Clicky

የፀረ ሽብር ህጉና የኛ ምክናያታዊ ተቃውሞ (2)

Wasihun Tesfaye, executive committee member of Ethiopian Democratic Partyከዋሲሁን ተስፋዬ
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል

ባለፈው  አስራ አምስት ቀን በወጣው ኢትዮ-ምህዳር ጋዜጣ ላይ ከላይ በተጠቀሠው ርዕስ ስር የፀረ-ሽብር ህጉን በተመለከተ የመጀመሪያ ክፍል ፅሁፍ መውጣቱ የሚታወቅ ነው፡፡ በባለፈው ሳምንት የህጉን አንቀፅ ከቁጥር 1-21 ያለውን አንቀፆች አለፍ አለፍ እያልን ከህግ መንግስቱና ከሌሎች የአገሪቱ ህጎች ጋር ያለውን ግልፅ ተቃርኖ ህጉን ለማየት ተሞክሯል፡፡ ለዛሬ የመጨረሻውን ክፍል ለማየት እንሞክራለን፡፡

የፀረ-ሽብር አዋጁ ቁጥር652/2001 በክፍል አራት ተቀባይነት ስለሚኖራቸው ማስረጃዎች (Admissible evidences) በቁጥር 23 አስቀምጧል፡፡ ይህን ከማየታችን በፊት ግን በህጉ አግባብ ማስረጃ ማለት ምን ማለት ነው? ምን አይነት ማስረጃስ ነው በህግ ፊት ተቀባይነት የሚኖረው ? የሚለውንና መሰል ጉዳዮችን እንመልከት

ማስረጃ በአጠቃላይ በኑሮአችንም ሆነ በማህበራዊ ህይወታችን ውስጥ የማይተካ ሚና ያለው ነው፡፡ ሕይወታችን በሙሉ በማስረጃ ክስተት የተሞላ ነው በአጠቃላይ በእንቅስቃሴያችን ቦታ ሁሉ ማስረጃ የማይኖርበት ቦታ የለም በህግ ጥናትም ውስጥ ማስረጃ ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው ፡፡

ማንኛውም የህግ ጉዳይ ያለማስረጃ ዋጋ አይኖረውም በመሆኑም ለህጉ ቀጥተኛ አፈፃፀም ማሽረጃ የሚጫወተው ሚና ቀላል አይደለም ያለዳኝነት ፍትህ አይበየንም ፣ያለማስረጃ ዳኝነትም አይኖርም፡፡

ማስረጃ ማለት የአንድን አከራካሪ ነገር መኖር ወይም አለመኖር (existence or non-existence) የዳኛው አይምሮ እንዲያምን (Persuade) የሚያደርግ ነገር ነው፡፡ በአጭሩ ዳኛው በፊቱ የቀረቡለትን ጉዳይ እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ለመረዳትና ከውሳኔ ላይ ለመድረስ ግምት ለመውሰድ አእምሮው የሚመራበትን ነገር የያዘ ወሣኝ ሰነድ ነው፡፡ ስለዚህም ይህ የሚቀርብ ማስረጃ በወንጀልም ሆነ በፍታብሔር ጉዳዮች የተጠረጠረውን ሰው ጥፋተኛ ለማሰኘት ትልቅ አቅም ያለው በመሆኑ ከምንም በላይ ህጉ ጥንቃቄ የሚያረግበት ነው፡፡ በተለይም በወንጀል ጉዳይ ሲሆን ማስረጃ በፍትህ መንበሩ ላይ የተቀመጠውን ዳኛ ከጥርጣሬ በፀዳ መልኩ (Beyond reasonable doubt) ማሳመን መቻል አለበት ምክናያቱም የወንጀል ቅጣት የሰውን ልጅ ከነፃነት ማሳጣት አልፎ ክብር ሕይወቱን እስከመንጠቅ የሚደርስ በመሆኖ ነው፡፡ የህጉ ምርጫ ንፁሃን ያለአግባብ ከሚበደሉ አጥፊው ቢያመልጥ ይሻላል የሚል ነውና ፡፡

በኢትዮጵያ የህግ ስርዓትን አሁን እስካለንበት ጊዜ ድረስ ራሱን ችሎ በመጸሐፍ መልክ (በኮድ) የተዘጋጅ ህግ የለንም የማስረጃ ህጎቻችን በመጽኀፍ መልክ ተዘጋጅተው አይቅረቡ እንጂ በተለያዩ የወንጀል ህጉም ሆነ የፍታብሔር ህጋችን አንዲሁም በስነስርዓት ህጎቻችን ውስጥ ተበታትነው ይገኛሉ፡፡ በመጽሐፍ መልክ ህጎቻችን ከመፃፋቸው በፊትም ቢሆን አሁን ተቀባይነት የሌላቸው በጊዜው ግን ስራ ለይ ይውሉ የነበሩና እንደ ማስረጃ ማሰባሰቢያ ዘዴ ጥቅም ላይ ይውሉ የነበሩ እንደ “ሌባሻይ” አውጫጭኝ ወይም አፈርሳታ፣ ገዳ፣ ዋቅፍሴራ እና የመሳሰሉት ስራዓቶች ጥቅም ለይ ይውሉ ነበር፡፡

