‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከባድ ማጥ ውስጥ ነው›› አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የኢዴፓ ሊቀመንበር

ምንጭ ሪፖርተር

ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ በአገሪቱ የተከሰተው የኑሮ ውድነት በከፍተኛ ደረጃ እየተባባሰ ቀጥሏል፡፡ የተለያዩ ምሁራንና የመንግሥት ባለሥልጣናት የግሽበቱ ምንጭ ምንድነው? በሚለው ጉዳይ ላይ የየራሳቸውን ማብራሪያ ሲሰጡ ቆይተዋል፡፡
ኃይሌ ሙሉ ‹‹የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ታሟል›› ከሚሉት ከኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ ጋር በግሽበቱና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁን ወቅት በአገሪቱ ያለውን ግሽበት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ሙሼ፡- በሁለት መንገድ መግለጽ ይቻላል ብዬ ነው የማስበው፡፡ አንደኛው ዓለም አቀፍ መግባባት የተደረሰበት በቁጥር የምንገልጸው አስር፣ አሥራ አምስትና ሃያ ፐርሰንት የምንለው ነገር ነው፡፡ እንግዲህ ያንን ስንወስድ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በተለይ በዚህ ወርና ባለፈው ወር ያለው ግሽበት ወደ አርባ ፐርሰንት አሻቅቧል፡፡ ያ ማለት በመግዛት አቅማችን ላይ አርባ ፐርሰንት ቅናሽ ታይቷል ማለት ነው፡፡ ይኼ ቁጥሩ ነው፡፡ ለአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማኅበረሰብ ትክክለኛ ገለጻ ነው ወይ ስንል? አይደለም፡፡ ቁጥሩ በሕይወቱ ላይ ምን ያህል ጉዳት እንዳደረሰበት የሚያሳይ አይደለም፡፡ በሕዝቡ በውስጡ ያለውን ስቃይና መከራ የሚገልጽ አይመስለኝም፡፡ ሁለተኛው መገለጫ መንገድ ደግሞ እኛው ራሳችንን እንደ አንድ ተጠቃሚ የምናይበት መንገድ ነው፡፡ ያለው አቅርቦት ፍጹም አስተማማኝ አይደለም፡፡ የአቅርቦት መጥፋት ብቻ ሳይሆን ጥራት ፈጽሞ የጎደለበት፣ ሚዛን የተዛባበትና የግብይት ሥርዓቱ የተናጋበት ሁኔተ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ የምርቶች ዋጋ በአንድ ዲጂት ሳይሆን በሁለትና በሦስት ዲጂት አድጓል፡፡ አንድ ብር ስንገዛው የነበረውን ነገር በሚቀጥለው ቀን አምስትና ስድስት ብር የምንገዛበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ በጥቅሉ ስናየው የግብይት ሥርዓቱ ተናግቷል፡፡ አቅርቦቱ ተናግቷል፡፡ የዋጋ ንረቱ ይህ ነው ተብሎ ሊገለጽ የሚችል አይደለም፡፡ የኢትዮጰያ ኢኮኖሚ ከባድ የሆነ ማጥ ውስጥ ነው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የግሽበቱ ዋና ምንጮች ምንድናቸው? አቀጣጣዮቹስ?

