Clicky

ሃቀኛ ትኩረት ለውጤታማ ድርድር ወሳኝ ነው!

በሃገራችን ለተከሰተው የፖለቲካ ቀውስ ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት በማሰብ በሃገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የቅድመ ድርድር ውይይት ከተጀመረ ከሁለት ወር በላይ ማስቆጠሩ ይታወሳል፡፡ በዚህ ግዜ ውስጥ የፖለቲካ ፓርቲዎች በድርድሩ የአካሄድ ስነ-ስርዓት ዙሪያ ለ7 ግዜ ተገናኝተን የተወያየን ቢሆንም በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ያለው ግንኙነት ወደ ተሻለ የመግባባትና የመቻቻል መንፈስ ከመሸጋገር ይልቅ እንደተለመደው ገና ከጅምሩ የመክሸፍ አደጋ እየታየበት ነው፡፡

በቅድሚያ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስብስብ የሆነው መድረክ ከአንድ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እታገላለሁ ከሚል የፖለቲካ ሃይል በማይጠበቅ መንገድ ̋ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለሁት ጠንካራና ሀቀኛ ተቃዋሚ እኔ ብቻ ስለሆንኩ ብቻዬን ከኢህአዴግ ጋር መደራደር አለብኝ ” በማለት የድርድሩን መድረክ ለቆ ወጥቷል፡፡ በመቀጠልም ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግ በተለመደው አንባገነናዊ ባህሪው ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲካሄድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበውን ጥያቄ ያለ አግባብ አልቀበልም በማለቱ 1 ተቃዋሚ ፓርቲ ፓርቲ ድርድሩን ለቆ መውጣቱን አስታውቋል፡፡

በኢዴፓ እምነት ለድርድሩ ሂደት መዳከም ምክንያት እየሆኑ ያሉት ከግትር አቋሙ መለዘብ ያልቻለው ገዥው ፓርቲ ኢህአዴግና ያለ አሳማኝ ምክንያት የድርድሩን ሂደት ጥለው እየወጡ ያሉት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ናቸው፡፡ ኢህአዴግ በሃገራችን እየተፈጠረ ያለው የፖለቲካ ውጥረትና ቀውስ በሃቀኛ የውይይትና የድርድር ሂደት መፍትሄ እስካላገኘ ድረስ የሃገሪቱም ሆነ የራሱም ህልውና በአደገኛ ጠርዝ ላይ መገኘት መቻላቸውን መገንዘብ ባለመቻሉ በአንባገነናዊ ባህሪው ቀጥሎበታል፡፡ በሃገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከሚታየው ከፍተኛ የቅራኔና ያለመተማመን እውነት አንጻር ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲካሄድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የቀረበው ጥያቄ ተገቢና ምክንያታዊ ቢሆንም ይሄንን ጥያቄ ኢህአዴግ ሊቀበለው አለመፈለጉ ዛሬም እንደትናንቱ ከአምባገነናዊ ባህሪው ያለመላቀቁ ዋና ማሳያ ነው፡፡

ኢዴፓ ድርድሩ በገለልተኛ አደራዳሪዎች እንዲመራ የቀረበውን ጥያቄ ሙሉ ለሙሉ የሚደግፈው ቢሆንም ይሄንን ጥያቄ ኢህአዴግ አልተቀበለም ብሎ አጠቃላይ የድርድሩን ሂደት አቋርጦ መውጣት ግን ተገቢ ነው ብሎ አያምንም፡፡ ኢዴፓ የድርድር ሂደት በሰጥቶ መቀበል መርኅ የሚመራ ከመሆኑም በላይ በሁሉም ነገርም አሸናፊ መሆን የማይጠበቅበት ሂደት መሆኑን ስለሚነዘብ ነው፡፡ በሌላም በኩል በአንድ የስነ-ስርዓት ጥያቄ ላይ ልዩነት ስለተፈጠረ ብቻ ሂደቱን ጥሎ መውጣት ተገቢ እርምጃም ነው ብሎ አያምንም፡፡

ኢዴፓ ሃገራችን በአሁኑ ወቅት ለምትገኝበት የፖለቲካ ቀውስ ብቸኛው መድህን ውይይትና ድርድር መሆኑን ከልቡ ስለሚያምን ከተዳራዳሪ ፓርቲዎች ጋር ያሉትን ልዩነቶች በልዩነት እያስመዘገበ በድርድሩ ሂደት መቀጠልን ይፈልጋል፡፡ የድርድሩን አጠቃላይ ሂደት ከገመገመ በኋላ የድርድሩን የመጨረሻ ውጤት የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ጋር አያይዞ በመጨረሻ የሚደርስበት ውሳኔ ይሆናል፡፡ ገዥው ፓርቲም ሆነ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ ዓይነት የድርጅትን ሳይሆን የሃገርንና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ መንፈስ ድርድሩን በሃላፊነት ስሜት ሊያካሂዱ ይገባል ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡

ከሁሉም በላይ የጉዳዩ ዋና ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ህዝብ በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የሚደረግ ድርድር የወደፊት ሰላሙንና ሃገራዊ ህልውናውን የሚወስን ቁም ነገር መሆኑን ተገንዝቦ ለድርድሩ ሂደት ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል፡፡ በተጨማሪም ተደራዳሪ ፓርቲዎች በሃገራዊ የሃላፊነት ስሜት እንዲደራደሩ የራሱን የማይተካ ግፊት እንዲያደርግ በዚህ አጋጣሚ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
መጋቢት 29 2009 ዓ.ም