ከለይ ስለማስረጃ ህግና ተቀባይነት ሰላላቸው የማስረጃ ህጉች ይህን ያህል ካየን ለዛሬ ወደያዝነው ጉዳይ እንግባ፡፡ የፀረሽብር ህጉ (በአንቀጽ 23 ቁጥር 1-4)

  1. የመረጃውን ምንጭ ወይም መረጃውን እንዴት እንደተገኘ ባይገለጽም በሽብርተኝነት ወንጀል የተዘጋጀ የመረጃ ሪፖርት
  2. የሰሚ ሰሚ ወይም በተዘዋዋሪ የተገኘ ማስረጃዎች
  3. ዲጂታል ወይም ኤሌክትሮኒስ ማስረጃዎች
  4. በጠለፋ ወይም በክትትል የተገኙ ማስረጃዎች ወይም በውጭ አገር የህግ አስተባባሪ አካላት በተደረገ ጠለፋ የተገኙ መረጃዎች ተቀባይነት ይኖራቸዋል ብሎ ይደነግጋል

እነዚህን ከህግመንግስትና ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ህጉች አንጻር እንመልከት ‹‹የመረጃ ምንጭ ወይም መረጃው እንዴት እንደተገኘ ባይገለጽም ” በአንድ የወንጀል ጉዳይ ተጠርጥሮ የተያዘ ግለሰብ በፍርድ ቤት ፊት የሚቀርብበትን የፁሕፍም ሆነ የቃል ማስረጃ እሱን በወንጀለኘነት ለማስቀጣት የቀረበበት እስከሆነ ድረስ የሚቀርብበትን ሰነድ ምንጭ የማወቅ መብት አለው፡፡ ይህን የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህግ መንግስት አንቀጽም ሆነ ኢትዮጵያ በፊርማዋ ካጸደቀቻው አለም አቀፍ ህጉች አንፃር ስንመለከት የኢ.ፊ.ዴ.ሪ ህግ መንግስት አንቀጽ 20 (2) (4) የተከሳሾ ሰዎቸ መብት በሚለው ስር ተከሳሾች (2) “ክሱን በበቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸውና ክሱን በፅሁፍ የማግኘት መብት አላቸው ”

4.“የቀረበባቸውን ማንኘውንም ማስረጃ የመመልከት ለመከላከል የሚስችላቸውን ማስረጃ የማቅረብ ወይም የማስቀረብ መብት አላቸው ” ይላል፡፡ ይህም ማለት በወንጀል የተጠረጠረው ግለሰብ የሚቀርብበትን ማስረጃዎች ምንነትና ከየት እንደተገኘ የማወቅና የመጠየቅ ሕገ-መንግስታዊ መብት እንዳለው ሚደነግግ ነው፡፡ እንዲሁም ኢትዮጵያ ኦገስት 8 ቀን 1945 ያጸደቀችው የበላይ ህግ አካል በሆነው በአለም አቀፍ ስምምነት የኑረንበርግ ቻርተር ለይ የወጣው መርህ ደግሞ “fair trial for defendants” በሚላው አንቀጽ ስር “ የክስ ማመልከቻው በተከሳሾች ላይ የቀረቡትን ክሶች የወንጀል ሙሉ ዝርዘር የያዘ መሆን አለበት ” ይህ ማለት የክሱ ግልባጭና የሚቀርብበት ሰነዶች በሙሉ ከነምንጫቸው ለተከሳሽ በግልጽ ሊደርሱትና ሊነገሮት ይገባል ማለት ነው፡፡ ይህም የማይሆን ከሆነ ሰነዱ እንዲት እንደተገኘ ባልታወቀበት ሆኔታ ተከሳሱን ለመወንጀል ብቻ የተፈጠረ ሪፖሪት ፍ/ቤት ልቀርብበት የሚችል እድል ከፍተኛ ነው፡፡ ፍ/ቤቱም የቀረበው ሪፖርት ትክክለኝነትና ከየት እንደተገኘ ያቀረበውን አካል መጠየቅ ይኖርበታል ፡፡ ከሳሾም የሰነዱን እውነተኘነት (genuiness) በማስረጃ በማስደገፍ ማስረዳት ይኖርበታል፡፡ ይኸውም አንድ ምስክር የሚሰጠው ምስክርነት እውነትነትን በፍ/ቤት ፊት ቀርቦ በመሐላ እንደሚረጋግጠው ሁሉ ከሳሽም ያቀረበውን ረፖርት ምንጭና እውነተኘነት በሌላ ማስረጃ አስደግፎ የማረጋገጥ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ የህጉ መንፈስ ይህ ቢሆንም የፀረ ሽብር ህጉ ግን በአንቀጽ 23(1)ላይ ተጠርጣሪውን ወንጀለኛ ለማድረግ ዐቃቢ ህግ የሚቀርበውን የሰነድ ማስረጃ መረጃው እንዲትና ከየት እንደተገኘ ሳይገልጽ ከየትም አምጥቶ ቢቀርብ ፍ/ቤቱ መረጃውን ያለምንም ጥያቄ እንዲቀበል ግዴታ ይጥልበታል፡፡ ይህ አንቀጽ የፍ/ቤቱን ስልጣን በመግፈፍ ለዐቃቢ ህግ የከሳሽነትም የፈራጅነትም ስልጣን የሚሰጥ እንዲሁም ከህገ መንግስቱም ጋር ሆነ ኢትዮጵያ ከተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ህጉች ጋር በግልጽ የሚጣረስ ነው፡፡