አቶ ሙሼ፡- ግሽበቱን በሚመለከት መሠረታዊ ምንጮች የምንላቸው ነገሮች ሦስትና አራት አካባቢ ይሆናሉ፡፡ አቀጣጣይ የምንላቸውም እንዲሁ ሁለት፣ ሦስት ይሆናሉ፡፡ ይኼ ችግር በአንድ ቀን ድንገት የተከሰተ አይደለም፡፡ ዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ማኅበራትን ጨምሮ ያገባናል የሚሉ አካላት ሲገልጹ እንደቆዩት፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግሽበት እያደገ የመጣው እ.ኤ.አ ከ2008 ጀምሮ ነው፡፡ ያ ግሽበት የራሱ መነሻ አለው፡፡ በዚያ ወቅት መንግሥት ያካሂደው የነበረው የመሠረተ ልማት ግንባታ ከፍተኛ እየሆነ የመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ አንደኛውና መሠረታዊ ችግር መንግሥት በዚህ መሠረተ ልማት ላይ የሚያወጣው ገንዘብ ነው፡፡ ያ ገንዘብ ደግሞ ከአገር ኢኮኖሚ ጋር የማይመጣጠንና የሚደጋገፍ አልነበረም፡፡ መንግሥት ይህንን የመሠረተ ልማት ግንባታ የሚያሟላው በአንድ በኩል በመበደር፣ በሌላ በኩል ደግሞ በቁጠባ መልክ የተቀመጠውን ገንዘብ መጠቀም ነው፡፡ ሁለቱ የመንግሥት የብድር ምንጮች ዓለም አቀፍ ተቋማትና የአገር ውስጥ ኢኮኖሚ ናቸው፡፡ ከአገር ውስጥ የሚያገኘው ብድር ገንዘብን ከማተም ጀምሮ በባንክ ውስጥ እስከመጠቀም ይደርሳል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በከፍተኛ ደረጃ ሲካሄዱ ወደ ኢኮኖሚ የሚገባው ገንዘብ በመጀመሪያ ደረጃ የሚያጠቃው በዝቅተኛ አቅርቦት ላይ ያለውን ፍጆታ ነው፡፡ ምክንያቱም ማኅበረሰቡ ከዚህ በፊት ያልነበረውን የመግዛት አቅም እንዲያገኝ ነው የምታደርገው፡፡ አዲስ ደመወዝ ተከፋይ ማኅበረሰብ ነው የምትፈጥረው፡፡ አዲስ የገንዘብ አቅም ኢኮኖሚ ውስጥ ነው የምታስገባው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ተመጣጣኝ በሆነ ደረጃ አቅርቦቱ እያደገ አይደለም፡፡ አቅርቦቱ ባላደገበት ሁኔታ ብዙ ገንዘብ ጥቂት አቅርቦትን ያሳድዳል፡፡ ያ ውድድር የዋጋ ግሽበትንና ንረትን ያመጣል፡፡ በእኛ እምነት የግሽበቱ መሠረታዊ ችግሩ ይኼ ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ መንግሥት እንደ መንግሥት ሥራውን ለመሥራት የሚያደርገው እንቅስቃሴ ቀላል አይደለም፡፡ ገንዘብ ይጠይቃል፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጀቱን ብናየው በጣም እያደገ ነው የመጣው፡፡ ይህች አገር እያደገ ያለውን በጀት የመሸከም አቅም የላትም፡፡ የአገሪቷ ኢኮኖሚ እጅግ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ስላለ ትንሽ የገንዘብ አቅም መጨመር ወይም ደግሞ የገንዘብ ሥርጭቱ ማደግ ፈጣን የሆነ ግሽበት ነው የሚያስከትለው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ መነሳት የሚገባው ነገር መንግሥት በፖሊሲ የሚደግፋቸው ማዕከሎች አትራፊ እንዳልሆኑ እየታወቁ ድጋፉ እንዲቀጥል መደረጉ ኢኮኖሚውን እንዲወድቅ ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ አሁን በግብርና ላይ እየተሠራ ያለውን ነገር ማየት እንችላለን፤ ለግብርና ድጋፍ መስጠቱ ስህተት ነው ማለቴ አይደለም፡፡ ነገር ግን የሚወጣው ገንዘብ ኢኮኖሚውን የሚመጥን አይደለም፡፡ አንድ አርሶ አደር በተሰጠው የመሬት ይዞታ ላይ የተለያዩ ግብዓቶችንና የተለያዩ ወጪዎችን ጨምሮ ከዚያ መሬት ማምረት የሚችለው ነገር ኢኮኖሚውን በሚፈለግበት ደረጃ የሚያደርስ አይደለም፡፡ ያ ገንዘብ በአቅርቦት ካልተደገፈ ግሽበትን ያስከትላል፡፡ መንግሥት በመሠረተ ልማትና በሕዝብ ኢንቨስትመንት ላይ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመደገፍ ማንኛውንም ዓይነት ገንዘብ የማግኘት ፍላጐቱ ሰፍቷል፡፡ ሁሉንም የገንዘብ ማግኛ መንገድ ይጠቀማል፡፡ ከነዚያ መንገዶች አንዱ ቫት ነው፡፡ የመንግሥትን ገቢ ለመጨመር ዕድል ከሚሰጡ ተጨባጭ ሁኔታዎች አንዱ ይኼ ነው፡፡ ቫት በተፈጥሮው ተከታታይ የሆነ ዋጋን የመጨመር ባህሪ አለው፡፡ እንደኛ ባለ ፈጽሞ ኋላቀር የግብይት ሥርዓት ውስጥ ተፅዕኖው ከባድ ነው፡፡ ምርቱ ወደ ገበያ ከሚወጣበት ቀን ጀምሮ ተጠራቅሞ አምስት ስድስት ጊዜ ቫት ይጨመርበታል፡፡ በአንድ ምርት ላይ ተደራራቢ የሆኑ ታክሶች ሲጨመሩበት መጨረሻ ላይ ዋጋው በጣም ከፍተኛ ይሆናል፡፡ ይኼ ደግሞ የዋጋ ግሽበት ያመጣል፡፡ የማኅበረሰቡን የመግዛት አቅም ይሻማል፡፡ ይኼ ደግሞ የግብይት ሥርዓቱን ያናጋዋል፡፡ አቅርቦትን ያናጋዋል፡፡ ግሽበትን ያስከትላል፡፡ እነዚህ ሦስቱ መሠረታዊ የግሽበት ምንጮች ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- መንግሥት ለሚያካሂደው የልማት ሥራ በዚህ መልኩ ገንዘብ ካልሰበሰበ ከየት ያገኛል?