ኢዴፓ የጋራ ም/ቤቱ አሰራር የማይስተካከል ከሆነ ከጋራ ምክር ቤቱ ሊወጣ እንደሚችል ለጋራ ም/ቤቱ በፃፈው ደብዳቤ አሳወቀ ።

Ethiopian Democratic Partyከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የአዲስ አበባ – ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን ተከትሎ ከተቀሰቀሰው ተቃውሞና በቅርቡ ደግሞ የወልቃይት – ጠገዴን ህዝብ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ እስከተፈጠረው ከፍተኛ ቀውስ ድረስ ጉዳዩችን እየተከታተለ መግለጫዎችን ሲሰጥ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በሰጣቸው መግለጫዎችም ፓርቲያችን በዚህ ግጭትና ተቃውሞ የሃገሪቱ ቀውስ ተባብሶ እንደ ሃገርም እንደ ህዝብም ተገቢ ያልሆነ ዋጋ ከመክፈላችን በፊት መንግስት፣ ህዝቡ፣ የመገናኛ ብዙሃንና የፖለቲካ ሃይሎች በተገቢው መንገድ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፏል፡፡ የችግሩን መንስዔዎችና መፍትሄዎችንም ለማመላከት ሞክሯል፡፡ ይሁን እንጂ ኢ.ዴ.ፓ በነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም እና ከዚያም በፊት የሰጣቸውን ጋዜጣዊ መግለጫዎች የተለያዩ የመንግስት ሚዲያዎች በተዛባ መንገድ ከማቅረብ አልተቆጠቡም፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የአገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም በነበረው አስቸኳይ ስብሰባ በሃገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይቷል፡፡ ነገር ግን ፓርቲያችን ውሳኔው የጋራ ምክር ቤቱን አዋጅና ደንብ የጣሰ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ምክር ቤቱ አካሂዱን እንዲያስተካክል ፓርቲያችን በተለያዩ ግዚያት ጥሪ አድርጓል፡፡ የሃገራችንን መፃዒ ዕድልና ለዲሞክራሲው ግንባታ የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት ባለን ፅኑ እምነት ረዥም ጉዞ በምክር ቤቱ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ብንጓዝም በውስጣዊ አሰራሩና በመንግሥት መገናኛ ብዙሃን የሚፈፀሙብን ጫናዎች ሊታረሙ አልቻሉም፡፡ ስለሆነም ፓርቲያችን የሚከተሉትን ውሳኔዎች አስተላልፏል፡፡

ኢዴፓ በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጠናከርና ዴሞክራሲ እንዲጐለብት የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ይሁን እንጂ በአባሎቻችን ላይ እስራት፣ ወከባና እንግልት እየተፈጸመባቸው ይገኛል፡፡ከነዚህም ውስጥ በሰሜን ወሎ፣ በደቡብ ወሎ ደሴና አካባቢው፣ በምስራቅ ጐጃም በደብረ ማርቆስና አካባቢው ያሉ አባሎቻችን በመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እየታሰሩና እየተዋከቡ ይገኛሉ፡፡ በአባሎቻችን ላይ የሚደርሰውን እስራት፣ እንግልትና ወከባ እናወግዛለን፡፡

ኢ.ዴ.ፓ ነሐሴ 6 ቀን 2008 ዓ.ም በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን መግለጫውን በመንግስት ቁጥጥር ስር ያሉት መገናኛ ብዙሃን ማለትም ኢ.ዜ.አ፣ ፋና፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣና የአማራ ብሄራዊ ክልል ቴሌቭዠን የመግለጫችንን ይዘት አዛብተው ያቀረቡ ሲሆን ኢ.ቢ.ሲ ጭራሽ ዜናውን አልሰራውም፡፡ ይህ የሚያሳየው የመንግስት ሚዲያዎች የተለየን ሃሳብ በአግባቡ ያለማስተናገድ አባዜ የተጠናወታቸውና የጋዜ ጠኝን ስነ-ምግባር የጐደላቸው መሆኑንን እየጠቆምን ድርጊቱን ፓርቲያችን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ የህብረተሰቡን መረጃ የማገኝት መብት እንዲያከብሩና አሰራራቸውንም ፈትሸው እንዲያስተካክሉ ኢ.ዴ.ፓ. ይጠይቃል፡፡

የአገር አቀፍ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 2008 ዓ.ም በጠራው አስቸካይ ስብሰባ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ተወያይቷል ፡፡ ነገር ግን ውሳኔ የተላለፈው የፖለቲካ ፓርቲዎችን ስነምግባር ለመደንገግ የወጣውን አዋጂ ቁጥር 662/2002ዓ.ም አንቀጽ 26 ንዑስ ቁጥር 11 እና የተሸሻለው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 13 (1) መሰረት የጋራ ምክር ቤቱ ማንኛውንም ውሳኔ በጋራ መግባባት ወይም በተባበረ ድምፅ ይወስናል የሚለውን አንቀፅ ሙሉ ለሙሉ በመጣስ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ የጋራ ምክር ቤቱ ባፀደቀው ደንብ መሰረት ውሳኔዎቹ መተላለፍ የሚገባቸው በስምምነት (consensus) መሆኑን ቢገልፅም ውሳኔው የተላለፈው አዋጁንና ደንቡን በሚጥስ ሁኔታ ነው፡፡ የህዝብን ጥያቄ የማቅረብ መብት በተመለከተና በተለያዩ የሃገራችን አካባቢዎች የተከሰቱ ህዝባዊ ሰልፎችን በተመለከተ በተደረገው ውይይት ኢ.ዴ.ፓ በብቸኝነት በልዩነት መውጣቱ እየታወቀ በሚዲያ የተገለፀበት መንገድ ግን ከስምምነት ውጪ በተዛባ መልኩ መሆኑን ፓርቲያችን ተገንዝቧል፡፡ ስለሆነም የጋራ ምክር ቤቱ ህግን የሚጥስ ተግባሩን እሰከ ሦስት ወር ጊዜ ውስጥ የማያስተካክል ከሆነ ኢ.ዴ.ፓ ከጋራ ምክር ቤቱ ሊለቅ እንደሚችል ከወዲሁ ያሳውቃል፡፡