ሁለተኛው የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ወይም የተዘዋዋሪ ማስረጃዎች ተቀባይነት በሚመለከት ነው፡፡ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ (Hearsay Evidence) በአንድ ሰው (ምስክር ባልሆነ ሰው ) አንደበት የተነገረ ሆኖ በሌላ ሁለተኛ ሰው አንደበት ተመልሶ በቃል ወይም በፅሕፍ የተነገረ ሲሆን ነው፡፡ በሌላ አባባል የቃሉ ምንጭ ሌው ሰው ሆኖ የሀሳብ ትክክለኝነትም ሆነ ብቃት በተናጋሪዊ ሰው ሳይሆን ቀድሞ በተናገረው ሰው ሁኔታ ላይ የተመሰረተ ምስክርነት ማለት ነው፡፡ በምስክርነት የሚቀርብው ሰው ለፍ/ቤቱ የሚያስረዳው እገሌ እንዴህ ሲል ሰምቻለው የሚለውን እንጂ የተባለው ነገር ሀሰት ይሁን እውነት የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ እስካሁን ባለውና የአገራቸን ፍ/ቤቶች የፀረ ሽበር አዋጅ እስከሚወጣ ድረስ ባለው ጊዜ የሰሚ ሰሚ ማስረጃን ተቀባይነት እንዳለው ማስረጃ አይቀበሉትም፡፡ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ በመሰረታዊ ሀሳብ በህግ ተቀባይነት የሌለው (Inadmissible Evidence) ነው፡፡ ለምን ? በሶስት ምክንያቶች

  1. ተከሳሽ ተናግሯል የተባለውን ሰው መስቀለኛ ጥያቄ ለመጠየቅና እውነቱን ለማውጣጣት እድል የማይሰጥ በመሆኑ (ተናገረ የተባለውን ሰው አስቀርቦ ለመጠየቅ ስለማይቻልና ማንነቱ ስለማይታወቅ)
  2. ፍ/ቤቱም ተናገረ የተባለው ሰው የተናገረው ነገር እውነት ወይም ሀሰት መሆኑን ለማጣራት የሚችልበት እድል ባለመኖሩ
  3. እውነቱን ማረጋገጥ ለማይቻል ማስረጃ የፍ/ቤቱን ጊዜ ማጥፋት አስፈላጊ ባለመሆኑ በአጭሩ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተቀባይነት የሚያገኘው እውነትነቱን ለማረጋገጥ የማይቻል በመሆኑ ነው፡፡ በህግ ስርዓት ዋነኛው የእውነት ነገር ማውጫ መሳሪያ የመስቀለኛ ጥያቄ ነው በሰሚሰሚ ማስረጃ ግን ተናገረ ወይም አለ የተባለውን ሰው ፍርድ ቤት አስቀርቦ ለመጠየቅ የማይቻል ስለሆነ እንዲሁም አንድን ተጠርጣሪ እውነት ባልሆነ ማስረጃ መቅጣት ኢ-ፍታዊ ስለሆነ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተቀባይነት የለውም፡፡ የጸረ-ሽብር ሕጉ ግን በአንቀጽ 23 (2) ላይ የሰሚ ሰሚ ማስረጃ ተጠርጣሪውን ለማስቀጣት በቂ ማስረጃ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ ይህ ህግ አስፈጻሚው በፖለቲካ አመለካከቱ ስጋት ያሳደረበትን ማንኛውንም ግለሰብም ሆነ ድርጅት ተጨባጭ ማስረጃ በሌለበት በአውጫጭኝና በሰሚ ሰሚ ብቻ ወንጀለኛ አድርጉ ለመወንጀል የገባ አንቀጽ እንጂ ሌላ ምንም ሊሆን አይችል፡፡