አቶ ሙሼ፡- መንግሥት የገቢ ምንጮቹ ብዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ድንገተኛ በሆኑ ጊዜዎች የተለያዩ ታክሶችን ይጥላል፡፡ ሱር ታክስ ይጥላል፡፡ የተስተካከለ የገበያ ሥርዓት በሌለበት ሁኔታ ከቫት ገቢ ለመሰብሰብ መሞከር የዋጋውን ግሽበት ቀጥተኛ በሆነ መንገድ ማባሳስ ነው፡፡ መንግሥት የሚያይበት መንገድ ነው ስህተቱ፡፡ እኔ እንዴት አድርጌ ልሥራ? ብለህ ጥያቄ ማንሳትና ምንም ቢሆን ገንዘብ ማግኘት አለብኝ ብለህ ማሰብ ይለያያል፡፡ መሠረተ ልማትን ለመገንባት ገንዘብ ያስፈልገኛል፡፡ ገንዘብ ካስፈለገኝ ደግሞ በምንም መንገድ ገንዘብ ማግኘት አለብኝ ነው የሚለው መንግሥት፡፡ ይኼ ደግሞ የኢኮኖሚ ሥርዓት መለኪያ ሊሆን አይችልም፡፡ መንግሥት የመሠረተ ልማት ግንባታው የዋጋ ግሽበት በማያስከትል መልኩ መሥራት አለበት፡፡ ሁላችንም ኢትዮጵያ ኒውዮርክ እንድትሆን እንመኛለን ግን አንችልም፡፡ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተጨባጭ ሁኔታ ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ አትራፊ አይደለም፡፡ ከተሞች ደግሞ በተመጣጣኝ ደረጃ ማደግ ነው ያለባቸው፡፡ በተመጣጣኝ ሁኔታ ማደግ አለመቻላቸው ግልጽ በሆነ መንገድ ግሽበት እያስከተለ ነው፡፡ እኛ በሒደት የሚመጣ ዕድገት ነው የምንፈልገው፡፡ ቫትም ቢሆን ከዝቅተኛ የቫት ደረጃ ተነስተህ የገበያ ሥርዓቱን እያረምክና እያስተካከልክ የቫት መጠንን እየጨመርክ ብትመጣ፣ ከግንዛቤ ጋር ስለሚመጣ ውጤት ያስገኛል፡፡ አለበለዚያ ጠቅላላ ሥርዓቱን ነው የምታዛባው፡፡

ሪፖርተር፡- ግሽበቱን ያቀጣጠሉት ነገሮች ምንድናቸው?

አቶ ሙሼ፡- አቀጣጣዮቹ ነገሮች ሦስት ናቸው ብዬ ልወስዳቸው እችላለሁ፡፡ አንደኛው በመንግሥት ውስጥ የሚታየው የብቃት ጉድለትና ብክነት ነው፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የመንግሥት ብክነት ብትመለከተው ከመጠን በላይ የገዘፈ ነው፡፡ ሁለተኛ መንግሥት ብቁ አይደለም፡፡ በየዓመቱ አዳዲስና ዘመናዊ የሆኑ መኪና፣ የቤት ቁሳቁሶች፣ ኮምፒዩተሮችና አክሰሰሪዎች ይገዛል፡፡ እነዚህን ነገሮች መንግሥት ብቁ በሆነ መንገድ ሊጠቀምበት የሚያስችል ዘዴ የለውም ወይ ነው? ጥያቄው፡፡ ወጪ ቆጣቢ መሆን አለብን፡፡ መንግሥት የሚሰበስበው ገንዘብ ወይም ወደ ኢኮኖሚ የሚያስገባው ነገር ሁልጊዜም ተፅዕኖ ስላለው ብክነትን መቆጣጠር አለበት፡፡ ሌላው አቀጣጣይ ነገር ሙስና ነው፡፡ ሙስና የመንግሥት መገለጫ ሆኗል፡፡ መንገዶች ሁለት ሦስት ጊዜ ሲሠሩ እናያለን፡፡ አንድ ጊዜ የተጀመረ መንገድ ሳይጠናቀቅ ዓመት ቆይቶ እንደገና ሲፈርስና ሲናድ እናያለን፡፡ ድልድዮች እንደገና ሲገነቡ፣ ትልልቅ የኤሌክትሪክ ግንባታዎችና ግድቦች ከተሠሩ በኋላ እንደገና ተጨማሪ ወጪ ሲጠይቁ እናያለን፡፡ እነዚህ ነገሮች ግሽበትን ያባብሳሉ፡፡

ሪፖተር፡- መንግሥት በቅርቡ ወስዶት የነበረው የዋጋ ተመን ያስከተለው ችግር አለ?

