደፊት ለባሰ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይዳርገን ስጋት ፈጥሮብናል፡፡

በአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ዙሪያ ገዥው ፓርቲ እየተከተለው ያለው ግልፅነት የጎደለውና ተቋማዊ ይዘት የሌለው አካሄድም ወደፊት የአገራችን ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂክ ጥቅም ላይ ከባድ አደጋ ይዞ እንዳይመጣ ስጋት እየተሰማን መሆኑን እንገልፃለን፡፡ በዚህ ወቅት በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ሊወስናቸው እና ሊያከናውናቸው የሚገቡ ተግባራት በዋናነት የሽግግር ሂደቱን ውጤታማ በማድረግ ላይ መወሰን ሲገባቸው በአሁኑ ወቅት ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑ በግልፅ የምናውቃቸው እና የማናውቃቸው ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ውሳኔዎች እየተሰጡ መሆናቸው አብዝቶ ያሳስበናል፡፡

መጭውን አገራዊ ምርጫ በተመለከተ
ከአሁን ቀደም ለመግለፅ እንደሞከርነው በአሁኑ ወቅት በአገራችን ሰላማዊና ለህዝብ መንግስት መመስረት የሚያበቃ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ነባራዊ ሁኔታ አለ ብለን እናምንም፡፡ በአሁኑ ወቅት ፓርቲዎች፣ መንግስትም ሆነ ህዝቡ ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የሞራልና የመዋቅር ዝግጅት የላቸውም፡፡ የፅንፈኝነትና የብሄርተኝነት ፖለቲካ ከፍተኛ ጡዘት ላይ በደረሰበት በአሁኑ ወቅት፣ አብዛኛዎቹ ማህበራዊና መደበኛ መገናኛ ብዙሃን የአክራሪ ኃይሎች የአቋም ማራመጃ መድረክ በሆኑበትና፣ ከሁሉም በላይ ስኬታማ የሽግግር ሂደት ባላካሄድንበትና መሰረታዊ የፖለቲካ ቅራኔዎቻችንን ለማቻቻል የሚያስችል ብሄራዊ መግባባት ባልፈጠርንበት ሁኔታ የምናካሂደው ምርጫ የበለጠ ጉዳት እንጂ ጥቅም ሊኖረው አይችልም፡፡
በዚህ አይነቱ ነባራዊ ሁኔታ ሆነን የምንካሂደው ምርጫ የለውጥ ሂደቱን የመጨረሻ ክሽፈት የሚያበስርና ወደ ቅድመ 2010 ሁኔታ የሚመልሰን እንጂ ከቶውንም ወደ መዋቅራዊ ዲሞክራሲ ሊያሸጋግረን አይችልም፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በምርጫ ወቅት የበለጠ ሊባባስና ሊወሳሰብ እንጂ ሊፈታ የሚችል ችግር የለም፡፡ ስለሆነም ከላይ ከፍ ሲል ለመግለፅ እንደሞከርነው የተሳካ የሽግግር ሂደት ማካሄድ እስከምንችል ድረስ መጭው ምርጫ ከአንድ እስከ ሁለት ዓመት ለሚደርስ ጊዜ መራዘም አለበት ብለን እናምናለን፡፡
ነገር ግን ገዢው ፓርቲ እንደተለመደው ከአገሪቱ ህልውና ይልቅ የራሱን ጊዜያዊና ቡድናዊ ጥቅም በማስቀደም ምርጫውን በቅርብ ጊዜ የሚያካሂድ ከሆነ ሂደቱን ለፅንፈኛና ብሄረተኛ ኃይሎች ለቆ መተው ተገቢ ነው ብለን አናምንም፡፡ ከዚህ እምነት በመነጨ ምርጫው የሚካሄድ ከሆነ ኢዴፓ በምርጫው ይወዳደራል፡፡ ከአሁን ቀደም እንደገለፅነው ፓርቲያችን ከሚገኝበት የአቅም ውስንነት አንፃር በምርጫው የሚኖረው ዋና ትኩረት አዲስ አበባን አሸንፎ በመረከብ ላይ ይሆናል፡፡ ይህ ውሳኔያችን አሁንም የተጠበቀ ቢሆንም ከዚህ ቀደም ይህንን ውሳኔያችንን ለህዝብ ይፋ ካደረግን በኋላ “ኢዴፓ በምርጫው የሚኖረው ሚና ለምን በአዲስ አበባ ብቻ ይወሰናል? ” የሚል ከፍተኛ ቅሬታና ግፊት በደጋፊዎቻችንና በህዝቡ ውስጥ እንዳለ ለመገንዘብ ችለናል፡፡ ይህንን የህዝብ ስሜት ግምት ውስጥ በማስገባት ኢዴፓ በአንድ በኩል በከፍተኛ ፍጥነት ድርጅታዊ ጥንካሬውን ለማጐልበት በመሞከር፣ በሌላ በኩል ደግሞ ከሌሎች ተቀራራቢ አቋም ካላቸው ፓርቲዎች ጋር ትርጉም ያለው ትብብር በመፍጠር በሚመጣው ምርጫ በአገር ደረጃ አሸናፊ ለመሆን የሚያስችለውን ጥረት ሁሉ ለማድረግ ወስኗል፡፡ ይህ አገራዊ አላማ ያለ ህዝብ ሁለንተናዊ ድጋፍና ተሳትፎ ሊሳካ አይችልምና አገራዊ ህልውናችን ተጠብቆ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ዜጐች ሁሉ የፓርቲ አባላት በመሆን፣ የሃሳብና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ ከጐናችን እንዲቆሙ ጥሪያችንን በአክብሮት እናቀርባለን፡፡
ሰላምና ህብረ-ብሄራዊነት አላማችን ነው!!
የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት

ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት በኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጠይቁ

የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን 3 አባላት በጋራ ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ፡፡ በደብዳቤያቸው በኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት ላይ የተጣለው እገዳ እንዲነሳ ጠይቀዋል፡፡ ሙሉ ደብዳቤያቸውን ከዚህ በታች አቅርቤዋለው፡፡
ቀን- 19/09/2011 ዓ.ም

ቀን- 19/09/2011 ዓ.ም
ለክብርት ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፤- ላለፉት አንድ ዓመታት የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት ላይ ተጥሎ የቆየው እገዳ እንዲነሳ ስለመጠየቅ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ መሰረት ተጠሪነታቸው ለጠቅላላ ጉባዔ በሆነ ሶስት አባላት የሚቋቋም ነው፡፡

እኛም ስማችን ከታች የተዘረዘረውና በጠቅላላ ጉባዔ ተመርጠን እና በቦርዱም ህጋዊ እውቅና ተሰጥቶን ያለን 3 አባላት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ መሰረት የፓርቲውን የብሔራዊ ምክር ቤት እንቅስቃሴ በመከታተልና በመቆጣጠር ለጠቅላላ ጉባዔው ሪፖርት የማድረግ ሃላፊነት ተሰጥቶናል፡፡ በዚህ መሰረት በፓርቲያችን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረውን ችግርና የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት በፓርቲው ውስጥ የነበሩ የመርህ ጥሰት የፈጠሩ አመራሮችን ችግር ለመፍታት የሄደበትን ርቀት ሁሉ በቅርበት ተከታትለናል፡፡

በመጨረሻም የፓርቲውን ህገ-ደንብ ተከትሎ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ፍጹም የሆነ ህጋዊ ውሳኔ ወስኖ እነዚህ የመርህ ጥሰት የፈፀሙ አመራሮቹን ከሃላፊነት አንስቶ በሌላ ተክቷል፡፡ እኛም በቦታው በመገኘት የተወሰነው ውሳኔ የፓርቲውን ህገ-ደንብ ተከትሎ መከናወኑን አረጋግጠን ለምርጫ ቦርድ በደብዳቤ አሳውቀናል፡፡ ሆኖም በጊዜው የነበረው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በተለይም አንድ ግለሰብ ቦርዱ ከተሰጠው ስልጣንና ሃላፊነት ውጭ የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት የወስናቸውን ውሳኔዎች እኛም በአካል ተገኝተን ያረጋገጥነውን ውሳኔ በፍፁም እንደማይቀበል ገለፀ፡፡