በጸረ-ሽብር ህጉ ላይ ሌላው በግልጽ የተቀመጠው እና አከርካሪው አንቀጽ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት ስለሚሰየምበት ስርዓት የተቀመጠው አንቀጽ 25 ነው፡፡ ይህ አንቀጽ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመንግስት አቅራቢነት ድርጅቶችን በአሸባሪነት ለመፈረጅ ስልጣን ይሰጠዋል፡፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን መቀመጫ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በገዢው ፓርቲ ቁጥጥር ስር በሆነበት ራሱ አስቀርቦ እራሱ የሚወስንበት እድል የሚሰጥ ነው፡፡ ይህም ማለት መንግስት በሽብርተኛነት ጠርጥሬዋለው ያለውን ድርጅት ለምክር ቤቱ አስቀርቦ ያለምንም ተቃውሞ በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ምንም የሚያግደው ነገር አለመኖሩን ያሳያል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን አንድ ድርጅት በሽብርተኝነት የሚሰየምበትን ሁኔታ ሲዘረዝር በአንቀጽ 25 (2) (መ) ላይ ‹‹በሌላ መንገድ ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ ከተገኘ›› ይላል ይህ በሌላ መንገድ የሚለው ቃል በህጉ ላይ እንዲካተት የተደረገው ለመንግስት የፈለገውን ተቋም በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ስፊ እድል የሚሰጥ በመሆኑ ብቻ ነው ህጉ አንድ ድርጅት በሽብርተኝነት ሊሰየም የሚችልበትን መንገድ በግልጽ አሻሚ ባልሆነ መንገድ ማስቀመጥ ቢኖርበትም ይህን ባለማድረጉ ለአስፈጻሚው ህጉን በፈለገው መንገድ እንዲተረጉም እድል የሚሰጥ ነው፡፡

እንደመውጫ

በአጠቃላይ በዚህም ሳምንት ሆነ በባለፈው ሳምነት የጸረ-ሽብር አዋጁን /አዋጅ ቁጥር 652/2001/ አንቀጾች ምክንያታዊ በሆነ መንገድ ለማየት እንደሞከርነው ይህ አዋጅ በጥቅል ይዘቱ ሀገሪቷ ካወጣቻቸውና ከተቀበለቻቸው አለም አቀፍ ህጎችም ሆነ ከህገመንግስቱ ጋር የሚጋጭና በግልጽ ሰባዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጥስ ነው፡፡ ዜጎችን የሚያሸብርና ለመንግስት የፈላጭ ቆራጭነትን ስልጣን የሚሰጥ ማንኛውንም ምክንያት እየፈጠረ ድርጅቶችን በሽብርተኝነት እንዲፈርጅ ንጹሐንን እንዲያስርና እንዲያስቃይ ህጋዊ ሽፍን የሚሰጥ አዋጅ ነው፡፡ በመሆኑም ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ እታገላለሁ የሚል ሀይል እና የዚች ሀገር እጣ ፈንታ መወሰን ያለበት በዲሞክራሲያዊና ፍታዊ ምርጫ ብቻ ነው ብሎ የሚያምን ሁሉ ይህን አዋጅ በአንድነት ወይ እንዲሻሻል ወይ እንዲቀየር ህጉ በሚፈቅደውና በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞውን ማሰማት ይኖርበታል፡፡ በቋፍ ላይ የሚገኘው የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ እንዳይጨናገፍ እንዲሁም አምባ ገነኖች ህግ እየጠቀሱ በህጋዊነት ሽፋን ስም ዜጎችን እንዳሻቸው እየረገጡና እየቀጠቀጡ እንዳይቀጥሉ ያገባኛል የሚል ሀይል ሁሉ በአንድ ድምጽ ህገመንግስታዊነት ለሁሉም ሊል ይገባል፡፡

 

 

የጸረ-ሽብር ህጉና የኛ ምክንያታዊ ታቃውሞ

Wasihun Tesfaye, executive committee member of Ethiopian Democratic Partyከዋሲሁን ተስፋዬ
የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ አባል

መንግስታት የሚያስተዳድሩትን ህብረተሰብ ዘላቂ ሰላም ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ለማሳለጥ የተለያዩ ህጎችን ሲያወጡና ሲያሻሽሉ መኖራቸው እውን ነው፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያም ከረጅም አመታት ጀምሮ እንደቀረው አለም ሁሉ ህጎችን ስታወጣና የወጡትንም ስታሻሽል ኖራለች ከመጀመሪያው የተጻፈ ህግ ነው ተብሎ ከሚታመነው የፍታ ነገስት ህግ ጀምሮ /ከ13ኛ ክ/ዘመን አሁን እስካለንበት ዘመን ድረስ አያሌ ህጎች በስራ ላይ ውለዋል የዋሉትም አንድም ተሽረዋል ወይም ተሻሽለዋል፡፡