አቶ ሙሼ፡- የዋጋ ቁጥጥሩ ኖሮ መንግሥት ላይ መተማመን የምትችልበትም ሁኔታ ሊኖር ይገባል፡፡ በተለይ ነጋዴው ማኅበረሰብ በመንግሥት ላይ እምነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ኢኮኖሚውን ለማስተካከል ዕርምጃ ልትወስድ ትችላለህ፡፡ ግን ዕርምጃው አስደንጋጭና የሚረብሽ መሆን የለበትም፡፡ መንግሥት ሁሉም ነጋዴ ቫት ከፋይ እንዲሆን ለማድረግ ሲንቀሳቀስ፣ ነጋዴው ማኅበረሰብ የንግድ ፈቃዱን በመመለስ ከንግድ ግብይት ሥርዓቱ ውስጥ ለመውጣትና ለመግባት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ ራሱን ሲሰበስብ፣ በግብይት ሥርዓት ውስጥ የዕቃ አቅርቦት ችግር ተፈጠረ፡፡ ይህ ሳያንስ እንደገና መንግሥት የመረጋጋት አዝማሚያ የሚያሳየውን ኢኮኖሚ ጠልፎ ገብቶ የዋጋ ተመን ጣለ፡፡ የዋጋ ተመኑ ደግሞ እጅግ አሳዛኝ የሆነ በመንግሥት የማይገመት ባህሪ ነበረው፡፡ ሦስት ጊዜ ነው የዋጋ ተመን የጣለው፡፡ በመጀመሪያ የዋጋ ተመን አወጣ፡፡ ወደቀ፡፡ ሁለተኛ ዋጋ እንደገና አወጣ ይህም ወደቀ፡፡ ከዛ ቀጥ ብሎ ከነጋዴው ጋር አብሮ ትመና ውስጥ ገባ፡፡ በመጨረሻ ላይ ባልሆነ መንገድ ገበያውን እያናጋህ ነው የተባለውን ነጋዴ የዚህ ጉዳይ አካል አደረገው፡፡ ከነጋዴው ጋር መነጋገሩ አይደለም ስህተቱ፡፡ ግን በጥርጣሬ ስታየው የነበረውን ነጋዴ እቆጣጠራለሁ ብለህ መቆጣጠር አቅቶህ እንደገና ደግሞ የዚሁ ቁጥጥር አካል አድርገህ አብረን እንሠራለን ማለት ስትጀምር መጀመሪያ የተነሳህበትን ነገር ያናጋዋል፡፡ ይህ ሁኔታ የንግዱን ማኅበረሰብ ዋጋ ይጨምራል የሚል መላምት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ አሁን ለምሳሌ ዘይት እንደ ኮካ ኮላ ካልሆነ ሱቅ ገዝተህ ጠጥተህ የምትጨርሰው ነገር አይደለም፡፡ መንግሥት ዘይት ማስገባት ከጀመረ ወር ሞላ፡፡ ሰማንያ ሚሊዮን ሊትር እያስመጣሁ ነው ብሏል፡፡ ይህ ዘይት አሁን በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘይት ፍጆታ መጠን ሲለካ ከአንድ ወር ወይም ከሁለት ወር በላይ ማቆየት ይቻላል፡፡ ነገር ግን አሁንም የዘይት እጥረት አለ፡፡ ይህ የሆነው ሕዝቡም ነጋዴውም መገመት ስለጀመረ ነው፡፡ ገማች እንዲሆን ያደረገው የመንግሥት ዕርምጃ ነው፡፡ ከአንድ ወር ወይም ከሁለት ወር በኋላ ዘይት መምጣት ያቆማል ብሎ ያስባል፡፡ ነጋዴው ለማትረፍ ተጠቃሚው ደግሞ መንግሥት ዘይት ማስመጣት ሲያቆም ነጋዴው ማኅበረሰብ ይጫወትብኛል፣ አንድ ሊትር ዘይት በስልሳ እና በሰባ ብር ይሸጥልኛል ብሎ ስለሚስብ፣ ዘይት እየገዛ ሊያስቀምጥ ይችላል፡፡ ሸማቹም ሆነ ነጋዴው በመንግሥት ላይ እምነት የለውም፡፡

ሪፖርተር፡- እየተገነቡ ያሉት መሠረተ ልማቶች በተለይም የመንገድ ግንባታዎች ለክልሎች የኢኮኖሚ ትስስር ጠቀሜታ እንዳላቸው መንግሥት ይገልጻል፡፡

