Clicky

ኢዴፓ በመቐለ ከተማ ህዝባዊ ስብሰባ ሊያካሂድ ነው

ኢዴፓ ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ ባስቀመጠው የሦስተኛ አማራጭነት ሚናውን ወደ ህዝብ የማስረጽ እቅድ አንዱ አካል የሆነው ህዝባዊ ስብሰባ በማካሄድ ከህዝብ ጋር የመወያያ መድረክ ማዘጋጀት መሆኑ ይታወቃል፡፡ የዚህ አካል የሆነው የአዲስ አበባ ህዝባዊ ስብሰባ እንደተጠናቀቀ ስራ አስፈጻሚው ወደ መቀሌ ጉዞ እንደሚያደርግ ታውቋል፡፡  ስራ አስፈፃሚው የህዝባዊ ስብሰባውን በሌሎች ክልል ከተሞች ላይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከጽ/ቤቱ እንዳገኘነው መረጃ ሌሎች ህዝባዊ ስብሰባው የሚካሄድባቸው የክልል ከተሞች መካከል ባህር ዳር፣ ሃዋሳ፣  ናዝሬት፣ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በ2007 ምርጫ ፓርቲውን ይረዳው ዘንድ በአፋር ክልል አምስቱ ዞኖች በቤንሻንጉል ጉምዝ ስምንት ዞኖችና ወረዳዎች እንዲሁም በአገሪቱም አራቱም አቅጣጫዎች ድርጅታዊ ስራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የኢዴፓ አመራሮች ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባላት ምርጫ ቦርድ ከundp ጋር በመተባበር ባዘጋጀው ስብሰባ እና ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመለሱ፡፡ የፖለቲካ ምህዳሩንና በምርጫ 2007 ፓርቲዎች በሚኖራቸው ተሳትፎ ዙርያ ለማወያየት ለሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ባደረገው ጥሪ መሰረት ኢዴፓን ጨምሮ 8 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡

በቦታው ላይ የተገኙትም የፓርቲ ተወካዮች በጋራና በተናጥል ስለ ፖለቲካ ምህዳሩና ስለ ምርጫ 2007 ተሳትፎአቸው ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡ ስብሰባውን በንግግር የከፈቱት የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ሲሆኑ በቦታው የተገኙት የፓርቲው የጥናትና ምርምር ሃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ የፓርቲውን አቋም ለundp ተወካዮች አስረድተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ሃላፊ አቶ ኤርምያስ ባልከው ለ5 ቀናት ደብረ ዘይት በሚገኘው የስራ አመራር ኢንስቲትዩት በግጭት አፈታት (conflict management) ዙርያ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ ተካፍለው ተመልሰዋል፡፡ በስልጠናው ላይ ኢህአዴግን ጨምሮ 23 ሀገር አቀፍ ፓርቲዎች ተካፋይ ሆነዋል፡፡  ፓርቲዎቹ በግጭት አፈታት ዙርያ ያላቸውን ተሞከሮ በውይይትና በቡድን ስራ ላይ እርስ በርስ የተለዋወጡ ሲሆን  ችግር እንዳይፈጠርና ችግር ተፈጥሮም ቢገኝ  ፓርቲዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸውና ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባህላችን መዳበር እንዳለበት መጠቆማቸውን አክለው ገልጸዋል፡፡

በስልጠናው ማጠቃለያም የምርጫ ቦርድ ዋና ጸሃፊ ለስልጠናው ተካፋዮች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል፡፡ ይሄ ስልጠና ለ2ኛ ግዜ የተካሄደ ሲሆን በመጀመርያ ዙር በተካሄደው ስልጠና ላይ የፓርቲው የፋይናንስ ሃላፊ አቶ አዳነ ታደሰ ተካፍለው መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡

ኢዴፓ ለሚቀጥለው አገር አቀፍ ምርጫ ያለውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር የሚያስችሉ መዋቅሮችን ፈጠረ

የኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ በሚቀጥለው አመት ለሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በአዲስ አበባ እና በሌሎች አካባቢዎች ያለውን እንቅስቃሴ ለማጠናከር  የሚያስችሉ መዋቅሮችን ፈጠረ፡፡ ስለሆነም ዘጠኝ አባላት ያሉት የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ኮሚቴ ተቋቁሞ ኃላፊነት በመከፋፈል ሥራ ጀምሯል፡፡

ጊዜያዊ ኮሚቴው ባካሄዳቸው ሁለት ስብሰባዎች አመራሩን መርጧል፡፡ በዚህም መሰረት አቶ ግዛቸው አንመው ሰብሳቢ፣ አቶ መንገሻ ገ/ሚካኤል ም/ሰብሳቢ ፤ አቶ ለማ ጪማ ፀሐፊ፤ ወ/ሪት አለም ዘውዱ ድርጅት ጉዳይ እንዲሁም አቶ አስማማው ተሰማ የኮሚቴው ህዝብ ግንኙነት በመሆን ተመርጠዋል፡፡ በዛሬው እለትም ኮሚቴው ሶስተኛ ስብሰባውን እያካሄደ ይገኛል፡፡

በተያያዘ ዜናም በቦንጋ፣ በሀዋሳ፣ በወላይታ፣ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ወሎ እና በሀረርጌ የፓርቲ መዋቅሮች የየአካባቢያቸውን አመራር በመምረጥ የእውቅና ጥያቄ በማቅረብ እውቅና ተሰጥቷቸው ወደስራ እንዲገቡ ተደርጓል፡፡
[facebook_like_button]

[facebook_send_button]