ለዛሬ ከነዚህ ህጎች መሀል አንዱን ለመመልከት እሞክራለሁ፡፡ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በ2001 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 652 /2001/ የጸረ- ሽብርተኝነት አዋጅ ማውጣቱ ይታወቃል ይህ አዋጅ ከወጣ ስድስት አመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም እስካሁንም ግን ውግዘትን እያስተናገደ ይገኛል፡፡ ኢህአዴግ እንደ መንግስት ከተቋቋመበት ባለፉት ሀያ ሶስት ዓመታት ውስጥ ካወጣቸው አዋጆች እንደዚህኛው አዋጅ ከፍተኛ ተቃውሞ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጪ የደረሰበት አዋጅ የለም ማለት ይቻላል፡፡ ለምንድን ነው ይህ አዋጅ ከሌሎቹ አዋጆች በተለየ ከፍተኛ ተቃውሞ እየተሰነዘረበት ያለው አለፍ አለፍ እያልን በወፍ በረር /random/ የተወሰኑ አንቀጾችን እንመለከታለን፡፡

አዋጅ በመግቢያው ላይ እንዳሰፈረው የዚህ ህግ መውጣት አስፈላጊ የሆነው በስራ ላይ ያሉት ህጎች ሽብርተኝነትን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚያስችሉ ባለመሆናቸው ጠንካራ የህግ አቅም መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን እንደ አንድ ምክንያት ይጠቅሳል፡፡ ይህ የሽብርተኝነት ወንጀል በባህሪው ከሌሎች ወንጀሎች በተወሰነም መልኩ ቢሆን የሚለይ በመሆኑና አፈጻፀሙም እንደየጊዜው ሁኔታ የሚቀያየር በመሆኑ የተለየ ይህን ወንጀል ብቻ ሊዳኝ የሚችል ህግ መውጣቱ ብዙም የሚያከራክር አይሆንም፡፡ በአጭሩ አገሪቱ ራሱን የቻለ የጸረ ሽብር ህግ ቢኖራት የሚነቀፍ አይሆንም  ነገር ግን ጥያቄው ምን አይነት የጸረ-ሽብር ህግ ይኑራት የሚለው ነው፡፡ ምልከታችንን አንድ በአንድ እንቀጥል የዚህ አዋጅ / አዋጅ ቁጥር 652 /2001/ ህፀፅ የሚጀምረው ከትርጓሜው ነው፡፡

በአዋጅ አንቀፅ 2 (6) ላይ ማነሳሳት የሚለውን እንዲህ ሲል ከወንጀል ህጉ መንፈስ ውጪ ይተረጉማል ‹‹ ‹‹ማነሳሳት›› ማለት ድርጊቱ ባይሞከረም ሌላውን ሰው በመጎትጎት ተስፋ በመስጠት በገንዘብ በስጦታ በማስፈራራት ወይም በማንኛውም ሌላ ዘዴ የሽብርተኝነት ድርጊትን እንዲፈፀም ማግባባት ነው (ስርዝ የተጨመረ) ይህ አንቀጽ ከነበሩ የወንጀል ህግ ጋርም  ሆነ ከመሰረታዊ የወንጀል ባህሪያት አንጻር የሚፋለስ ነው፡፡ አንድ ወንጀል ተፈፅሟል የሚባለው በወንጀል ህጉ አንቀፅ 23 (2) በሠረት ሶስት ነገሮችን አሟልቶ ሲገኝ ነው‹‹ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚቋቋሙት ህጋዊ ግዝፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮችን በአንድነት ተሞልተው ሲገኝ ነው›› ህጋዊ ሲል አንድ ግለሰብ ወንጀል ፈፅሟል ለማለት በግልፅ በህጉ ላይ የተቀመጠውን አድርግ ወይም አታድርግ የሚለውን ሲጥስ ብቻ ነው
ዝፈው ሲል በተግባር የተገለፀ መሆን አለበት ማለት ሲሆን ሞራላዊ ሲል የሀሳብ ክፍል የሚያመለክት ሲሆን አውቆ አጥሮነትን ወይም ቸልተኝነትን ይወክላል፡፡ እነዚህ ሶስት ሁኔታዎች የወንጀል ሀላፊነት ቅድመ ሁኔታዎች መሆናቸውን ሕጉ በግልጽ ይደነግጋል በወንጀሉ ህግ እንደተቀመጠው ማነሳሳት የሚያስቀጣው ወንጀሉ ቢያንስ የተሞከረ እንደሆነ ነው፡፡ አንቀፅ 36(2) ‹‹ አነሳሹ የሚቀጣው ወንጀሉ ቢያንስ ተሞክሮ እንደሆነ ነው›› የፀረ-ሽብር ህጉ ግን ከላይ እንደተጠቀሰው ማነሳሳትን ድርጊቱ ባይሞከርም አንኳን አነሳሹን እንደሚቀጣ ይገልፃል ይህ የህጉ የመጀመሪያው ግልፅ ተቃርኖ ነው፡፡ የሚቀጥለውን አንቀጽ አለፍ ብለን እንመልከት የጸረ-ሽብር አዋጅ አንቀጽ 4 ላይ ‹‹ ማንኛውም ሰው በዚህ አዋጅ በአንቀጽ 3 ከንዑስ አንቀጽ (1) እስከ (7) የተመለከተውን ማናቸውንም የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ያቀደ የተዘጋጀ  ያሴረ ያነሳሳ ወይም የሞከረ እንደሆነ በዚሁ አንቀጽ በተቀመጠው መሠረት ይቀጣል ይላል ከነዚህ ውስጥ ማነሳሳት የሚለውን በመግቢያችን ላይ የተመለከትን በመሆኑ ሁለቱን የተሰመረባቸውን ብቻ በ1996 ተሻሽሎ ከወጣውና እየተጠቀምንበት ከሚገኘው የወንጀል ህግ አንጻር እንመልከት