አቶ ሙሼ፡- መንግሥት ሁልጊዜ ምርጫው የጥቁርና የነጭ ፖሊሲ ነው፡፡ ወይ ነው ወይ አይደለም ነው፡፡ ነገር ግን ዓለም በዚህ መንገድ አይሠራም፡፡ ምክንያቱም ሁሉም ነገር ሚዛናዊና አንጻራዊ ነው፡፡ ኢኮኖሚውን ለማሳደግና ለማስተሳሰር ያስፈልጋል፡፡ ነገር ግን ወቅታዊ ነው ወይ? አቅምን ያገናዘበ ነው ወይ? ሌሎች ተያያዥና ተከታታይነት ያላቸው ጉዳዮች የኢኮኖሚ ችግሮችን አይፈጥሩም ወይ? ያንን ትኩረት ሳትሰጥ መንገድ መሥራት የለብህም፡፡ አንዳንዴ ኢሕአዴግ ከሚለውም ያልፋል፡፡ በመሠረተ ልማት ላይ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች አንዳንድ ጊዜ ፕሮፓጋንዳ ነው የሚመስሉት፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶቹ ከተሠሩ በኋላ በሚቀጥለው ሁለትና ሦስት ዓመታት ያቆማሉ፡፡ የኤለክትሪክ ግድቦችን ብናያቸው አሁንም ድረስ በሙሉ አቅምና ጉልበት እያመነጩ አይደሉም፡፡ የሐዋሳ መንገድ ቅርብ ነው፡፡ የረጅም ዘመን መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን በዚያ መንገድ ላይ የሚተላለፉት መኪኖች ቢቆጠሩ እውነቴን ነው የምልህ በናዝሬትና በአሰብ መካከል የሚተላለፉትን ያህል ሊያክሉ አይችሉም፡፡ ያ የሚያሳየው የተወሰኑ መንገዶች ላይ ያዋልከውን ኢንቨስትመንት ሳትጠቀምበት ከቅጥም ውጭ እንደሚሆን ነው፡፡ መኪና ሳይሄድበትና የሚፈለገውን ግብ ሳይመታ ዝም ብሎ የማዳረስ ሁኔታ ነው ያለው፡፡ እስቲ መንገድ እናዳርስ፣ መንገድ ያላዩ አካባቢዎችን መንገድ እንስጣቸው ከሚል መንፈስ የምትሠራው ነገር ቅድም እንዳልኩት ውድቀት አለው፡፡ በተጠና መንገድ አሁን እንደተባለው የንግድ ፕሮጀክቶችን ከአንድ ክልል ወደ ሌላ ክልል፣ ከዚያ ክልል ደግሞ ወደ ውጪ ለማስወጣት የሚያስገድዱ ሁኔታዎች ካሉ፣ ያንን መንገድ ሠርተን ከንግድ እንቅስቃሴ በሚገኘው ገቢ ሌሎቹን የማዳረስ ሥራ መሥራቱ ችግር የለውም፡፡ ክልሎች የራሳቸው አቅምና ጥያቄ አላቸው፡፡ አንድ ክልል በጣም ትልቅ ፕሮጀክት ሊኖረው ይችላል፡፡ በዚያ ክልል መንገድና የመሳሰሉትን መሠረተ ልማቶች ስትሠራ ሌላው ክልል ለኔም ይሠራልኝ ብሎ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ያንን የፖለቲካ ጥያቄ ለመመለስ ስትል የምታደርገው እንቅስቃሴ ግሽበት ያስከትላል፡፡ ይህ መንግሥት በጠቅላላው በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚከተለው የፌዴራል አወቃቀር ችግር የሚመጣ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት አሁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ጉልበት አግኝቼ በሰው ዘንድ ተደማጭ እየሆንኩ የመጣሁት ይህን የመሠረተ ልማት ሥራ ከጀመርኩ በኋላ ነው ብሎ ስለሚያምን እስካሁን ድረስ ጉዳቱን አይደለም የሚያስበው፡፡ ብዙ መንገዶችን ያየንበት ዕድል መፈጠሩ እርግጥ ነው፡፡ ነገር ግን የመብላት አቅማችን እየተሸረሸረ የመኖር ሕልውናችን አደጋ ላይ የሚወድቅበት ሁኔታ መፈጠር የለበትም፡፡ ኢዴፓ ደጋግሞ በዚህ ጉዳይ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ መሠረተ ልማት ላይ የሚደረገው የግንባታ ርብርብ ኢኮኖሚውን ከሚገባው በላይ እያጋለው ነው፡፡ መጨረሻ ላይ የሚከሰተውን የዋጋ ግሽበት ልንቆጣጠረው አንችልም ስንል ቆይተናል፡፡ መንግሥት እንዳልኩህ አይሥራ እያልን አይደለም፡፡ ዋናው ተግባሩ ይኼው ነው፡፡ እንዲያውም መንግሥት ከጥቃቅን ነገሮች እጁን አውጥቶ በእንደዚህ ያሉ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር ነው የምንፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- አሁን የዋጋ ግሽበት ባለበት ሁኔታ መንግሥት ለሚቀጥለው ዓመት 117 ቢሊዮን ብር በጀት ይዟል፡፡ አንዳንዶች ይህንን በጀት እሳት ላይ ነዳጅ እንደማርከፍከፍ ነው ይላሉ፡፡ እርስዎ እንዴት ነው የሚያዩት?