የኢ.ዴ.ፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ነሐሴ 12 ቀን 2008 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ሃገራችን ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ እንዳትገባ መከላከል የሁሉም ሃላፊነት ነው!

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ባለፉት ወራት የአዲስ አበባ እና ኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላን አቅዱን ተከትሎ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ ዙሪያና በአማራ ክልላዊ መንግስት ከቅማንት ህዝብ የማንነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ በጎንደር የተቀሰቀሰውን ግጭት አስመልክቶ ሁለት ተከታታይ መግለጫዎችን ማውጣቱ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም ይሄ ታቃውሞና ግጭት ከመቆምና ከመብረድ ይልቅ በተለይ በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች ተባብሶ እንደቀጠለ ነው፡፡ በተጨማሪም በጋምቤላ ግጭቶች የተከሰቱ ሲሆን የወልቃይት ጸገዴ ህዝብ የማንነት ጥያቄን ተከትሎ የተፈጠረው ችግርም በአግባቡ ሳይፈታ ተባብሶ የቀጠለበት ሁኔታ መኖሩን ከተለያዩ አቅጣጫዎች የሚደርሱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ኢዴፓ ባለፉት ሁለት መግለጫዎቹ ላይ ግጭቶችን ለማብረድ ተገቢና ዘላቂ የመፍትሄ እርምጃ መንግስት መውሰድ እንዳለበት አሳስቦ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ ነገር ግን መንግስት ለችግሩ ዘላቂና አስተማማኝ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ እለታዊ ግጭቶችን በማብረድ ላይ ያተኮረ እርምጃ መውሰድን ስለመረጠ በተለይም በኦሮሚያ ክልል ግጭቱ ተባብሶ የሰው ህይወት እየጠፋና የአካል ጉዳት እየደረሰ ነው፣ በመንግስትና በግል ንብረቶች ላይ ውድመት እየደረሰ ነው፣ ከዛም አልፎ ብሄርንና ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ ጥቃት እየደረሰ ይገኛል፡፡ ከዚህ እንደምንረዳው በተለያዩ አካባቢዎች የተነሳው ተቃውሞና ግጭት አቅጣጫውን እየሳተና አደገኛ አዝማሚያ እየያዘ መምጣቱን ያሳያል፡፡

ከችግሩ መባባስ ጋር የመንግስት የሃይል እርምጃ ተባብሶ የቀጠለበት መሆኑ ሲታይ መንግስት ችግሮችን በተገቢው ግዜና ሁኔታ በአግባቡ ለመፍታት የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ እየተከተለ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ መንግስት እየተከተለው ያለው ችግሩን በሃቀኛ ውይይት እና መግባባት የመፍታት ሳይሆን በሃይል እርምጃ የማፈን አቅጣጫ እንደማያዋጣ ተገንዝቦ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ለማምጣት የሚያስችል አቅጣጫ መከተል እንዳለበት ፓርቲያችን አበክሮ ያሳስባል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም በተለያዩ የሃገሪቱ አካባቢዎች የተቃውሞ እንቅስቃሴ እያደረገ የሚገኘው የህብረተሰብ ክፍልም ተቃውሞውን ሰላማዊና ህጋዊ ማድረግ እንዳለበት ኢዴፓ ያምናል፡፡

የህብረተሰቡን የተቃውሞ እንቅስቃሴ ተገን በማድረግም የራሳቸውን ድብቅ አላማ ለማስፈጸም ሲሉ ግጭቱን ለማባባስ ጥረት የሚያደርጉ ሃይሎችንም ኢዴፓ አጥብቆ ያወግዛል፡፡ ህዝቡም በተቃውሞ ሰበብ አብሮ የመኖር ባህላችንንና እርስ በእርስ ያለንን አንድነት ከሚያናጉ ተግባሮችና ድርጊቶች በመቆጠብ የጠባብ ቡድኖችን ርካሽ አላማ መከላከል አለበት፡፡ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሰውም ውድመት ፍጹም ተገቢ ያልሆነ ተግባር በመሆኑ ኢዴፓ አጥብቆ እያወገዘ መንግስት ጉዳዩን የሚያጣራ ገለልተኛ ቡድን ባስቸኳይ አቋቁሞ ውጤቱን ለህዝቡ ይፋ እንዲደርግ ኢዴፓ በድጋሚ ይጠይቃል፡፡

በዋናነት ኢዴፓ በተለያዩ መድረኮች እንደምንገልጸው የፌደራል አደረጃጀቱ ከአንድነት ይልቅ ልዩነት ላይ ያተኮረ በመሆኑ በዜጎች ተንቀሳቅሶ የመስራትና ሃብት የማፍራት ህገ መንግስታዊ መብታቸው ላይ ትልቅ አደጋ ፈጥሯል፡፡ በተለያዩ ግዜያት በሃገራችን እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ብሄረሰባዊ ማንነት ላይ መሰረት ያደረገም ጭምር መሆኑ የሚሰተዋል ነው፡፡ መንግስት አሁንም በሃገሪቱ ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በፌደራል አደረጃጀቱ ላይ ለውን አቋም መመርመር አለበት፡፡

በመጨረሻም በተለይ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ እንደታየው ዘርንና እምነትን አስታኮ የሚፈጸም ጥቃት ይህችን ሃገር ወደማያባራ ግጭት ውስጥ ሊከት የሚችል አደገኛ አዝማሚያ መሆኑን ህብረተሰቡ፣ መንግስት፣ የፖለቲካ ሃይሎችና የመገናኛ ብዙሃን ተገንዝበን በህብረት እንድንታገለው ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አሁን ያለው ያለመረጋጋት በዚሁ ከቀጠለ ማንም አትራፊ እንደማይሆን እየገለጸ በድጋሚ ሁሉም ሃይሎች ሃገሪቱ ወደ ለየለት ቀውስ ውስጥ አንዳትገባ የየበኩላቸውን ሃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ለማስገንዘብ ይወዳል፡

 

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

የካቲት 16 2008 .

ምርጫው ዴሞክራሲያዊ ፍትሀዊ በሕብረተሰቡም ዘንድ ተአማኒ አልነበረም !!

ከኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት ተገንብቶ ነጻና ዴሞክራሲዊ ምርጫ በሃገራችን ተካሂዶ ህዝቡ ከተለያዩ አማራጮች ይበጀኛል ለሚለው ፓርቲ ስልጣን በውክልና የሚሰጥበት ስርአት እውን እንዲሆን በጽናት ሲታገል ቆይቷል፡፡ ይህ የምርጫ ስርአት ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ሁኔታ እውን እንዲሆን በየምርጫዎቹ በመሳተፍ የሚገጥሙ እንቅፋቶችንና ችግሮችን በመቃወምና እንዲታረሙም ትግል በማድረግ የበኩሉን አስተዋፆኦ እየተወጣ ይገኛል፡፡ ከዚህ እምነቱም በመነሳት በ2007ቱ አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በቂ ዝግጅት አድርጎ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ወደ ምርጫው በመግባት ለሰለጠነ የምርጫ ስርአት እውን መሆን ያለውን ፍላጎት እንደ ከዚህ ቀደሙ በተግባር አረጋግጧል፡፡

በምርጫውም ውስጥ በነበረው ተሳትፎ በምርጫው ሂደት ላይ በተደጋጋሚ ሲያጋጥሙ የነበሩ እንቅፋቶችና ችግሮች በምርጫው ፍትሃዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነትና ተዓማኒነት ላይ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን በማሳሰብና ድርጊቱንም በመቃወም በተደጋጋሚ መግለጫ መስጠታችን ይታወቃል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በተለይም ምርጫ ቦርድ፣ ገዥው ፓርቲና የመገናኛ ብዙሃን ለምርጫው ስኬታማነት የበኩላቸውን አስተዋፆኦ እንዲወጡም ተደጋጋሚ ጥሪ ስናደርግ ቆይተናል፡፡

ሙሉውን መግለጫ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ። (PDF)

የኢዴፓ የ2007 ዓ.ም የምርጫ መወዳደሪያ ማንፌስቶ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የ2007 ዓ.ም የምርጫ መወዳደሪያ ማንፌስቶ

EDP_Manifesto_Cover

ከኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ የተሰጠ የመልካም ምኞት መግለጫ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ መጭው ዘመን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ስርአት የሚጠናከርበት፣ የጥላቻና የኩርፊያ ፖለቲካ ታሪክ የሚሆንበት፣ የመቻቻልና የመከባበር ፖለቲካ የሚጎለብትበት፣ የጭፍን ተቃውሞና ድጋፍ በአማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ የሚተካበት፣ ምክንያታዊ ፖለቲካ የሚያብብበት፣ በመጭው 2007 ምርጫ ህዝቡ በተሳትፎው የሰለጠነና የበቃ ህዝብ መሆኑን ዳግም የሚያረጋግጥበት፣ የፖለቲካ ምህዳሩ ሁሉንም አሳታፊ በሆነ መልክ የበለጠ የሚሰፋበት እንዲሆን በመመኘት የሀገርን ዳር ድንበር ለማስጠበቅ በግምባር ለተሰማራችሁ ለመከላከያ ሰራዊት አባላት፣ በማረሚያ ቤት ለምትገኙ ወገኖቻችን፣ እንዲሁም በስደት ከሀገር ውጭ ላላችሁ ወንድሞችና እህቶች በአጠቃላይም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ በሙሉ መጭው ዘመን የሰላም፣ የጤናና የፍቅር እንዲሆንላችሁ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ኢዴፓ/ ስራ አስፈጻሚ መልካም ምኞቱን ይገልጻል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ

በሽብርተኝነት ስም የሚወሰደው እርምጃ ግልጽነት ይኑረው!

ከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ

በአገር ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም መንግስት በሽብር ጠርጥሮ በቁጥጥር ስር ማዋሉ በሚዲያዎች ተገልጿል፡፡ እነዚህ አመራሮች ከ48 ሰዓታት በላይ ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውና የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት በጉዳዩ ላይ ዝርዝር መረጃ አለማቅረባቸው አመራሮቹ የታሰሩት በሚያራምዱት የፖለቲካ አቋም እንዳይሆን ፓርቲያችን ስጋት አድሮበታል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ጥልቅ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተለውን አቋም ወስዷል፡፡

 1. መንግስት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች የተያዙበትን ምክንያት ለህብረተሰቡ ዝርዝር እና ግልጽ መረጃ እንዲሰጥ፤
 2. የታሰሩት የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 21 መሰረት ለዜጎች የተሰጠው መብት እንዲከበርላቸው፤
 3. በአስቸኳይ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ፤ የፍርድ ሂደታቸውም ተአማኒ፤ ግልጽ እና ፈጣን በሆነ መንገድ እንዲታይ እያሳሰብን
  ይህ ሳይሆን ቢቀር ግን የአገሪቱን ህግ አክብረን በሰላማዊ ትግል ከምንንቀሳቀስ ፓርቲዎች ይልቅ ከዚህ በተቃራኒ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኛ ሀይሎችን የሚያጠናክር፤ ክርክራቸውንም ምክንያታዊ የሚያደርግ እና የዴሞክራሲያዊ ግንባታውን ወደኋላ የሚመልስ በመሆኑ ጉዳዩ እጅግ እንደሚያሳስበን እንገልጻለን፡፡

ስለዚህም መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝቦ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጥ ኢዴፓ ያሳስባል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
ሐምሌ 7 ቀን 2006 ዓ.ም

ሰላምና ህብረ-ብሔራዊነት አላማችን ነው!

ለዘላቂ ልማት የፌደራሊዝሙ ጉድለቶች ይታረሙ!

ሰሞኑን በአንዳንድ የኦሮሚያ ከተሞች የተከሰተውን ብጥብጥና በዚህ ምክንያት በሰዎችና በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡

 1. የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ባደረገው ውይይት እና ማጣራት ለግጭቱ መነሻ የሆነው ዋና ምክንያት ለአዲስ አበባና ለአጎራባች የኦሮሚያ ክልል ከተሞች የተዘጋጀው የጋራ የልማት መሪ ፕላን መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ ኢዴፓ የተዘጋጀው መሪ ፕላን ለአካባቢው የልማት እድገት ጠቃሚ መሆኑንና የአገራችንን ህግጋት የጣሰ አካሄድ አለመሆኑን አምኖበታል፡፡
 2. ማንኛውንም ቅሬታ አለኝ የሚል ወገን ቅሬታው ወይም ተቃውሞው ሊከበርለት ይገባል፡፡ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖችን (ለሚያነሱት ቅሬታ ሌላ ፖለቲካዊ ትርጉም ሳይሰጥ) በአግባቡ ማዳመጥና ተገቢውን መልስ መስጠት ይገባዋል፡፡
 3. በመሪ ፕላኑ ላይ ቅሬታ ያላቸው ወገኖች ቅሬታቸውን ለመግለፅ ህጋዊና ሰላማዊ መንገድን ብቻ መጠቀም ይኖርባቸዋል፡፡ በሰዎች ህይወት እና ንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ ተቃውሞን ለመግለፅ የሚደረገውን ሙከራ ኢዴፓ ያወግዛል፡፡
 4. መንግስት ህግና ስርአት እንዲከበር የማድረግ ሃላፊነት እና ግዴታ ያለበት መሆኑን እንደተጠበቀ ሆኖ በአመፅ መልክ ለሚገለፁ ተቃውሞዎች የሚወሰደው እርምጃ ጥንቃቄ የተሞላበትና በተቻለ መጠን በሰዎች አካልና ህይወት ላይ ጉዳት የማያስከትል መሆን ይገባዋል፡፡
 5. ሰሞኑን በተለያዩ ከተሞች በተፈጠረ ብጥብጥ የሰው ህይወትና የአገር ሃብት ተጠያቂው ማን እንደሆነ በአግባቡ የሚያጣራ ገለልተኛ ኮሚቴ መንግስት እንዲያቋቁምና በተጠያቂው አካል ላይ ህጋዊ እርምጃ እንዲወስድ ኢዴፓ ይጠይቃል፡፡
 6. በአጠቃላይ እንዲህ አይነቱ ብሔራዊ ማንነትን መሰረት ያደረገና ለአገራዊ የልማት እድገት ፀር የሆነውን ጠባብ አመለካከት በአገራችን እየተጠናከረ የመጣውና ምናልባትም ወደፊት የበለጠ ተባብሶ ሊቀጥል የሚችለው በዋናነት በብሔራዊ ማንነት መሰረት ካደረገው የአገሪቱ የፌደራል አደረጃጀት ጉድለቶች በመነጨ ነው፡፡ ይህ አይነቱ ችግር በዘላቂነት ሊፈታ የሚችለው የፌዴራሉ አደረጃጀት እና ፖሊሲዎች ለአገር አንድነትና ለጋራ ልማት በሚበጅ መልኩ  ሲሻሻሉ ብቻ ነው ብሎ ኢዴፓ ያምናል፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
                      ሚያዝያ 28/2006 ዓ.ም
                ሰላምና ህብረ-ብሄራዊነት አላማችን ነው!!