1.    የተዘጋጀ፡- በወንጀል ህጉ አንቀፅ 26 ላይ ይህ በጸረ-ሽብር ህጉ የተዘጋጀ የሚለው ‹‹ የማሰናዳት ተግባር›› በሚል በግልፅ ተቀምጧል፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀጽ 26 ማዘጋጀት በራሱ እንደማያስቀጣ ‹‹የወንጀል ደርጊት ለማሰናዳት ወይም ለማመቻቸት በተለይም መሣሪያዎችን በማሰባሰብ ወይም ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር የተደረጉ ድርጊቶች አያስቀጡም›› በማለት በግልጽ ያስቀምጣል፡፡ ሆኖም መሰናዳት ወይም መዘጋጀት ሊያስቀጣ የሚችለው በህጉ ላይ እደተጠቀሰው ራሳቸው ወንጀል ሆነው የሚስቀጡ መሆናቸው በህግ የተደነገገ እንደሆነና ልዩ ወንጀል መሆኑ በህጉ በግልፅ የተገለፁ  እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት ሰውየው የሚቀጣው በመሰናዳቱ ወይም በመዘጋጀቱ ሳይሆን የፈጸመው ድርጊት በራሱ የሚያስቀጣ ከሆነ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ  ፈቃድ የሌለው የጣር መሣሪያ ድርጊቱን ለመፈጸም ቢያዝ ይህ በራሱ ወንጀል በመሆኑ ድርጊቱን ለመፈፀም በመዘጋጀቱ ሳይሆን ያለፍቃድ መሳሪያ በመያዙ ይቀጣል የጸረ-ሽብር ህጉ ግን ከላይ በአንቀፅ 4 ላይ እንደተመለከትነው መዘጋጀት ብቻውን ምንም ውጤት ባያመጣም የሚያስቀጣ መሆኑን ደንግጓል፡፡ የመሰናዳት ተግባር ከውጤት የራቀ በመሆኑ ግን ብቻውን ሊያስቀጣ ባልተገባ ነበር

2.    ያሴረ፡- ይህ በወንጀል ህጉ በአንቀፅ 38 ላይ ‹‹ ወንጀል ለማድረግ ማደም›› በሚል ርዕስ የተቀመጠው መሆኑ ነው፡፡ አንቀፅ 38 (1) ሁለት ወይም ብዙ ሰዎች ወንጀል ለማድረግ የተስማሙ እንደሆነ ስለወንጀል ተካፋይነት ቅጣትን ስለማክበድ የተጻፉት ድንጋጌዎች ተፈጻሚ ይሆኑባቸዋል ይላል፡፡ በመሆኑም የአንቀፁ ግልፅ አቋም ማንኛውም ወንጀል ለመፈፀም የተደረገ አድማ ወይም ሴራ ፈፃሚ እስካላገኘ ድረስ ራሱን የቻለ ወንጀል ተደርጎ አይቆጠርም የሚል ነው፡፡ ሆኖም ወንጀሉ ከተሞከረ ወይም ከተፈጸመ ግን ለዚህ ወንጀል ተደነገገው ቅጣት በወንጀል ህጉ ቁጥር 84 /መ/ ላይ ያለው የቅጣት ማክበጃ ተፈጻሚ ይንበታል፡፡

በተጨማሪም በወንጀል ህጉ አንቀጽ 478 ላይ በግልፅ እንደተቀመጠው አድማ ሊያስቀጣ የሚችለው በተግባር የተፈጸመ እንደሆነ ብቻ ነው፡፡ አንቀፅ 478 (1) ‹‹ ማንም ሰው ከአንድ በላይ ከሆኑ ሰዎች ጋር በመሆን በህዝብ ደህንነት ወይም ጤንነት ወይም በሰው ወይም በንብረት ላይ ከባድ ወንጀል ለመፈጸም ወይም ይህን ወንጀል ለማዘጋጀት ያደመ ወይም ሌላ ሰው በዚህ አድማ እንዲካፈል የገፋፋ እንደሆነና አድማው በተግባር የተገለፀ እንደሆነ እንደወንጀሉ አይነት ከስድስት ወር እስከ አምስት አመት ይቀጣል›› ስለሆነም አድማው በድርጊት እስካልተገለጸ ድረስ ለቅጣት ብቸና ምክንያት ሊሆን እንደማይችል ያሳያል፡፡ ይህንን ሀሳብ ረ/ፕሮፈሰር ጸሀይ ወዳ የወንጀል ህግ መሠረታዊ መርሆች በሚለው መፃፋቸው ላይ በግልጽ አስፍረውት ይገኛል፡፡ በመቀጠል ከህገመንግስቱ ጋር በግልጽ ስለሚጣረሱት የጸረ-ሽብሩ አንቀጾች እንመልከት በመጀመሪያም የፀረ-ሽብሩ ህግ አንቀጽ 14(1) (ሀ) ን እንመልከት

