Clicky

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ፍትሀዊ በሕብረተሰቡም ዘንድ ተአማኒ አልነበረም !!

ከኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ተገንብቶ ነጻና ዴሞክራሲዊ ምርጫ በሃገራችን ተካሂዶ ህዝቡ ከተለያዩ አማራጮች ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ስልጣን በውክልና የሚሰጥበት ስርአት እውን እንዲሆን በጽናት ሲታገል ቆይቷል፡፡ ይህ የምርጫ ስርአት ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ሁኔታ እውን እንዲሆን በየምርጫዎቹ በመሳተፍ የሚገጥሙ እንቅፋቶችንና ችግሮችን በመቃወምና እንዲታረሙም ትግል በማድረግ የበኩሉን አስተዋፆኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከዚህ እምነቱም በመነሳት በ2007ቱ አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በቂ ዝግጅት አድርጎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ምርጫው በመግባት ለሰለጠነ የምርጫ ስርአት እውን መሆን ያለውን ፍላጎት እንደ ከዚህ ቀደሙ በተግባር አረጋግጧል፡፡

በምርጫውም ውስጥ በነበረው ተሳትፎ በምርጫው ሂደት ላይ በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ የነበሩ እንቅፋቶችና ችግሮች በምርጫው ፍትሃዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን በማሳሰብና ድርጊቱንም በመቃወም በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠታችን ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም ምርጫ ቦርድ፣ ገዥው ፓርቲና የመገናኛ ብዙሃን ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋፆኦ እንዲወጡም ተደጋጋሚ ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል፡፡

ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ። (PDF)

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ

EDP_Manifesto_Coverየኢዴፓ ሦስተኛ አማራጭነት

ኢዴፓ የራሱን ጨምሮ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ ድክመቶችንና ጥንካሬዎችን አንጥሮ በመተንተን፣ ድክመቶችን በግልፅ በመቀበልና በማመን፣ የተቃዋሚው ጐራ በኢትዮጵያ አስተማማኝ የለውጥ አማራጭ እንዲሆን የሚያግዙ ሂሣዊ አቋሞችን ያራምዳል፡፡ ኢዴፓ ይህን የማድረግ አስፈላጊነትን ያረጋገጠው በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ የተለያዩ የፖለቲካ ኃይሎችን ፖለቲካዊ ባሕርይ በመተንተንና ከብዙዎቹም ጋር አብሮ በመሥራት በኢትዮጵያ የተሻለ ዴሞክራሲያዊ ስርዓትን ለማምጣት ያላቸውን ውስንነት በማየት ነው፡፡ በኢዴፓ እምነት ኢህአዴግን መቃወም ብቻውን ዴሞክራሲያዊ መሆንን ወይም ከኢህአዴግ የተሻለ መሆንን አያረጋግጥም፡፡ ኢዴፓ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ያሉ በርካታ ችግሮችን በመተንተን ከሌሎች በተለየ ሁኔታ የሱ የትግል ስልት ዋነኛ መለያ ስልት ዴሞክራሲያዊ መሆን እንዳለበት ወስኗል፡፡ የኢዴፓ የትግል ስልቶች በባህሪያቸው ከጭፍን ጥላቻ እና ኢ-ምክንያታዊነት የራቁ በመሆናቸው ኢዴፓ እራሱን በተቃውሞ ትግሉ ውስጥ ካሉ ብዙ ኃይሎች የተለየ አማራጭ አድርጐ ለማቅረብ መርጧል፡፡ ኢዴፓ የኢህአዴግንም ማንአለብኝነትና ጭፍንነት ይቃወማል፣ ይታገላልም፡፡ ኢህአዴግ በአገራችን የዴሞክራሲ ስርአት መገንባት ያቃተው መሆኑንም ኢዴፓ በሚገባ ይረዳል፡፡