በሐረር ከተማ የተፈጠረው ችግር አስቸኳይ መፍትሄ ያሻዋል!

ቀን 02/07/2006 ዓ.ም
ቁጥር ኢ.ዴ.ፓ.023/06

የካቲት 30 ቀን 2006 ዓ.ም ምሽት ሁለት ሰዓት አካባቢ በሐረር ከተማ ከፍተኛ የእሳት ቃጠሎ ተከስቷል፡፡ ከዚህ በፊትም በዚሁ አካባቢ ተደጋጋሚ የእሳት ቃጠሎዎች መከሰታቸው ይታወሳል፡፡ ችግሩ እንደተከሰተ መንግሥት ድርጊቱን የፈፀመውን አካል ለማወቅ የማጣራትና ህብረተሰቡን የማረጋጋት ሥራ መሥራት ሲገባው በተመሳሳይ ቀን በተቻኮለ ሁኔታ ግሬደር አቅርቦ አካባቢውን ማፅዳት በመጀመሩ ህብረተሰቡ በመንግሥት ላይ የተለያዩ ጥርጣሬዎች እንዲያድሩበት ምክንያት ሆኗል፡፡

በዚህም ምክንያት አላስፈላጊ ግጭት ተፈጥሮ ንብረት ወድሟል፣ የንግድ እንቅስቃሴ ተቋርጧል፣ በሰዎችና በሰላማዊ ህይዎታቸው ላይ መጠኑ ያልተረጋገጠ ጉዳት ደርሷል፡፡ ስለሆነም መንግሥት እንደነዚህ እና መሰል ችግሮች ሲከሰቱ በሰከነ መንገድና ግልፅነት ባለው አሰራር ከህብረተሰቡ ጋር እየተመካከረ መፍታት ይገባዋል ብሎ ኢዴፓ በፅኑ ያምናል፡፡ ህብረተሰቡም ግጭቱ አቅጣጫውን ስቶ ተጨማሪ አላስፈላጊ ጉዳት እንዳይደርስ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት የተፈጠረውን ግጭት መንግሥት ቆም ብሎ ችግሩ የተፈጠረበት ምክንያት ምን እንደሆነና ማን እንደፈጠረው በአስቸኳይ አጣርቶ እርምጃ እንዲወስድና በቃጠሎው ምክንያት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች ተገቢውን መፍትሄ በአስቸኳይ እንዲሠጥ ኢዴፓ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

የኢዴፓ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ

ሰላምና ህብረ-ብሔራዊነት አላማችን ነው!

ውይይትና ድርድር ደከመኝ፣ ሰለቸኝ የማይባልበት ብቸኛው የሰላምና የዴሞክራሲ አማራጭ ነው፡፡

ከኢዴፓ የተሰጠ መግለጫ፡፡

የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማህበረስብ አካላትና መንግስት በተለያየ መድረክ መፋጠጥ ከጀመሩ ከአስራ ስምንት ወራት በላይ ሆኗል፡፡ በአብዛኛው ከአዲስ አበባና አካባቢዋ የሶላት ስግደት ቀን ያልዘለቀው  የመብት ጥያቄ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መዳረሻውን እየሰፋና እያደገ በመሄድ በርካታ ሙስሊሞችን ማካተት ችሏል፡፡እንቅስቃሴውን ለመግታት መንግስት በተከታታይ በወሰደው እርምጃ ምክንያት በሰው ሕይወትና ንብረት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች  ደርሰዋል፡፡ በተለይ ደግሞ ካለፉት ጥቂት ወራት ወዲህ ግጭቱ በስፋትና በቅርጽ እየጎለበተ በመሄድ ወደ ሌሎች የአገሪቱ አካባባዎች በመዛመት በበርካታ ዜጎች ዘንድ አነጋጋሪና አሳሳቢ ጉዳይ ለመሆን በቅቷል፡፡

በኢዴፓ እምነት ዜጎች በሃይማኖታዊም ሆነ በፖለቲካዊ አሊያም በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥያቄ የማንሳት፣ ከመንግስትና ከመንግስታዊ ተቋማት ጋር ወይም በተናጠል የመብት ጥያቄዎቻቸውን የማቅረብ፣ የመደራደርና መፍትሔ የመሻት መብታቸው ያለአንዳች ገደብ ሊከበር እንደሚገባ አጠንክሮ ያምናል፡፡ ኢዴፓ  ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ፣ የመቃወም፣ ያለማንም ጣልቃ ገብነት የማምለክና የመሳሰሉት ዴሞክራሲያዊና ሰብአዊ መብቶች እንዳይሸረሸሩ ዘብ የሚቆምላቸው አጀንዳዎቹ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

በሌላ በኩል ኢዴፓ እነዚህ የመብት ጥያቄዎች በስምምነት ካልሆነ በስተቀር የሌሎችን ጥቅምና መብት በማይነኩበትና በሕገ-መንግስቱ ላይ በሰፈረው መሰረት መቅረብ፣ መደመጥና አግባብነት ያለውን ፍትሐዊ መልስ የማግኝት ዋስትና ሊኖራቸው እንደሚገባ ያምናል፡፡ ከዚህም በላይ ዜጎች ጥያቄዎቻችን በበቂ ሁኔታ አልተመለሱም ብለው ሲያምኑ ጥያቄዎቻቸው እንዲመለሱቸው ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሰላማዊ ሰልፍ፣ የአዳራሽና ሕዝባዊ ስብሰባ በማድረግ በመንግስት ላይ ገንቢ ተጽእኖ በመፍጠር ለጥያቄዎቻቸው መፍትሄ የመሻትና የማግኘት መብታቸው ሊሸረሸርና ሊገሰስ እንደማይገባ ኢዴፓ በጽኑ ያምናል፡፡