‹‹ በሽብርተኝነት ወንጀል የተጠረጠረን ሰው የስልክ፣ የፋክስ፣ የሬድዮ፣ የኢንተርት፣ የኤሌክሮኒክስ የፖስታና የመሳሰሉ ግንኙነቶችን ለመጥለፍ ወይም ለመከታተል ይችላል›› ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ የህገ-መንግስቱን አንቀጽ 26 (2) ‹‹ ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም በቴሌፎን በቴሌኮሙኒኬሽንና በኤሌኪትሮኒጅ መሣሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም›› ይላል ማንኛውም ተራ ሰው (ordinary person) ከላይ የተገለጹትን ሁለት አንቀጾች ብቻ  በማንበብ የጸረ ሽብር ህጉ የህገመንግስቱን አንቀጽ 26 (2) ምን ያህል ጨፍልቆ እንደሚያልፍ ይረዳል፡፡ እንቀጥል የፀረ-ሽብር ህጉ አንቀጽ 14 (1) ለናሐ
ለ‹‹ጠለፋውን ለማስፈጸም ወደ ማናቸውም ቤት ውስጥ በሚስጥር ለመግባት ወይም
ሐ‹‹ የህንኑ ለመፈጸም የሚያስችሉ መሳሪያዎችን ለማስቀመጥ ወይም ለማንሳት ይችላል›› ይላል

የህገመንግስቱን አንቀፅ 26 (1) ደግሞ እንመልከት

‹‹ ማንኛውም ሰው የግል ህይወት ግላዊነቱ የመከበር መብት አለው፡፡ ይህ መብቱ መኖሪያ ቤቱ ሰውነቱና ንብረቱን ከመመርመር እንዲሁም በግል ይዞታው ያለ ንብረት ከመያዝ የመጠበቅ መብትን ያካትታል›› የጸረ-ሽብር ህጉና የህገመንግስቱ አንቀጾች ምን ያህል እንደሚቃረኑ ሁለቱ አንቀጾች ግልጽ ማሳያ ናቸው፡፡ ይህ የሚያሳየው ኢህአዴግ እንደ አይኔ ብሌን እጠብቀዋለሁ የሚለውን ህገ-መንግስት እሱን እስከልጠቀመው ድረስ ግን ቀዶ ለመጣል ወደ ኋላ እንደማይል ነው፡፡ ይኸን ርእስ ተጨማሪ ሁለት አንቀጾችን ብቻ በማየት ለአሁን እንቋጭ

የጸረ-ሽብር ህጉ አንቀጽ 19 (1) ‹‹ በዚህ አዋጅ የተመለከተ የሽብርተኝነት ድርጊት ለመፈጸም ወይም እየፈጸመ ያለ ስለመሆኑ በሚገባ የሚጠረጠረውን ማንኛውንም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ፖሊስ ለመያዝ ይችላል››
ይህንን ከወንጀለኛ መቅጫ ስነስርአት ህግ ቁጥር 49 አንጻር ያለውን ተቃርኖ እንመልከት፡፡ የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ/ ቁ 49 ግልጽ የሆነ ሌላ ተቃራኒ ድንጋጌ ከሌለ በቀር ማንም ሰው ቢሆን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊያዝ ወይም ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በማረፊያ ቤት እንዲቆይ ለማድረግ አይቻልም ያለ ፍረድ ቤት ትእዛዝ የሚደረገው የሰው መያዝ በዚህ ክፍል በተመለከተው ሁኔታዎች መሰረት ብቻ ነው››( ያለፍ/ቤት ትዕዛዝ  ለመያዝ የሚልባቸውን ሁኔታዎች የወ/መ/ሕ/ሥ/ሥ በቁጥር 50-51 የዘረዘራቸው ሲሆን አንዲም ከያዝነው ጉዳይ ጋር አይገናኝም፡፡) እንግዲህ የኢህአዴግ ደንነቶችና ፌደራል ፖሊስ በዚህ አንቀጽ መሰረት ነው ወጣት የፓርቲ መሪዎችን ጋዜጠኞችንና ብሎ ገሮችን ከየመንገዱ ላይ ሰዋዊ ክብራቸውን በሚደፍር መልኩ አስፋልት ላይ እየጎተቱና እያዳፋ የሚወስዱት፡፡ የመጨረሻውን አንቀጽ እንመልከት የጸረ-ሽብር ህጉ አንቀጻ 21 ‹‹ ፖሊስ በሽብርተኝነት ወንጀል ጉዳይ የተጠረጠረ ሰው የእጅ ጹሁፍን፣ የጣት አሻራውን፣ ፎቶ ግራፉን፣ የጸጉሩን፣ የድምጹን፣ የደሙን፣ የምራቁንና ሌሎች በሰውነቱ የሚገኙ ፈሳሽ ነገሮችን ናሙናዎች ለምርመራ እንዲሰጥ ሊያዝ ይችላል፡፡ በተጨማሪም የህክምና ምርመራ እንዲያደርግ ሊያዝ ይችላል ተጠርጣሪው ለምርመራው ፈቃደኛ ካልሆነ ፖሊስ አስፈላጊ የሆነ ተመጣጣኝ ሀይል ተጠቅሞ ከተጠርጣሪው ናሙና ሊወስድ ይችላል›› (ሰረዝ የተጨመረ)
የህገ-መንግስቱ አንቀጽ 19(5) ደግሞ ይህን ይላል‹‹ የተያዙ ሰዎች በራሳቸው ላይ በማስረጃነት ሊቀርብ የሚችል የእምነት ቃል እንዲሰጡ ወይም ማናቸውንም ማስረጃ እንዲያምኑ አይገደድም፡፡ በማስገደድ የተገኘ ማስረጃ ተቀባይነት አይኖረውም›› (ሰረዝ የተጨመረ)