በመሆኑም ራሱን ከሁለቱ ኃይሎች የተለየ ሦስተኛ የለውጥ ትግል አማራጭ አድርጐ ለሕብረተሰቡ ያቀርባል፡፡ ሦስተኛ አማራጭነት የለውጥ ፍልስፍና ሳይሆን የትግል ስልትና የአሠራር ፍልስፍና ነው፡፡ መለያ ባሕሪዎቹም በምክንያታዊነት እውነተኛነት መቻቻልንና መከባበርን በማስቀደም መወያየትና መደራደር ናቸው፡፡ በሦስተኛ አማራጭ ስልታችን አስተሳሰብ መሠረት የተቃውሞ ትግሉ በጥላቻ ሳይሆን በአማራጭ አስተሳሰቦች ላይ በማተኮር በአንድ በኩል በኢህአዴግ ላይ የአስተሳሰብ የበላይነት እያገኘ በሌላ በኩል የተሣትፎ ፖለቲካን በማስቀደም በልዩነት ስር በአንድነት ለጋራ የአገር ጥቅም መሥራት ተገቢ ነው፡፡ ኢዴፓ ኢህአዴግን በፅኑ የሚቃወመውን ያህል አብሮ በመሥራትና በመደራደር ሂደት በብሄራዊ ፖለቲካችን ውስጥ በሁለት ፅንፎች የተወጠረውን የአክራሪነት ዝንባሌ በማለዘብ አጠቃላይ ወደ ሆነ አገራዊ መግባባት ላይ እንድንደርስ ተስፋ ያደርጋል፡፡ ይህ በተቃውሞ ጐራ ውስጥ ገና አጠቃላይ ተቀባይነት ያገኘ ባለመሆኑ በኢዴፓና በሌሎች ተቃዋሚዎች መካከል የልዩነት ምንጭ ሆኖ ይገኛል፡፡

በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ የኢዴፓ አቋም

ኢዴፓ በአለፉት ዓመታት የኢህአዴግ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲዎችን ሃገራዊ ፋይዳ እየመዘነ በጥብቅ ሲተች ብቻ ሳይሆን የተሻሉ ያላቸውን የፖሊሲ አማራጮችን ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ኢዴፓ ኢህአዴግ አጋኖ የሚያቀርበው የኢኮኖሚ እድገት እጅግ መሠረታዊ ችግሮች ያሉበት መሆኑን በመግለፅ ሲተች ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ወቅት ለሕዝባችን እጅግ ፈተና ሆነው ከሚገኙ ችግሮች መካከል ዋነኛው የዋጋ መናር ነው፡፡ የዋጋ መናር የፈጠረው የኑሮ ውድነት ከኢህአዴግ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲና አመራር ድክመት የሚመነጭ ሲሆን ኢህአዴግ ይህን ለማስወገድ ተደጋጋሚ ጥረቶች ቢያደርግም የወሰዳቸው እርምጃዎች የፖሊሲውን ስህተት ያላረሙ በመሆናቸው ችግሩን የሚያባብሱ እንጂ የሚያቃልሉ አልሆኑም፡፡

በፖለቲካው መስክ ኢህአዴግ አገሪቱን በብቸኝነት ለመግዛት ያለውን አላማ ለማሳካት ሲል የአንድ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ዋነኛ መገለጫ የሆነውን የመድብለ ፓርቲ ስርዓት በአገራችን እንዳይፈጠር አፍኖ ይገኛል፡፡ በሱ የበላይነትና ብቸኛ ቁጥጥር ላይ የመሠረተው የፖለቲካ ስርዓት ለስሙ ዴሞክራሲያዊ ነው ቢባልም በሃገሪቱ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል ሊኖር በሚገባው ስምምነት፣ ትብብርና ተሳትፎ ላይ የተመሠረተ ሊሆን አልቻለም፡፡