መንግስትና ተቋማቱ ዜጎች በሕገ-መንግስቱ ላይ የሰፈሩ መብቶቻቸው ወደ ተግባር እንዲለወጡ ሁኔታዎችን በማመቻቸትና ጥያቄዎቻቸው በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን አቅጣጫ በማሳየት፣ የማገዝና ቅራኔዎችን በሰለጠነ መንገድ በትዕግስት የመፍታት የሞራልና ሕጋዊ ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግስት በአጣብቂኝ ውስጥም ሆኖ ቢሆን ከዜጎች የሚቀርቡ የመብት ጥያቄዎች እንዳይጨፈለቁ ጥበቃ ማድረግ ይገባዋል፡፡ በተለይ ደግሞ መንግስት በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚቀርቡለትን የመብት ጥያቄዎች ለማስከበር የሚሄድበት ርቀት የዜጎችን የመብት ጥያቄ ለማስተናገድ የሚኖረውን ቁርጠኝነት የምንለካበት ነው፡፡

መንግስት በማንኛውም መስፈርት ዜጎች ጥያቄዎቻቸውን በነጻነት የማቅረብ መብታቸው እንዳይታፈን በማድረግ ቁርጠኝነቱን ማሳየት የሚጠበቅበትን ያህል አጀንዳዎቹ ተጠልፈዋል ብሎ በተጨባጭ መረጃ ሲያምን የችግሩን ምንጮች ብቻ ለይቶ በማውጣት ቀሪው ዜጋ ጥያቄውን የማስተጋባት መብቱ እንዲቀጥልና መፍትሔ እንዲያገኝ በማድረግ ሕገ-መንግስታዊ ግዴታውን መወጣት አለበት፡፡ መንግስት በዚህ የመብት ጥያቄ ሂደት ውስጥ መብታቸውን በአግባቡ መጠቀም ያልቻሉ ዜጎች ቢገኙ እንኳን በዜግነታቸው ተገቢውን ሕጋዊ ጥበቃና እንክብካቤ ሳያጓደልባቸው ሕግ ፊት በማቅረብ ሳይፈረባቸው ወንጀለኛ ያለመባል ሕገ-መንግስታዊ መብታቸውን በማስከበር ዋስትና መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡

ኢዴፓ “መብቶች ሁሉ ግዴታ ያዘሉ መሆናቸውን” የምናምነውን ያህል የመብት ጥያቄዎች በቅድመ ሁኔታዎች መጨናገፍና መጨፍለቅ እንደሌለባቸው ደግሞ በጥብቅ የምንታገልለት ፍልስፍናችን ከመሆኑም በላይ ስህተት ሊሰራበት የማይገባ ጉዳይ መሆኑን ግልጽ ለማድረግ እንሻለን፡፡

ከላይ በዝርዝር ያነሳናቸው የሰብአዊና የዴሞክራሲያዊ መብቶች በመርህ ደረጃ እንደተጠበቁ ሆነው፡፡ ካለፉት አስራ ስምንት ወራት ወዲህ በሙስሊሙ ማህብረስብ ውስጥ የተነሳውና እስከ አሁንም የዘለቀው  የመብት ጥያቄ መፍትሔ ሳያገኝ በእንጥልጥል መቆየቱና ከነአካቴውም ስፋት እያገኘ መምጣቱ መንግስት በተናጠል በሚወሰደው የእምቃ እርምጃዎች ብቻ ጥያቄዎቹ ሊፈቱ እንደማይችሉ ጠቋሚ ምልክቶች ናቸው፡፡ ዛሬ ላይ ለመገንዘብ እንደቻልነው የመብት ጥያቄዎቹ መልስ ሳያገኙ ለበርካታ ወራት መዝለቃቸው ቅራኔው እየሰፋና መልኩን እየለወጠ በመሄድና ወደ አልተጠበቀ አቅጣጫ በመገፋት ለዜጎቻችንን ሞት፣ አካል ጉዳትና የንብረት ውድመት መንስኤ እየሆነ እንደመጣ ኢዴፓ በሃዘኔታ ለመታዘብ ችሏል፡፡