አቶ ሙሼ፡- ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ በእርግጥ ምንድነው ይኼ በጀት በአንጻራዊነት አገሪቱ ከተከሰተባት የዋጋ ግሽበት አኳያ ብታወዳድረው የሚታዩ ነገሮች አሉ፡፡ የመንግሥት በጀት ገንዘብ ግሽበት ሲመታው በጀቱም በተመጣጣኝ ሁኔታ ማደግ ይጠበቅበታል፡፡ እኔ አሁን ስጋቴ ቁጥር ብቻ የሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት አለበት አይደለም፡፡ ይህንን ገንዘብ ከየት ነው የሚያመጣው? እንዴት ነው የሚያገኘው? እንደሚባለው ወይም እንደምሰማው ብዙ ሰዎች የንግድ ፈቃዳቸውን እየመለሱ ነው፡፡ አቅርቦት እንደምታየው ተመናምኗል፡፡ ነጋዴውም ማኅበረሰብ ስጋት ስላደረበት እጁን ሰብስቧል፡፡ ይህ ማለት በመንግሥት ገቢ ላይ ትርጉም ያለው ጫና ያመጣል፡፡ ይኼ ከሆነ ደግሞ መንግሥት ከፍተኛ ወለድ ወደሚያስከፍሉ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ሊሄድ ነው፡፡ ወይም ደግሞ አገር ውስጥ ገንዘብ በማተም ያንን ነገር ለማሟላት ይሞክራል፤ አለበለዚያም አዳዲስ የግብር ዘዴዎችን ይተገብራል ማለት ነው፡፡ ይኼ በማኅበረሰብ ላይ የሚያስከትለውና የሚፈጥረው ጫና ቀላል አይሆንም፡፡ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ያደርገዋል፡፡ መንግሥት በጀት አይመድብ አይደለም ሁሌ ክርክሩ፡፡ ይኼ አይደለም ጥያቄው፡፡ መንግሥት ያለበጀት እንደማይኖር ማንም ዜጋ ያውቃል፡፡ እንኳን እኛ አይደለንም ትምህርት ቤት ገብተን የወጣን ሰዎች ትምህርት ቤት ያልገባው አርሶ አደርም ቢሆን ያውቃል፡፡ ግን የሚበጀተው በጀት ማኅበረሰቡ ወደፊት ሃያና ሰላሳ ዓመት ሊጠቀምበት የሚችለውን ነገር ብቻ አይደለም ታሳቢ ማድረግ ያለበት፡፡ ትውልድ ወደፊት ተጠቃሚ የሚሆንበትን ነገር ማመቻቸት አስፈላጊ ነው፡፡ ግን መሠረቱ ማን ነው? አሁን ያለው ሰው የመኖር ህልውናው አደጋ ላይ ወድቋል፡፡ አነሰም በዛም በዚህም መካከል የአንድ ኢኮኖሚ መዛባት ማኅበራዊ ቀውስ ያስከትላል፡፡ ተፈናቅሎ በረንዳ አዳሪ መሆን፣ ጐዳና ተዳዳሪ መሆን፣ ሌብነት፣ ውንብድናና ዘረፋ የመሳሰሉት ማኅበራዊ ቀውሶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ተከትሎ ደግሞ ማኅበረሰቡ ጥያቄ ያነሳል፡፡ ያ ደግሞ መረጋጋትን ያጠፋል፡፡ ከአመፅ፣ ከግርግርና ከብጥብጥ የሚመጣ ነገር አለ ብለን አናምንም፡፡ መንግሥት ኢኮኖሚውን ማሻሻል አለበት ብለን ነው የምናምነው፡፡

ሪፖርተር፡- እንግዲህ ከጥቅምት ወር ጀምሮ መንግሥት የተለያዩ ዕርምጃዎችን ወስዷል፡፡ የዋጋ ቁጥጥር፣ የገንዘብ ምንዛሪ መቀነስና ከእነዚህ ዕርምጃዎች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ግሽበቱ ግን አሁንም ተባብሷል፡፡ ሁኔታው ወዴት እያመራ ነው?