ኢህአዴግ የገዢ ፓርቲነቱን ሚና ከመንግሥትነት በላይ በማድረግ የአገሪቱን መንግሥታዊ መዋቅሮችና የሕዝብ ተቋማትን ጭምር የፓርቲው መዋቅር አድርጐ በመጠቀም ዜጐች ሁሉ ለኢህአዴግ የስልጣን አላማና ፍላጐት ብቻ እንዲገዙ እያስገደደ ይገኛል፡፡ የልማትና እድገት አጀንዳዎች ሁሉ በዜጐች ላይ የፓርቲ ስልጣኑን መጫኛ መሳሪያ ሊሆኑ በሚችሉበት መንገድ ብቻ ሥራ ላይ ያውላቸዋል፡፡ ዜጐችን ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ በራሱ ፖለቲካዊ ተፅዕኖ ሥር እንዲወድቁ በማስገደድ በሕገ- መንግስቱ የተረጋገጡላቸውን ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶቻቸውን በሚጥስ መልኩ ከፍላጐታቸው ውጪ የራሱ የፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ በአገሪቱ አሉ የሚባሉ ዴሞክራሲያዊ ተቋሞች ሁሉ የኢህአዴግ ሥልጣን መጠቀሚያና መጠበቂያ ብቻ እንዲሆኑ በማድረጉ ተቋማቱ በገለልተኝነት እንዳይሰሩና አላማቸውን ለማሳካት የሚያስችል ነፃነት ብቻ ሳይሆን አቅምም እንዳይኖራቸው አድርጓል፡፡

የሕግ የበላይነት፣ ግልፅነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የመንግሥት አሠራር ባለመኖሩ በስልጣን መባለግ፣ የመልካም አስተዳደር እጦት ዛሬም የአገራችን ዋነኛ የፖለቲካ ችግሮች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በእለት ተእለት የመንግሥት እንቅስቃሴ ውስጥ የሕዝቡን መብትና ጥቅም የማያከብር መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በብቸኝነት የተቆጣጠረውን ፓርላማ እንዳሻው በመጠቀም በሕገ መንግሥቱ የተደነገጉ የሕዝብ መብቶችንና ነፃነቶችን መሠረት ያደረጉ ድንጋጌዎች በማን አለብኝነት በመጣስ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ የራሱን ሥልጣን ለማጠናከር ዋነኛ አላማ ያደረጉ አዋጆችን እያፀደቀ መተግበርን ሥራዬ ብሎ ተያይዞታል፡፡

መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅና የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጐች የዚህ ዋነኛ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ኢዴፓ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ለመቆጣጠር የወጣው አዋጅ ካገር ጥቅም ይልቅ የኢህአዴግን የሥልጣን የበላይነት ለማረጋገጥና ለማስቀጠል ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠንቅቆ ያውቃል፡፡ የፀረ-ሽብርተኝነት ሕጉም ቢሆን ከሌሎች የዳበረ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ካላቸው አገሮች ተቀዳሚ ነው ቢባልም በአገራችን የዜጐች መብትና ነፃነትን የሚጠብቁ የዳበሩ ተቋማት ባለመኖራቸው መንግሥት ሕጉን ሽብርተኛ ያልሆኑትን ዜጐችን ጭምር ማጥቂያ ለማድረግ አለማሰቡን በአግባቡ ለመረዳት በሚያስቸግር ሁኔታ ተግባራዊ እየሆነ በመሆኑ በዜጐች ላይ አላስፈላጊ የሆነ ፍርሃትንና ስጋትን የሚፈጥር ሆኗል፡፡

የጥላቻ ፖለቲካን እንጠየፋለን!

ኢዴፓ የዛሬውና የወደፊቱ ትውልድ ፓርቲ ነው!

የምርጫ ምልክታችን አበባ ነው!

ኢዴፓን ምረጡ አበባን ምረጡ!

የፓርቲው የአዲስ አበባ አድራሻ

ቁጥር 1 ጊዮን መድሃኒት ቤት አጠገብ፤ ቁጥር 2 በቅሎ ቤት ሃዊ ሆቴል ፊት ለፊት

ስልክ ቁጥር 0115-508727/28 ወይንም ደግሞ 0114-655765 የፖስታ ሣጥን ቁጥር 101458
ምንጭ – አዲስ ዘመን

የኢዴፓ የ2007 ዓ.ም የምርጫ መወዳደሪያ ማንፌስቶ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የ2007 ዓ.ም የምርጫ መወዳደሪያ ማንፌስቶ

EDP_Manifesto_Cover

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክ ጉባኤ ተሳትፈው ተመለሱ

Photo ALN

Photo ALN

የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ጫኔ ከበደ በሞሮኮ በተካሔደው የ11ኛው የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክ ጠቅላላ ጉባኤ ተሳትፈው ተመለሱ፡፡ ከህዳር 18 – 202007 .. በተካሄደው ጉባኤ ከ90 የሚበልጡ ተሳታፊዎች በጉባኤው ተስተናግደዋል፡፡

በጠቅላላው ጉባዔው የቀጣዩን 2 አመታት ስራ አስፈጻሚ የተመረጡ ሲሆን ኦሊቨር ካሚታቱ በድጋሚ ለሁለት አመታት የአፍሪካ ሊበራል ኔትወርክን እንዲያገለግሉ ተመርጠዋል፡፡ በኔትወርኩ ታሪክ ውስጥ ለመጀመርያ ጊዜ ሴት ስራ አስፈጻሚ መካተቱ ይህንን ጉባኤ ታሪካዊ እንዲሆን አድርጎታል፡፡

በተጨማሪም ከ44 በላይ ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ መሳተፋቸው ጉባኤውን ታሪካዊ ከሚያደርጉት ክስተቶች መካከል አንዱ ነው፡፡ ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ተሳታፊ ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ ሲገኙ ይህ የመጀመርያው ነው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ኔትወርኩ ለመጀመርያ ጊዜ በሊበራል ዲሞክራሲ እይታ የተቃኘ የአፍሪካ ሰብአዊ መብት አያያዝን በተመለከተ የራሱን ሰነድ ያረቀቀ ሲሆን፤ ሰነዱም በዋናነት የሴት ልጅ ግርዛት፤ የህጻናት ጉልበት ብዝበዛ እና የፖለቲካ ነጻነት ላይ በትኩረት ይተነትናል፡፡

/ር ጫኔ ከበደ በዚህ ስብሰባ ላይ ኢዴፓን ወክለው የኢዴፓን ሀሳብ እና አመለካከት ለጉባኤው ተሳታፊዎች በማካፈል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡

ኢዴፓ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ እንደማይቆርጥ አስታወቀ

ኢዴፓ ለግንቦት አገር አቀፍ ምርጫ ዝግጅት ማድረግ የጀመረው ካለፈው አመት ጀምሮ ቢሆንም ነገር ግን የዝግጅቱ ዋናው አካል የሆነው በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ሊያካሂዳቸው ያሰባቸው ህዝባዊ  ስብሰባዎች በተለያዩ የመንግስት ቢሮክራሲ ችግሮች ምክንያት እንደተሰናከሉበት ይታወቃል፡፡ የባለፈው ወር የባህር ዳር ስብሰባ እና የባለፈው አመት የሐምሌ ወር የአዲስ አበባው ህዝባዊ ስብሰባዎች ለዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየባሱ መምጣታቸው የሰላማዊ ትግሉን በእጅጉ የሚያዳክሙ እርምጃዎች ቢሆኑም ኢዴፓ አሁንም ከሰላማዊ ትግል መርሁን እንደማይለቅ እና የአገሪቷ ብቸኛ ዘላቂ መፍትሔ መሆኑን እንደሚያምን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ባልከው ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሰረት ፓርቲው ባለፈው ወር ጥቅምት 22 ቀን በባህርዳር የተሰናከለበትን ስብሰባ በድጋሚ ቅዳሜ ህዳር 27 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በከተማው በሚገኘው ሙሉአለም አዳራሽ እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡

በመቀጠልም እሁድ ታህሳስ 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ከጠዋቱ 3፡00 ጀምሮ በመቀሌ ከተማ ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ የመቀሌውን ስብሰባ እንደሚያደርግ ፓርቲው አስታውቋል፡፡

በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከሚነሱ ዋና ዋና አጀንዳዎች መካከል በግንቦት ወር የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት ላይ ሰለሚኖረው ፋይዳ ፤ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ እየተባባሰ የመጣው የአገራችን የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መዳከም፤ እንዲሁም እያደገ በሚገኘው የአገራችን ኢኮኖሚ ዙርያ የሚታዩት ከኑሮ ውድነት፣ ከሙስና፣ ከመዋቅራዊ ሽግግርና ከነፃ የገበያ ኢኮኖሚ መዳከም ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች ይገኙበታል፡፡ ኢዴፓ በመቀጠልም ህዝባዊ ስብሰባዎቹ በሌሎች ከተሞችም እንደሚካሄዱ አስታወቋል፡፡

ፓርቲው እንደቀደሙት ህዝባዊ ስብሳባዎች አሁንም እነዚህ ስብሰባዎች እንደማይሰናከሉበት ምን ዋስትና አለው? ብለን የጠየቅናቸው የድርጅት ጉዳይ ሀላፊው አቶ ኤርሚያስ ባልከው በእነዚህ ስብሰባዎች ፓርቲው ለከተሞቹ ማዘጋጃ ቤቶች እውቅና ደብዳቤ በማስገባት ብቻ ሳይወሰን ገፍቶ በመሄድ የእውቅና ደብዳቤ ከጽህፈት ቤቶች ማግኘት መቻሉን ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን የእነዚህ ደብዳቤዎች መያዝ ብቻ ስብሰባው እንደማይስተጓጎል ዋስትና ሊሆን እንደማይችል ገልጸው ማናቸውም አስቸጋሪ መሰናክሎች ቢኖሩም ኢዴፓ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ እንደማይቆርጥ ገልጸዋል፡፡ እንዲሁም ኢዴፓ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ ለስብሰባዎቹ መሳካት የበለጠ እንደሚጥር ገልጸው የለውጡ ባለቤት የሆነው ህዝቡም ከኢዴፓ ጋር በመሆን ሰላማዊ ትግሉን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ኢዴፓ በዛሬው እለት አቅዶት የነበረው የባህር ዳር ህዝባዊ ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ ተሰናከለ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በዛሬው እለት አቅዶት የነበረው ህዝባዊ ስብሰባ ለሁለተኛ ጊዜ መሰናከሉን የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ባልከው ገለጹ፡፡

ስብሰባው የተሰናከለበት ምክንያት የአማራ ክልል የባህርዳር ከተማ አስተዳደር ህዝባዊ ስብሰባ ማሳወቂያ ክፍል ህዝባዊ ስብሰባውን ለማካሔድ የሚያስችለውን የእውቅና ደብዳቤ ለመስጠት ባለመቻሉ እንደሆነ አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡

ሕዝባዊ ስብሰባውን ለማካሄድ ከታቀደ ጊዜ ጀምሮ ፓርቲው በተደጋጋሚ የእውቅና ደብዳቤ እንዲሰጠው ሲጠባበቅ የቆየ ቢሆንም እስከዛሬው የህዝባዊ ስብሰባው እለት ድረስ ደብዳቤው ሊሰጠው እንዳልተቻለ ታውቋል፡፡ በዚህም የተነሳ ህዝባዊ ስብሰባውን በአስገዳጅ ሁኔታ ለማካሄድ አለመቻሉን ገልጾ ፓርቲው ለደረሰበት ከፍተኛ ኪሳራ የሚመለከታቸውን የመንግስት አካላት ሀላፊነቱን እንደሚወስዱ አቶ ኤርሚያስ ገልጸዋል፡፡

ኢዴፓ የሚከተለው ሶስተኛ አማራጭ በሰላማዊ እና በህጋዊ መንገድ የተከተለ ቢሆንም ከመንግስት በኩል ግን የአገሪቷን የዴሞክራሲ እና ሰላማዊ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያዳክሙ እርምጃዎችን እየወሰደ እንደሚገኝ አቶ ኤርሚያስ አክለው ገልጸዋል፡፡ከሶስት ወር በፊት የፓርቲው አባላት በአዲስ አበባ ለህዝባዊ ስብሰባ በቅስቀሳ ላይ እንዳሉ ይህንን “የቅስቀሳ እውቅና ደብዳቤ አልያዛችሁም” በሚል ለሁለት ቀናት ታስረው እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

የሕዝባዊ ስብሰባ ጥሪ ለምክንያታዊ ፖለቲካ ደጋፊዎች በሙሉ !

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ግልፅና ዝርዝር አማራጭ ፕሮግራም ያለው ፣በጥላቻና በኩርፊያ ሳይሆን በመቻቻልና አብሮ በመስራት የፖለቲካ መርህ የሚመራ፣ ከሌሎችም ሆነ ከራሱ ጥፋትና ስሕተት የመማር ድፍረት ያለው፣ በተጨባጭና አሣማኝ ምክንያት የሚደግፍና የሚቃወም፣ ከይሉኝታና ከእወደድባይነት የፖለቲካ አመለካከት ራሱን ያፀዳ፣ ከትናንት በላይ ስለዛሬዋና ስለወደፊቷ ኢትዮጵያ የበለጠ የሚጨነቅና ሃላፊነት የሚሰማው የ21ኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ ፓርቲ ነው፡፡

ኢዴፓ በአገሪቱ ካሉ ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች መካከል

1ኛ – በዚህ ዓመት የሚካሄደው አገራዊ ምርጫ በአገራችን አጠቃላይ የፖለቲካ ሂደት ላይ ሰለሚኖረው ፋይዳ ፤

2ኛ – ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ከመምጣት ይልቅ እየተባባሰ የመጣው የአገራችን የሰብአዊ መብት አያያዝ ችግርና የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ሂደት መዳከም፤

3ኛ – እያደገ በሚገኘው የአገራችን ኢኮኖሚ ዙርያ የሚታዩት ከኑሮ ውድነት፣ ከሙስና፣ ከመዋቅራዊ ሽግግርና ከነፃ የገበያ ኢኮኖሚ መዳከም ጋር የተያያዙ መሰረታዊ ርዕሰ ጉዳዮች

ላይ ጥልቅ ሕዝባዊ ውይይት ከባህርዳር ከተማ እና አካባቢ ነዋሪዎች ጋር ይካሄድባቸዋል፡፡

እርስዎ በዚህ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ከላይ በተጠቀሱት ወቅታዊ አገራዊ ጉዳዩች ላይ አንዲወያዩ፣ በተጨማሪም ሌሎች ተዛማጅ ጥያቄዎችን አንስተው ተገቢ ምላሽ እንዲያገኙ፣ ስብሰባውን ባዘጋጀው ፓርቲ ላይም የድጋፍም ሆነ የተቃውሞ አስተያየት በነፃነት እንዲሰጡና ለፓርቲው የወደፊት አካሄድ ይጠቅማል ብለው የሚያምኑበትን ምክር አንዲለግሱ በአክብሮት ተጋብዘዋል፡፡

የስብሰባው ቦታ፡- ባህርዳር ሙሉአለም የመሰብሰቢያ አዳራሽ

የስብሰባው ቀን እና ሰዓት፡- ቅዳሜ ጥቅምት 22 ከቀኑ 3፡00 ጀምሮ

ኢዴፓ የዛሬውና የወደፊቱ ትውልድ ፓርቲ!!!

ለበለጠ መረጃ በ 011 550 87 27/28 ወይም 0913333150 ይደውሉ፡፡

ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ የተሰጠ የመልካም ምኞት መግለጫ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ መጭው ዘመን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት የሚጠናከርበት፣ የጥላቻና የኩርፊያ ፖለቲካ ታሪክ የሚሆንበት፣ የመቻቻልና የመከባበር ፖለቲካ የሚጎለብትበት፣ የጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ በአማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ የሚተካበት፣ ምክንያታዊ ፖለቲካ የሚያብብበት፣ በመጭው 2007 ምርጫ ህዝቡ በተሳትፎው የሰለጠነና የበቃ ህዝብ መሆኑን ዳግም የሚያረጋግጥበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መልክ የበለጠ የሚሰፋበት እንዲሆን በመመኘት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በግምባር ለተሰማራችሁ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በማረሚያ ቤት ለምትገኙ ወገኖቻችን፣ እንዲሁም በስደት ከሀገር ውጭ ላላችሁ ወንድሞችና እህቶች በአጠቃላይም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መጭው ዘመን የሰላም፣ የጤናና የፍቅር እንዲሆንላችሁ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ስራ አስፈጻሚ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ

የኢዴፓ ብሄራዊ ምክር ቤት 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሄደ

Ethiopian Democratic Party and Ethiopian Electionኢዴፓ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን 20 የብሄራዊ ምክር ቤት አባላት በተገኙበት አካሂዷል፡፡ ብሄራዊ ምክር ቤቱ በዚህ መደበኛ ስብሰባው ላይ በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ በማሣለፍና ለስራ አስፈጻሚው አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ለሙሉ ቀን የተካሄደውም ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁንም በተጨማሪ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ብሄራዊ ም/ቤቱ ከስራ አስፈጻሚው በቀረቡ አጀንዳዎች ጥልቅ ውይይት አካሂዷል፡፡ ም/ቤቱ ለመወያያ የቀረቡለትን አጀንዳዎች ማለትም የስራ አስፈጻሚ የ4 ወር የስራ ሪፖርትና  የ2007 ዓ.ም ምርጫን አስመልክቶ ፓርቲው ሊከተለው የሚገባውን ተሳትፎ በተመለከተ ባደረገው ስብሰባ ውሳኔዎችንና አቅጣጫዎችን አመላክቷል፡፡

ም/ቤቱ የስራ አስፈፃሚውን ሪፖርት በመገምገም ጥንካሬና ድክመቱ ላይ አስተያየት ሰጥቶ እንዲብራሩ የሚፈልጋቸውን ጥያቄዎችም አቅርቦ ከፕሬዘዳንቱ ዶ/ር ጫኔ ከበደ ማብራሪያ የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪ የስራ አስፈጻሚ አባላትም በየዘርፉ ያከናወኑትን ተግባራት ለም/ቤቱ አስረድተዋል፡፡ በመጨረሻም ም/ቤቱ ሪፖርቱን በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ማፅደቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በመጨረሻም የ2007 ሀገር አቀፍ ምርጫን በተመለከተ በተደረገው ውይይት ም/ቤቱ በተቃዋሚ ፓርቲ፣ በገዢው ፓርቲ እና በህዝቡ ዘንድ ያለውን ዝግጁነትና በምርጫው ዙሪያ ስለሚኖራቸው ሚና ሀገር አቀፍ ውይይት ቢደረግ የተሻለ ነው በሚል ስራ አስፈፃሚው ይሄንን ሁሉን አሳታፊ የሆነ የውይይት መድረክ እንዲያዘጋጅ፣ ኃላፊነት ወስዶ እንዲንቀሳቀስና በምርጫው ዙሪያ መነቃቃት የሚፈጠርበትን ሁኔታ እንዲያመቻች አቅጣጫ አስቀምጧል ሲሉ  ስለ ስብሰባው ያነጋገርናቸው አቶ አዳነ ታደሠ የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ተናግረዋል፡፡

የኢዴፓ መልዕክት

ሰሞኑን  በአዲስ አበባ   መስተዋል የጀመረው የፍጆታ ሸቀጦች  የዋጋ ንረት በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች  የሚገኘውን  ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል አስደንግጧል፡፡  በመላው አገሪቱ ላለፋት 15 ወራት ተስተውሎ የነበረው የነጠላ አሃዝ የዋጋ ግሽበት በዚሁ  ይቀጥላል የሚለው እምነትም በህብረተሰቡ ዘንድ እጅጉን እየሳሳ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን ለታየው የዋጋ ንረት ዋነኛው መንስኤ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለው የዋጋ ግምት (inflation expectation) ሲሆን ለዚህ የዋጋ ግሽበት ጥርጣሬ መንስኤ ደግሞ በቅርቡ የተገለፀው የመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ እና የ2007 ዓ.ም የባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ  በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡

ኢዴፓ ይህ የደሞዝ ጭማሪ የዋጋ ግሽበቱን ከማናር ባለፈ ለደሞዝተኛው እና ለጡረተኛው የህብረተሰብ ክፍል ዘላቂ እና የተጨበጠ ጥቅም አያመጣም ብሎ ያምናል፡፡ መንግስት ከደሞዝ ጭማሪው በፊት ሲቪል ሰርቪሱ ውስጥ የሚገኘው ስር የሰደደ ብልሹ አሰራር፣ የምንቸገረኝነት ስሜት እንዲሁም  በየመስሪያ ቤቱ የሚታየው የመንግስት እና የፓርቲ ስራ መደበላለቅ ችግሮቹ በቅድሚያ መቀረፍ አለባቸው ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡ እነዚህ ችግሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሱ በመጡበት በአሁኑ ወቅት እንዲሁም የሲቪል ሰራተኛው አገልግሎት አሰጣጥና ምርታማነት ባልተሻሻለበት ሁኔታ የመንግስት ሰራተኛ የደሞዝ ስኬል መጨመሩ የዋጋ ግምቱን (inflation expectation) እንዲጨምር ያደርጋል፡፡ ይህ ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ ላይ ቀጥተኛ ተጽእኖ  ያሳድራል፡፡

ኢዴፓ ሸማቹን የህብረተሰብ ክፍል ማገዝ የሚቻለው የደሞዝ ወለሉን (minimum wage) በማሻሻል እንዲሁም በጊዜያዊነት የስቪል ሰራተኛው ከገንዘብ ጋር ያልተገናኙ ጥቅሞችን (non-monetary incentives) በመጠቀም ሲቪል ሰራተኛውን ከኑሮ ውድነት ችግር በማውጣት ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሌላው የዋጋ ግምትን (Inflation Expectation) ጥርጣሬ የሚፈጥሩ የ2007 ዓ.ም ባጀት ጉድለት የሚሞላበት መንገድ ነው፡፡ መንግስት ይህንን ጉድለት የሚሞላው በግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አና በአገር ውስጥ ብድር መሆኑ ለግሽበቱ ከፍተኛ ጥርጣሬን እያሳደረ ይገኛል፡፡ በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ የግምጃ ቤት ሰነድ ሽያጭ አላማ የገንዘብ ፖሊሲ መሳሪያ ሆኖ ማገልገል ሳይሆን የመንግስትን ባጀት ጉድለት መሙያ ሆኖ ማገልገሉ የማእከላዊ ባንኩን ነፃነትና ገለልተኝነት በጥያቄ ውስጥ የሚጥል በመሆኑ ለዋጋ ግምት መናር የራሱ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሂደት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ነፃ እና ገለልተኛ ያልሆነው ብሄራዊ ባንክ ባለበት ሁኔታ መንግስት በፈለገና በፈቀደ ጊዜ  ከባንኩ መበደር መቻሉ ለዋጋ ግሽበቱ ቀጥተኛ አስተዋፆ ያደርጋል! በመሆኑም ኢዴፓ እንዲህ አይነቱን የዋጋ ግሽበቱን መቆጣጠር የሚቻለው ባጀቱን ለተገቢው  አላማ እንደሚውል በማረጋገጥ እናም ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚወጡትን የመንግስት ብክነቶችን በማስወገድ ነው ብሎ ያምናል፡፡ አንዲሁም መንግስት  ብሄራዊ ባንክን ነፃነት እና ገለልተኝነት የሚያጠናክር እርምጃዎችን በመውሰድ ባንኩ በህብረተሰቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት በመጨመር ነው ብሎ ያምናል፡፡