በተለይ ደግሞ በሙስሊሙ ማህበረሰብ የኢድ አልፈጥር በዓል  ላይ የታየው ፍጥጫ፣ ድብደባ፣ መጠነ ሰፊ እስርና እንግልት በማንኛውም መስፈርት ሃይል የተቀላቀለበት ፈጽሞ ያልተገባ እንደነበረ ኢዴፓ ያምናል፡፡ በዚህ አጋጣሚም በእለቱ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለታሰሩ የሙስሊሙ ማህበረስብ አባላትና ቤተሰቦቻቸው የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን መግለጽ ይወዳል፡፡ መንግስት የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማህበረስብ አባላትን በየበዓላቱ ቀን የመብት ጥቄዎቻቸውን በመያዝ ማብቂያ በሌለው አዙሪትና ፍጥጫ ውስጥ ገብተው ለሃይል እርምጃ እንዳይጋለጡ መደረግ እንዳለበት ኢዴፓ ያምናል፡፡ በዚህ አጋጣሚም በሂደቱ የታሰሩ ሙስሊሞች አሁን የሚገኙበትን ሁኔታ መንግስት ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርግ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ይህ ሳይሆን ቀርቶ ጥያቄዎቹ ከዚህ በላይ እየተገፉ ከሄዱ የጉዳዩን ጥልቀትና አሳሳቢነት በመረዳትም ሆነ ባለመረዳት ወይም በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ላልተፈለገ ግጭትና አለመረጋጋት በር መክፈቱ የማይቀር መሆኑ ግልጽ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ኢዴፓ በጉዳዩ ላይ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በሚመለከታቸው ፓለቲካዊ፣ ማህበራዊና የሃይማኖት ተቋማት አማካኝነት አጀንዳውን ወደ ወይይት መድረክ መመለስ ጉዳዩ መፍትሄ እንዲያገኝና በቅራኔ የተወጠሩ አካሄዶች እንዲረግቡ መንገድ እንደሚከፍት አምኗል፡፡ በፍጥጫና በውጥረት ውስጥ ያለን የሕዝብ ጥያቄ ማፈን ጊዜ ከመግዛት ያለፈ ፋይዳ የማይኖረው ከመሆኑም በላይ ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ የአጠቃላይ ማህበረሰቡን ጣልቃ ገብነትን መጋበዙ አጠራጣሪ አይሆንም፡፡

ከዚህም በላይ እጅግ አደገኛ የሆነው መንገድ ይህንን ክፍተት በመጠቀም በክርስትያንና በሙስሊሙ ማህበረሰቡ መካከል ልዩነትን የሚፈጥሩና ለቁርሾ የሚዳርጉ አደገኛ ዝንባሌውች ከየአቅጣጫው እየተደመጡ መምጣታቸው የጉዳዩን አሳሳቢነትና አደገኛነት እንድንገነዘብ የሚረዳ አመላካች ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ በኢዴፓ  እንዲዚህ ዓይነቶቹ አደገኛ ዝንባሌዎች ለጋራ ጥቅም ሲባል ምንጫቸውና ባለቤታቸው ማንም ይሁን ማን በሁላችንም የተባበረ ድምጽ ሊወገዙ እንደሚገባ ማስገንዘብ እንወዳለን፡፡

በመንግሰት በኩል በተደጋጋሚ የሚነሳው ስጋት የመብት ጥያቄው የአክራሪ ሃይሎች ሰለባ ሆኗል የሚል ነው፡፡ ኢዴፓ ይህ ጥያቄ  አሳሳቢ  መሆኑን ቢያምንም፤ ጉዳዩ በተጋነነ ሁኔታ እየቀረበ መሆኑን ለመረዳት አዳጋች እንዳልሆነ ይገነዘባል፡፡ ኢዴፓ፤ ኢትዮጵያዊያን የዓለም ማህበረሰብ አካል እንደመሆናችን መጠን የጉረቤት ሃገሮችን ጨምሮ አንዳንዳ ሃይሎች የውስጥ ጉዳዮቻችንንና ተፈጥሮአዊ ልዩነቶቻችንን አላግብብ በመለጠጥና በማራገብ የስግብግብ አጀንዳቸው ማራመጃ አድርገው ለመጠቀምና ሃገራችንን ከአደገኛ ሁኔታ ጋር ለማላተም የሚተጉ ሃይሎች የሉም የሚል “የዋህ” እምነት ያለው ፓርቲ አይደለም፡፡ ይህም ሆኖ እያለ ለእንደዚህ ዓይነቱ አደጋ አጋልጦ ወይም አመቻችቶ የሚሰጥንና  ምዕራፉን የሚከፈተው ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመደማመጥና በመግባባት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያለን አቅም ሲዳከም ብቻ  እንደሆነ ኢዴፓ ለማሳሰብ ይወዳል፡፡

ከዚህ መሰረታዊ ሃሳብ በመነሳት  የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማህበረስብ አባላትን ጉዳይ መንግስት እንደገና ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ በማምጣት መልስ እንዲያገኝ ጥረት እንዲያደረግና የተጀመረውን ፍጥጫና ቅራኔ የሚያረግቡ እርምጃዎችን አንዲወስወድ ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡ የመብት ጥያቄ ያነሱ የሙስሊሙ ማህበረስብ አካለትም ጥያቄዎቻችው መልስ እንዲያገኙ ወደ ውይይትና ድርድር መድረክ መመለሱ ወደ ውጤት የሚወስዳቸው ብቸኛ መንገድ መሆኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ፍጠጫዎቹንና ግጭቶቹ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን  ያልተገባ ዋጋ እንዳያስከፍል የድርድርና የውይይቱን መንገድ በቁርጠኝነት እንዲገፉበት ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የሃይማኖት ተቋማት፣ ታዋቂ ግለሰቦች፣ የሙያ ማህበራትና ማህበራዊ ተቋማት ይህ ጉዳይ የራሳቸው ጉዳይ መሆኑን ከወዲሁ ተረድተው ቅራኔውን ተቀራርቦ በመወያየት መፍትሔ እንዲያገኝ ገንቢ ግፊት  እንዲያደርጉ ኢዴፓ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

ሰላምና ሕብረ ብሔራዊነት ዓላማችን ነው፡፡

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፡፡