ይባስ ብሎ የብሔራዊ ምክር ቤቱን ስብሰባ ዶ/ር ጫኔ ካልጠሩት በስተቀር ብሔራዊ ምክር ቤቱ የሚወስናቸውን ማናቸውም ውሳኔዎች እንደማይቀበል በመግለፅ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ላይ እገዳ ጣለ፡፡ ከጠቅላላ ጉባዔው ቀጥሎ የፓርቲያችን ከፍተኛው የስልጣን አካል የሆነው የብሔራዊ ምክር ቤት በዚህ እገዳ ውስጥ ሆኖ የፖለቲካ ስራ መስራት ስለማይችል ሃምሌ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፓርቲው የውስጥ ጉዳይ ገብቶ ኢዴፓን እንዳፈረሰው ለመንግስት እና ለህዝብ ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ከዚህ መግለጫ በኋላ የመንግስት አካላት በተለይ ዶ/ር አብይ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተረድተው ጉዳችን ተጣርቶ ውሳኔ እንዲሰጠን ከእርስዎ በፊት ለነበሩት የቦርዱ ሰብሳቢ መመሪያ በመስጠት ጉዳያችን እንደገና እየታየ ነበር፡፡ እርስዎም ከመጡ በኋላ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት እየተከታተሉ እንደሆነ እና የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ግን የቦርዱን መቋቋም እየጠበቁ መሆኑን ገልፀው የፓርቲያችን አመራሮች ቀጠሮ ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

ነገር ግን ይሄ ሁኔታ እልባት ሳያገኝ ፓርቲው እንደከሰመ እና ከኢዜማ ጋር እንደተዋሃደ ተደርጎ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን እየተገለፀ ነው፡፡ አንደኛ- ከሃምሌ ወር 2010 ዓ.ም ጀምሮ የፓርቲው ብሄራዊ ም/ቤት ተሰብስቦ ውሳኔ ወስኖ እንደማያውቅ፡፡ ሁለተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 10 በዝርዝር በተሰጠን ስልጣን መሰረት የኦዲት እና ኢንስፔክሽን አበላት ባልተገኘንበት እና ባልታዘብንበት፣ ለጉባኤው የሂሳብ እና የስራ ኦዲት ሪፖርት ባላደረግንበት፣ የጠቅላላ ጉባኤ አባላቱ የኢዴፓ አባላት ይሁኑ አይሁኑ ባላረጋገጥንበት ሁኔታ ተደረገ የተባለው ጠቅላላ ጉባኤ ህገ-ወጥ ነው፡፡ ሶስተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 9.4.2 መሰረት የብሔራዊ ምክር ቤቱ የጠቅላላ ጉባዔውን መደበኛ፣ ልዩና አስቸኳይ ስብሰባዎችን ይጠራል ቢልም የብሔራዊ ምክር ቤቱ ያልጠራው ጠቅላላ ጉባኤ በመሆኑ ፍፁም ህገ-ወጥ ነው፡፡ አራተኛ- በፓርቲያችን መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 9.4.13 መሰረት ብሔራዊ ምክር ቤቱ ከመሰልና አቻ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ሊኖር ስለሚገባ ማናቸውም የትግል ግንኙነት ላይ መመሪያ እና ውሳኔ ይሰጣል ቢልም ግንኙነቱም ሆነ የውህደቱ ውሳኔ በጥቂት ግለሰቦች ፈቃደኝነት ብቻ የተፈጸመ ድርጊት በመሆኑ ፍጹም ተቀባይነት የለውም፡፡ ስለሆነም ክቡርነትዎ ፓርቲያችን ኢዴፓ አደረገ የተባለው እና በጠቅላላ ጉባዔው ተወሰነ የሚባለው ውሳኔ ሁሉ ፍፁም የፓርቲያችንን ህገ-ደንብ ያልተከተለ እና ህገ-ወጥ በመሆኑ የፓርቲያችንን ደንብ በመመርመር አስቸኳይ መፍትሄ እንድትሰጡንና ህጋዊው የኢዴፓ ብሔራዊ ምክር ቤት የተጣለበት እገዳ እንዲነሳ ስንል ከታች ስማችን የተዘረዘረው የኢዴፓ ኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ አባላት እንጠይቃለን፡፡
ከሰላምታ ጋር!


የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት
1ኛ- አቶ የኔመንግስት ጌታቸው-
2ኛ- አቶ ተስፋ መስፍን –
3ኛ- አቶ ሰለሞን ሰንደቁ-
ግልባጭ፤- ለመገናኛ ብዙሃን

ናሁ ቲቪ – ነጻ ውይይት ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር

ናሁ ቲቪ – ነጻ ውይይት ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር

Part 2

Part 3