አቶ ሙሼ፡- በጣም ጥሩ ጥያቄ ነው፡፡ ሁለት ነገሮች ናቸው ለዚህ ምክንያት ናቸው ብለን የምናስበው፡፡ እነዚህ ውሳኔዎች የሚመነጩት ከአንድ አስተሳሰብ መሆናቸው ነው፡፡ ከዛም አልፎ ከአንድ ግለሰብም ሊሆን ይችላል፡፡ ይኼ ሁልጊዜ በራሱ ችግር አለው፡፡ ምክንያቱም የኢኮኖሚ ውስብስብ ችግሮችን ከመጽሐፍ አውርደህ ወደ መሬት ስታመጣቸው ተጨባጭ ሁኔታን ይጠይቃሉ፡፡ አዳዲስ ሐሳቦችን መጠቀም አዳዲስ ዘዴዎችን መከተል ይጠይቃሉ፡፡ ጉዳዮችን በቅጡ ተመልክቶ መሠረት እንዲይዝ ለማድረግ የሚችል የተለየ ኃይል መፈጠር አለበት፡፡ አንድ ውሳኔ ስትወስን ያ ውሳኔ ከግብ መድረሱን ማረጋገጥ ግዴታ መሆኑን አብሮ መታሰብ አለበት፡፡ ሁልጊዜ የኢትዮጵያ ችግር ይኼ ነው፡፡ የዋጋ ተመኑ ተጀመረ ጣጣ ሲበዛበት ተቋረጠ፤ ሲቋረጥም ችግሩ ተስተካክሎ አልነበረም፡፡ እንዲያውም አንገጫግጮናል፡፡ መንግሥት ፖሊሲ ይቀይሳል፤ ፖሊሲው ወቅታዊ ችግርን ከመፍታት አኳያ ደግሞ ያንን ችግር መፍታትና አለመፍታቱ ሳይረጋገጥ በጫጫታና በግርግር ይሞከርና አልሆን ሲል ይቀራል፡፡ ያ ውጤት አያመጣም፡፡ ምንድን ነበር የሠራነው? ምንስ ችግር ገመጠን? ምንስ አጥፍተናል ብለህ ካልፈተሽክ ወደፊት መሄድ አትችልም፡፡ የዋጋ ተመኑ ለምን ተጀመረ? በመሃል ላይ ምን ዓይነት ፈተና ገጠመው? ለምን አልተሳካም? ወደፊትም ይኼ ነገር እንዳይደገም ብለህ አቅጣጫ ካልፈጠርክ ችግሩ ተመልሶ አዲስ ሆኖ ይወጣል፡፡ ዛሬ ይወሰናል፣ ተግባራዊ ይሆናል፣ አይሠራም ይረሳል፣ ከአምስት ዓመት በኋላ ደግሞ እንደገና ይመጣል፡፡ እኔ ገምቼ የነበረው የዋጋ ተመኑ ሳይሠራ ሲቀር፣ ከየት አገር ተሞክሮ እንደተወሰደ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ለምን እንዳልሠራ፣ ጥፋተኛ ማን እንደሆነ ይገለጻል የሚል ነበር፡፡ ይኼ ነገር እንዳይደገምስ ምን እንሥራ እያልክ ሥርዓት ባለው መንገድ እንደ መንግሥት የማታይ ከሆነ፣ ሁልጊዜ ወቅታዊ ችግሮችን ፈቺ ነው የምትሆነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ተጨባጭ ችግርም ይኼው ነው፡፡ ከዓመት ወደ ዓመት አንድ ዓይነት ችግሮች ናቸው የሚታዩት፡፡ በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ደግሞ ይደገማሉ፡፡ መንግሥት እየተከራከረ ያለው የዋጋ ተመኑ ችግር የለበትም በሚል ነው፡፡ ነገም ይደግመዋል ማለት ነው፡፡ በመንግሥት ላይ መተማማን አይቻልም፡፡ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ ነጋዴው ማኅበረሰብ የሚሠራው ለትርፍ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እንደሚለው ኪራይ ሰብሳቢ አይደለም፡፡ ኪራይ ሰበሳቢ የሚባለው በሶሻሊዝም ጽንሰ ሐሳብ ነው፡፡ ኪራይ ሰብሳቢት እንዳይፈጠር መንግሥት ራሱ ነው መታገል ያለበት፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ እያሉ ነጋዴዎች ከገበያ እንዲጠፉ ማድረግ አይደለም መፍትሔው፡፡ አንዳንድ ጊዜ መንግሥት ነጋዴዎች ልክ እንደጉንዳን ተሰልፈው በአንድ አቅጣጫ እንዲዘምቱ ይፈልጋል፡፡ እንዲህ ማድረግ አይቻልም፡፡ የሰው ልጅ የተሰጠውን የማሰብ፣ የመነገድና የማትረፍ ነፃነት ስትጠብቅለት ሊሰለፍልህ አይችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የበጀት ጉድለት አለ፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ከውጭ ይገኛል ተብሎ ታስቦ ከነበረው የገንዘብ ድጋፍ 43 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው ማግኘት የተቻለው፡፡ በሚቀጥለው ዓመትም ደግሞ ከውጭ ብዙ ይገኛል ተብሎ ብዙ ዕቅድ ተይዟል፡፡ ይኼ ገንዘብ ቀደም ብሎ አልተገኘም፡፡ ምናልባት ሰኔና ግንቦት አካባቢ ዘግይቶ ሊገኝ ይችላል ተብሏል፡፡ ይህንን የመንግሥት ዕቅድ እንዴት ያዩታል?