ህወሐት/ ኢህአዴግ አስከብረዋለው እገዛለታለሁ የሚለውን ሕገ-መንግስት እንኳን ተቀናቃኞቹን ለማጥፋት መሰዋት ለማድረግ በፍጹም እንማያንገራግር ከላይ የተጠቀሱት አንቀጾች ብቻ በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በህገ-መንግስቱ አንቀጽ 9 (1) ላይ በግልጽ የተቀመጠውን ህገ-መንግስቱን የበላይ ሕግ ነው ማንኛውም ህግ ልማዳዊ አሰራር እንዲሁም የመንግስት አካል ወይም ባለስልጣን ወሳኔ በዚህ ህገ-መንግስት ጋር የሚቃረን ከሆነ ተፈጻሚነት አይኖረውም የሚለው አንቀጽ ይህን የጸረ ሽብር ህግ ያረቀቁ አካላት አያቁትም ማለት ባይቻልም ሆነ ብለው ያለቆቻቸውን ሀሳብና የኢህአዴግን ህልውና እስካስጠበቀ ድረስ ቢሻር ምን ችግር አለው ብለዋል፡፡ ይህ ግን ዛሬ ባያስጠይቅም ነገ ግን አርቃቂውንም ሆነ አጽዳቂውን ከተጠያቂነት አያድንም

በመጨረሻም መፍትሄው ምንድን ነው?
መፍትሄው አንድና አንድ ብቻ ነው ይህ ህግ እዚህ ሀገር ላይ በተግባራዊነቱ እስከቀጠለ ድረስ ቢሮ ከፍተውና ከምርጫ ቦርድ ፍቃድ ወስደው በጠንካራ አደረጃጀት ላይ ቁመው በሰላማዊ መንገድ የሚታገሉ ፓርቲዎች ጠንካራ አባላትና አመራር እንዲሁም ኢህአዴግን በብዕራቸው የሚሞግቱ ጸሀፍትና ጋዜጠኞች በማንኛውም ሰዓትና በየትኛው ምክንያት ከዚህ አንቀጽ ውስጥ አንዱ እየተጠቀሰባቸው ወደ ኢህአዴግ ማጉሪያ ካምፕ መወርወራቸው የማይቀር መሆኑ ነው፡፡ ስለዚህም የጸረ-ሽብር አዋጁ አንቀጾች ህጉ በሚፈቅደው መሰረት እንዲቀየሩ ወይም እንዲሻሻሉ ሁሉም ያገባኛል የሚል አካል በአንድ ላይ መጮህ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነና ኢህአዴግም ይህን አፋኝ ህግ ለማሻሻልም ሆነ ለመቀየር ተነሳሽነት ካላሳየ እንዲሁም በሰሞኑ የማሰር ዘመቻው ከቀጠለ ወይ እስር ቤቶቹ ካልሞሉ ወይ እነሱ ማሰር ካልሰለቻቸው በስተቀር የሚተርፍ ጠንካራ የፖለቲካ አመራርና ጋዜጠኛ የሚኖር አይመስልም፡፡ እስር ቤቶች እንደማይሞሉ እነሱም ማሰር እንደማይሰለቻቸው እናውቃለን፡፡ እኛስ መታሰር ይሰለቸን ይሆን? አይመስለኝም፡፡