አቶ ሙሼ፡- በጀት የሚነሳው ከዚህ ነው፡፡ የማታገኘውን በጀት መበጀት ምን አመጣው? መንግሥት ግን ካለው ጉጉትና ከየትም መገኘት አለበት ከሚል መንፈስ የመንቀሳቀስ አዝማሚያ ነው ያለው፡፡ በየትኛውም መንገድ ብቻ ገንዘቡ ይምጣ ነው የሚለው፡፡ እኔ ችግሩ የዚሁ ውጤት ነው የሚመስለኝ፡፡ መንገዱ መሠራት አለበት፡፡ የፖለቲካ ጥቅሜ መረጋገጥ አለበት፡፡ አርባ ዓመት መግዛት አለብኝ በሚል የሚንቀሳቀስ ይመስለኛል፡፡ እነዚህ መውጪያ የሌላቸው አዙሪት ናቸው፡፡ በዚህ ዓመት የጠበቀው 100 ሚሊዮን ሆኖ እያለ 40 ሚሊዮን ካገኘ በሚቀጥለው ዓመት ሲያቅድ 50 ሚሊዮን ላገኝ እችላለሁ ነው ማለት ያለበት፡፡ የመንግሥት ተግባር ይኼ ነው፡፡ ከዚህ ልማታዊ መንግሥት ከመሆን ፍላጐት ጋር በተያያዘ በቃ ሁሉን ነገር ይቻላል፤ ይደረጋል በሚል የምኞት መንፈስ ነው እየተንቀሳቀሰ ያለው፡፡ ለምሳሌ የአምስት ዓመቱ ዕቅድ ችግር ይኼ ነው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በግልጽ እንደተናገሩት ማለት ነው፡፡ ‹‹ለምን ሰፋ አድርገን አንገምትም?›› ነው ያሉት፡፡ ይኼ እንግዲህ አጠቃላይ የመንግሥትን አመለካከት ያሳይሀል፡፡ መንግሥት ይኼን ያህል አገኛለሁ ብሎ ሲያስብ በዚህ መንፈስ ነው ሚንቀሳቀሰው፡፡

ሪፖርተር፡- የዋጋ ግሽበቱ እየጨመረ መጥቷል የመንግሥት ተዓማኒነት በጣም እየቀነሰ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱ ኢኮኖሚ ወዴት እያመራ ነው ይላሉ?

አቶ ሙሼ፡- እንደተቃዋሚ ፓርቲ በምናይበት ዓይን፣ ኢሕአዴግ ለምን የዋጋ ግሽበቱን አልተቆጣጠረም አይደለም፡፡ ኢሕአዴግ አልቻለም፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲው አልተሳካም፡፡ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ላለመሳካቱ መገለጫው አለመረጋጋትና ብጥብጥ መሆን የለበትም፡፡ ከዚያ በፊት መፍትሔ የመሻት ጉዳይ መምጣት አለበት፡፡ ስለዚህ ኢሕአዴግ ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ አስተሳሰቡ ወደ ነፃ ገበያ ሥርዓት አስተሳሰብ የመለወጥ ግዴታ አለበት፡፡ በአብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ዙርያ ራሱን አጠናክሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ከቀጠለ 20 ዓመት ሞልቶታል፡፡ በእነኝህ 20 ዓመታት ውስጥ ኢኮኖሚው አድጓል፡፡ የዋጋ ግሽቡቱ ግን የማይቀመስ ሆኗል፡፡ መሠረተ ልማቶችን ሰዎች ጥለዋቸው የሚያልፉ ናቸው፡፡ ትልልቅ አምፓየሮች ሁሉ ከመሠረተ ልማቶቻቸው ጋር ጠፍተዋል፡፡ መሠረተ ልማት ብቻውን በቂ ነገር አይደለም፡፡ ያ መሠረት ልማት ምርታማ በሆነ የኢኮኖሚ ሥርዓት መታገዝ አለበት፡፡  በእኔ እምነት በዚህ ረገድ አማራጭ ፖሊሲ ይዞ ያለው ፓርቲ ኤዴፓ ነው፡፡  እንዲህ ዓይነት ውስብስብ ለሆነው ኢኮኖሚ ቀውስ፣ አማራጭ ፖሊሲ ሲያቀርብ የነበረው ኤዴፓ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ አሁን ጥቅሙንና ጉዳቱን የሚገመግምበት ጊዜ ላይ ደርሷል፡፡ ብዙ ነገሮች በመሠረተ ልማት ሥራዎች ተደበስብሰውና በዓመታዊ ገቢ ዕድገት ተከምረው ማኅበረሰቡ የጠራ ግንዛቤ ሳይኖረው ቆይቷል፡፡ አሁን ግን የማገናዘቢያ ዕድል አግኝቷል፡፡ የመሠረተ ልማት ግንባታ ለአንድ አገር ጠቃሚ ቢሆንም፣ ሕልውና ከማስጠበቅ አኳያ ግን ኢሕአዴግ ውጤታማ እንዳልሆነ በተግባር ነው ያየው፡፡ አልፎ ተርፎ ወደ ደርግ ሥርዓት ተመልሶ ሠልፍ ውስጥ ገብቷል፡፡ ከጠዋት ጀምሮ እስከ ስድስት ሰዓት መሠለፍ ተጀምሯለ፡፡ በእኔ እምነት ይኼ በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ይለወጣል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ኢሕአዴግ የፖለሲ አቅጣጫውን መለወጥ ካልቻለ የዋጋ ግሽበቱም ይቀጥላል፤ ሊባባስም ይችላል፡፡ በዚሁ ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮችንም በቀላሉ ማቆም አይቻልም፡፡  ኢሕአዴግ ሦስት አማራጮች አሉት፡፡ የፖሊሲ አቅጣጫውን መቀየር፣ አልቻልኩም ብሎ በፈቃዱ ከሥልጣን መልቀቅ፣ ወይም ደግሞ በሕዝብ ድምፅ መቀጣት፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter