አል ኢስላሚያ ወርሃዊ መጽሔት ከአቶ ሙሼ ሰሙ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ

‹‹…የእያንዳንዱ ሙስሊም የመብት ጥያቄ ከእምነቱ መመሪያዎች አኳያ የመምረጥና አቋም የመውሰዱ ጉዳይ የማይሸረሸር መብቱ እንደሆነ አምናለሁ፡፡››

አል ኢስላም ፡- የኢትዮጵያን ሙስሊሞች የመብት ይከበርልን ጥያቄዎች አደባባይ ከወጡ አራት ወራት አልፈዋል፡፡ ለመሆኑ ይህ ሕዝብ ምን እየጠየቀ እንደሚገኝ ታውቃላችሁ?
አቶ ሙሼ፤ በመጀመሪያ እድሉን ስለሰጣችሁኝ እጅግ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡ ኢዴፓ ኢኮኖሚያዊ ፓለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የነጻነትና የመብት ጥያቄዎችን መነሻ በማድረግ የተደራጀ ፓርቲ በመሆኑና አባላቶቹም እንደማንኛውም ዜጋ በማህበረሰቡ ውስጥ ተደባልቀን የምንኖር እንደመሆኑ መጠን የተነሱትን ጥያቄዎች መስማታችን ጥርጣሬ ውስጥ ወይም ጥያቄ ላይ  መውደቅ የለበትም፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብ በተለያየ ምክንያት በተለያየ መልክና ቅርጽ፣ ከተለያየ መነሻና  ምክንያት በመነጨ በርካታ ፍትሓዊ ጥያቄዎች እንደነበሩትና ዛሬም እንዳሉት ይታወቃል፡፡ ከአራት ወራት ወዲህም በርካታ ጥያቄዎችን ይዞ አደባባይ እንደወጣ ይታወቃል፡፡ እነዚህም፡- የኢትየጵያ እስልምና ጉዳይ ጠቅላይ ምክር  ቤት ምርጫ ፣ በአወልያ የትምህርት ተቋም ቀጣይ ሚናና በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚነሱ የእምነት ዝንባሌዎችና የእምነት ትንታኔዎችን የሚመለከቱ ጉዳዮች መሆናቸውን ጠቅለል አድርጎ ማስቀመጥ ይቻላል፡፡
አል ኢስላም፤ የጥያቄዎቹን አግባብነት ከሕገ-መንግስቱ አንፃር እንዴት አገኛችኋቸው?
አቶ ሙሼ፤ ዜጎች በማንኛውም ጉዳይ ላይ ጥያቄ የማንሳት፣ ማብራርያ የመጠየቅና አግባብነት ያለውን ፍትሃዊ  መልስ በወቅቱና በአግባቡ የማግኝት መብት አላቸው፡፡ ሕገ-መንግስቱም ቢሆን በዚህ በኩል የመንግሰት ጣልቃ ገብነት በሌለበት ሁኔታ የሃይማኖት ነጸነትንና እኩልነትን በተለይ ደግሞ  ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ፣ መረጃ ከማግኘትና ከመስጠት ፣ ፍትሕን ከመጠየቅና ፍትሕን ከማግኝት አኳያ አንቀጾቹ የማያሻሙ ናቸው፡፡ ከመርህ አኳያ በዚህ መሰረታዊ ነጥብ ላይ መስማማት ይኖርብናል፡፡ ተግባርን በሚመለከት ግን የተፈጠረው ሌላ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ በመነሳትም የሃይምኖት ትንታኔ የመስጠትም ሆነ የትኛው የእምነት ዘርፍ ትክክል ነው፣ ወይም የትኛው እምነት ትክክል አይደለም የሚለው ጥያቄ መተው የነበረበት ሙስሊሙ ማህበረሰብ በጋራ ወይም በተናጠል በፈቃዱ ለሚመርጠው አካል መሆን አለበት፡፡

አልኢስላም፤ ጥያቄዎቹ ላይ በመንግስት የተያዘው አቋም ምን እንደሆነስ መረጃዎ አላችሁ?
አቶ ሙሼ፤ ችግሩን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን የሚገልጹ መረጃዎች ከመገናኛ ብዙሃን አድምጫለሁ ፤ነገር ግን ውይይቱና ድርድሩ በምን ዓይነት ሁኔታ እየተካሄደ እንደሆነ በቂ ነው ሊባል የሚችል መረጃ የለኝም፡፡በዚህ ረግድ ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ለመፍት ከመሞከሩ በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው አካሄድ ይኸው ነው፡፡ በጉዳዩ ላይ የመንግስት ሚና መሆን ያለበት በድርድርና በውይይት ችግሩን መቅረፍ ወይም ሕግን ማስከበርና ግጭቶች እንዳይፈጠሩ መከላከል ሲሆን ሕግ ሲጣስና ግጭቶች ሲከሰቱ ተጠያቂዎቹን ሕገ-መንግስቱ በሚፈቅደው አግባብ  መጠን  ስልጣን ላለው የፍርድ አስፈጻሚ አካል ጉዳዩን ማቅረብና የፍርድ ሂደቱን ተከታትሎ ማስፈጸም ነው፡፡ ከዚህ ውጭ የእያንዳንዱን ሙስሊም የእምነት ጥያቄ  ከይዘትም ሆነ ከእምነቱ መመሪያዎች አኳያ የመፈተሽ፣ እምነቱን የመምረጥና አቋም የመውስድ ጉዳይ መቼም ቢሆን የእያንዳንዱ ሙስሊም ማህበረስብ የማይሸረሸር መብት መሆን እንዳለበት በጥብቅ አምናለሁ፡፡ አንዳንድ መንግስታዊ ውክልና ያላቸው አስፈጻሚዎች ወይም ተወካዮች ሕግን ከማስከበር ውጭ ርቀው በመሄድ በቀጥተኛም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ በእምነቱ ይዘትና አስተምህሮት ውስጥ ዘልቀው በመግባት የሚሰጡት የፍረጃ ትንታኔና የአውቅልሃለሁ ጣልቃ ገብነት ከሕገ-መንግስቱ መሰረታዊ ሃሳብ ጋር ይጣረሳል፡፡

አልኢስላም፤ ፓርቲያችሁ በመንግስት የተያዘውን አቋም ይደግፋል፤ ወይንስ የራሱ የተለየ አቋም አለው?
አቶ ሙሼ፤ መንግስት በጉዳዩ ባለቤቶች ማለትም በሙስሊሙ ማህበረሰብ ካልተጋበዘና ሙስሊሙ ማህበረሰብ ጥያቄዎቹን ለመፍታት የሚያደረጋቸው ጥረቶች አጠቃላይ አለመረጋጋትና ስጋት የሚደቅኑ አዝማሚያዎች እንደሚያጭር በተጨባጭ መረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ መንግስት በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባት የለበትም የሚል ጽኑ እምነት ፓርቲያችን አለው፡፡

አል-ኢስላም፤ መንግስትና ኃይማኖት የተለያዩ መሆናቸውን በህገመንግስቱ በግልፅ ሠፍረዋል፡፡የእናንተ ፓርቲ ከዚህ ድንጋጌ የተሻለ ወይንም የተለየ የፖለቲካ ፕሮግራም አለው?
አቶ ሙሼ፤ ሊብራል ዴሞክራቶች እንደመሆናችን መጠን የግለሰቦች ነጻነት፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ መብቶች በማንኛውም የእምነት፣የአስተሳሰብ ወይም የፓለቲካ ፍልስፍና ምክንያት መጨፍለቅ እንደሌለበት እናምናለን፡፡ ከዚህ የፓለቲካ ፍልስፍናችን በመነጨም መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆናቸው በፕሮግራማችን ውስጥ በማያሻማ ቋንቋ ሰፍሯል፡፡ የተለየ ነገር ካለም መብትንና ግዴታን አካቶ የያዘውን የሕገ-መንግስት አንቀጽ ሙሉ በሙሉ በተግባር ላይ እንዲውል በሰላማዊ መንገድ መታገላችን ብቻ ይሆናል ፡፡

አል-ኢስላም፤ ይህ ሕገመንግስታዊ ድንጋጌ በተግባር ምን ያህል ተተርጉሟል የሚል እምነት አላችሁ ?
አቶ ሙሼ፤ በመጀመሪያ ደረጃ ሕገ-መንግስቱ እየተዳደርንበት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በይዘቱ ላይ በርካታ ልዩነቶች ያሉን መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ከዚህ የልዩነት እምነታችን በመነጨም ሕገ-መንግስቱ በሚፈቅደው መንገድና የትግል ስልት ሕገ-መንግስቱ ላይ የሚገኙ በርካታ አንቀጾች እንዲሻሻሉና እንዲለውጡ በመታገል ላይ እንገኛለን፡፡ በዓለም አቀፍ ማህበረሰብ እውቅና አግኝተው በሕገ-መንግስቱ ውስጥ በሚገኙ በርካታ አንቀጾች አማካኝነት የዜጎች ሁለንተናዊ ነጻነቶችና መብቶች መከበራቸው ቢገለጽም በተግባር ግን በርካታዎቹ ግን እየተተረጎሙ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡
በሕገ-መንግስቱ ውስጥ የሰፈሩ አንቀጾች በመመሪያዎች በፓሊሲዎችና በደንቦች አልፎ ተርፎም በተለያዩ መንግስታዊ ተቋማት፣ በፓለቲካ ሹመኞች፣ በአስፈጻሚ አካላትና በግለሰቦች አሊያም በቡድኖች አማካኝነት በገሃድ እየተጣሱ መሆኑ የእለት ተእለት እውነታዎች ናቸው፡፡ እንደዚህ አይነት ሕገ-መንግስታዊ ጥሰቶች በተለይ በኢትዮጵያ አሳሳቢ የሚሆኑት የዲሞክራሲ ስርዓት ዓይነተኛ መገለጫና የመንግስት የስልጣን ክፍፍል ምሰሶ የሆኑት ሶስቱ አካላት ሕግ አውጭው፣ ሕግ ተርጓሚውና ሕግ አስፈጻሚው ሚናቸው የተደበላለቀና አንዱ በአንዱ፤ በተለይም አስፈጻሚው አካል በሕግ አውጭውና በሕግ ተርጓሚው  አሰራር ውስጥ በከፍተኛ ደረጃ ጣልቃ የሚገባ በመሆኑ በዜጎች ላይ የሚፈጸሙ ሕገ-መንግስታዊ ጥሰቶችን ለመከላከል፣ ለማረምም ሆነ አግባብ ያለውን ሕጋዊ ቅጣት  ለመውስድ የሚቻልበት እድል የጠበበ በመሆኑ ነው፡፡

አል-ኢስላም፤ መንግሥት በሙስሊሙ ህብረተሰብ ውስጥ በመንግስት ህግ ሳይሆን በሸሪዓ እንተዳደር የሚል ፅንፈኛ ቡድን አለ ባይ ነው፡፡ በዚህ የመንግስት አቋም ትስማማላችሁ?
አቶ ሙሼ፤ በመጀመርያ ደረጃ የሸሪያ ሕግ በእምነቱ መሰረት ለተቀበለው ግለሰብ ጽንፈኛ ሊሆን የሚችልበት እድል አለ ብዬ አላምንም፤ የሸሪዓ ሕግ በሙስሊሞችም ዘንድ ቢሆን መተግበር ካለበት መተግበር የሚችለው የግለሰቡ ፈቃድኝነት ሲገኝ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ እስካሁን ድረስ ባለኝ መረጃ መሰረት ፈቃደኛ ሙስሊሞች በሸሪዓ ይጋባሉ፤ ጋብቻቸውም በሕግ ፊት የጸና ነው፡፡ ነገር ግን ሸሪዓን ጽንፈኛ የሚደርጉት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ዓለማዊ ሕጉን ወይም ሕገ-መንግሰቱን በሸሪዓ ለመተካት ተጽእኖ ሲያክሉበት ነው፡፡ ጽንፈኝነት ምንጩ ከየትኘውም ርዕዮት ዓለም ወይም የሃይማኖት አስተምሮት ሊሆን ይችላል፡፡ አደጋው  ግን ምንጩ ወይም መሰረቱ ላይ ሳይሆን እምነቱ በሌሎች ነጻነትና መብት ላይ ጣልቃ የመግባት ዝንባሌን ሲጋብዝ ነው፡፡ይህ ዝንባሌ ደግሞ የሰው ልጆች በነጸነት የማስብ፣ የመወሰን፣ የማምለክና የመደራጀት መብቶች ላይ የሚያነጣጥር አደጋ ነው፡፡

ጽንፈኝነት በአሁኑ ጊዜ አለም አቀፍ ቅርጽና ይዘት ያለው አደጋ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ፤ ይህ ችግር ኢትዮጵያ ውስጥ ሊከሰት አይችልም ብሎ መደምደም ያስቸግራል፡፡ ምክንቱም  ይህ  ስጋት የመንግስት ስጋት ብቻ ሳይሆን የሙስሊሙ ማህበረስብ አካላትም ስጋት እንደሆነ በተለያየ ጊዜ  ጽንፈኝነትና አደጋውን በማስመልከት በመገናኛ ብዙሃን ስጋታቸውን ሲያሰሙ ለማዳመጥ ችያለሁ፡፡ ከዚህ ባለፈ በፓርቲያችንም ሆነ በግሌ  የአደጋውንና የስጋቱን  መጠን በመረጃ ለማረጋገጥ የሚቻል አይደለም፡፡

አልኢስላም፤ በኢትዮጵያ ለኃይማኖት ግጭት ዋነኛ መንስኤ ምንድን ነው ?
አቶ ሙሼ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ግጭት የለም ብሎ በድፍረት መናገር ይቻላል፡፡ ነገር ግን በማንኛውም ማህበራዊ ሕይወት ሂደት ውስጥ ሊከሰት እንደሚችለው  ከግለሰቦች ግልፍተኝነት በተነሳ ወይም ከግንዛቤ እጥረት በመነጨ ወይም መከባባርና መቻቻልን ለመሸከም አቅም ከማጠር አንጻር አለመግባባቶችና ቁርቋሶዎች በአንዳንድ አካባቢዎች በግልጽ ሊታዩ በሚታይ ደረጃ ተከስተዋል፡፡ ኢትየጵያ ውስጥ የሚገኙ ሃይማኖቶች የሚሰብኩት መቻቻልን፣ መከባበርንና አብሮነትን በመሆኑ በተለይም የየእምነቶቻቸው ተከታዮች ለኃይማኖት ግጭት በር የማይከፍቱ በመሆናቸው የሃይማኖት ግጭት ተብሎ ሊወራለት የሚችል አደጋ አለ ለማለት አያስደፍርም፡፡

አል-ኢስላም፤ በአገሪቱ ኃይማኖትን ሽፋን በማድረግ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማስፈፀም የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች /ኃይሎች እንዳሉ አልፎ አልፎም ቢሆን ሲደመጥ ይሰማል፡፡ በዚህ ረገድ አስተያየትዎ ምንድን  ነው?
አቶ ሙሼ፤ በመጀመሪያ ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ሃይሎች የሚለው የጥቅል አቀራረብ ተነጣጥሎ መቅረብ አለበት፡፡ ሃይሎች የተባሉት የሚወክሉት እነማንንና ምንን እንደሆነ፤ ቅርጽና ይዘታቸው ምን እንደሚመስል ስለማይታወቅ ስለነሱ መነጋገር አይቻልም፡፡ እኔ እስከማቀው ድረስ ግን በሃይማኖት የተደራጁ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ አሉ ብዪ አላምንም፡፡
ይህም ሆኖ ማንም ቢሆን መንግሰትም ሆነ ዜጎች በኃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳን የሚያራምዱ ከሆነ ሃይማኖትንና መንግስትን በጉልበት ለመቀላቀል ከመታገል ውጭ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ በኃይማኖት ሽፋን የፖለቲካ አጀንዳን ማራመድም ሆነ ሃይማኖትንና መንግስትን በመቀላቀል የስልጣን መደላድል ለመፍጠር መፍጨርጨር፤ የዴሞክራሲ ዓይነተኛ መገለጫ ከሆኑት በነጻነት ከማሰብና በፈቃድ ከመደራጀት ፍልስፍና ጋር  የሚጋጭ ነው፡፡ በመሆኑም መንግስት፣ ፓርቲም ሆነ የትኛውም ቡድን አለበለዚያም ግለሰቦች ኃይማኖትን ሽፋን አድርገው መንቀሳቀሳቸው ከሊብራል ዲሞክራሲ ፍልስፍናችን አኳያ ተቀባይነት የለውም፡፡ ከሕግ አኳያም ቢሆን ሕገ ወጥነት ነው፡፡

አል-ኢስላም፤ መንግሥት የህዝበ ሙስሊሙን ጥያቄዎች የመፍታቱ አቋሙን እንደ ፓርቲ እንዴት ይገመግሙታል መፍትሄውስ ምንድን ነው?
አቶ ሙሼ፤ የኢትዮጵያ ሕገ-መንገስት የእምነት ነጻነትንና የሃይማኖት እኩልነትን በማያሻማ ቋንቋ ያስቀምጣል፡፡ መንግስትም ሆነ ሃይማኖቶች አንዱ በአንዱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንዳይገቡ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በመነሳት፣ ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርኩት መንግስት በሙስሊሙ ማህበረስብ ጥሪ እስካልተደረገለት ድረስ ሙስሊሙ ማህበረሰብ ችግሮቹን በራሱ መንገድ ሊፈታ ይገባል፡፡ ሙስሊሙ ማህበረሰብም ችግሩን የመፍታት ብቃትና አቅም እንዳለው አምናለሁ፡፡ በመሆኑም ሙስሊሙ ማህበረስብ የውስጥ ጉዳዩን ከራሱ ይልቅ በመንግስት እንዲፈታ የሚሻ አይመስለኝም፡፡ ይህ እንግዲህ ከእምነት አኳያ ሲፈተሽ ነው፡፡ መንግሰት ችግሩን ለመፍታት እየሄድኩበት ነው የሚለው አቅጣጫ በአንድ በኩል የጽንፈኞችን አጀንዳ የማዳፈን በሌላ በኩል ደግሞ በእምነቱ ውስጥ የተከሰቱ ልዩነቶችን የመዳኝት እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ጉዳዩ ሁለት ገጽታ አለው ማለት ነው፡፡
በሙስሊሙ ማህበረሰብም ዘንድ በአንድ በኩል በሃይምኖታችን የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየተገባብን ነው ተጽእኖ እየደረሰብን ነው የሚል የመብት ጥያቄ የሚያነሱ ሃይሎች  ያሉትን ያህል፤ በሌላ በኩል ሃይማኖቱን የስልጣን ማግኛ መሳሪያ ለማደርግ በማቀድ የጽንፈኝነት አልፎ ተርፎም የሌሎች ተቀጥላ አጀንዳዎችና ዝንባሌዎች ሰለባ የሆኑ  ሃይሎች ለሃይማኖቱ ደህንነት ስጋት እንደሆኑባቸው የሚገልጹ አሉ፡፡ ይህ በራሱ ጉዳዩን እጅግ ወስብስብ አድርጎታል፡፡ በእኔ እምነት በመንግስት አሰራር ውስጥ ጣልቃ የመግባት ድርጊት ከሃይማኖቱ ተከታዮች መንጭቶ ስጋት መሆኑ በመረጃ እስካልተረጋገጠ ድረስ መንግስት በሃይማኖት የውስጥ ጉዳይ ሊኖረው የሚገባው ሚና የሽምግልና፣ የማግባባትና የማስታረቅ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ሌላው ማንኛውም ችግር መፈታት ያለበት በሕግ አግባብ ብቻ መሆን ይኖርበታል፡፡
ማዋከብ፣ ማሸማቀቅም ሆነ የተለያዩ ስሞችን መስጥት በነጻና ገለልተኛ ሕግ ፊት ትርጉም የለውም፡፡ በነጻና ገለለተኛ የዳኝነት ስርዓትም ያስጠይቃል፡፡ መንግስት የተሰጠውን መንግስታዊ ሃላፊነት ከመወጣትና አደጋን በቅድሚያ ከመከላከል አኳያ ሊወስዳቸው የሚገቡ ሕጋዊና ፍትሐዊ ጥንቃቄዎችና እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው አንዳንድ የጉዳዩ ባለቤትና የመንግሰት ተጠሪዎች የሙስሊሙን ማህበረስብ አስመልክቶ የሚሰጧቸው መግለጫዎች የጉዳዩን ክብደትና የህግን የበላይነት የሚጻረር ከመሆኑም በላይ ሙስሊሙን ማህበረስብ የሚመጥን ሆኖ አላገኝሁትም፡፡ ይህ ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ፓለቲካ የሚመጥን ባህርይ አይደለም፡፡ ሕግ ተጥሶ ሲገኝ እንደጥፋቱ ስፋትና ጥልቀት የማስተማር፣ የማስገንዘብ፣ አቅጣጫ የማስያዝ ጉዳይ ይቀድማል፡፡ ይህ ካላረመ ደግሞ ሕጋዊ ቅጣት ይከተላል፡፡ በአጠቃላይ የመንግስት አካላት ሕገ-መንግስታዊ ግዴታቸውን በመወጣት ሂደት ውስጥ የሕግ የበላይነት መከበሩን፣ ተጽእኖ አለመኖሩን፣ የማንኛውም ዜጋ መብት አለመጣሱን በጥንቃቄ መከታተልና ማረጋገጥና እራሳቸውም ማክበር ይጠበቅባቸዋል፡፡
ይህን አሰራረር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ስም የሚንቀሳቀሱ የትኛዎቹም ሃይሎችም ሊከተሉትና ሊተገብሩት የሚገባ መሰረታዊ መርህ ነው፡፡ ከዚህ ውጭ በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የሚፈጠረው አለመረጋጋት የሁላችንም ችግር እንደመሆኑ መጠን መስሊሙ ማህበረሰብ ያለውን ብቃትና አቅም ተጠቅሞ በመንግስትም ሆነ በሌሎች ዜጎች ላይ ስጋትና ክፍተት ሊሆኑ የሚችሉና ጣልቃ ገብነት የሚጋብዙ ድርጊቶችንና ልዩነቶችን በማጥበብ ለጉዳዩ ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት ሃይማኖቱን መሰረት አድርገው መተባበር፣ መደማመጥ፣ ጥላቻና ልዩነትን በማራቅ ለእምነታቸውና ለሰላማቸው ቅድሚያ በመስጠት ችግሩን እንደሚፈቱት አምናለሁ፡፡

አል- ኢስላም፤ በመጨረሻም ፖለቲከኛ እንደመሆንዎ የአንድ እምነት ተከታይ ህዝብ እና የእምነት ተቋማት በኢትዮጵያ ውስጥ ለፖለቲካ አጀንዳነት የመዋል ዕድላቸው ምን ያህል ነው ይላሉ?
አቶ ሙሼ፤ በኢትዮጵያ ውስጥ የሃይማኖት ነጻነትና እኩልነት እንዲሁም በመንግስትና በሃይማኖት መካከል ግልጽ ልዩነት መኖር እንዳለበት በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን እንደ ኢትዮጵያ ባሉና ዴሞክራሲያዊ ባህል ባልበጸገባቸው ሃገራት መብቶች በአሰራረርና በአፈጻጸም ሊጣሱና ሊጨፍለቁ የሚችሉበት ሰፊ እድል አለ፡፡ በዚህም ምክንያት ሃይማኖቶች ከመጠቀሚያነት የጸዱ ናቸው ለማለት ያዳግታል፡፡ ሃያማኖቶችንና ተቋማቱን የሚመለከቱ የተለያዩ ሕግጋቶችና ድንጋጌዎች ከግንዛቤ እጥረት በመነጨ  ወይም መመሪያ በመቀበልና ከግል ፍላጎት በሚመነጩ ምክንያት በተለያዩ የመንግስት አስፈጻሚ አካላት ሊጣሱ የሚችሉበት እድል  መኖሩ ሁልጊዚም ቢሆን እንደስጋት መቀመጥ የሚገባው ጉዳይ ነው፡፡ ትልቁ ቁም ነገር ግን እነዚህ መብቶች በሕገ-መንግስቱ ውስጥ በመኖራቸው ብቻ የተሟሉ ናቸው ብሎ በማመን እጅና እግርን አጣምሮ መቀመጥ ሳይሆን፤ ሕገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎቹ ተግባር ላይ ሲውሉ  አስፈጻሚ አካላት በሕገ-መንገስቱ ውስጥ የሰፈሩ መብቶችን በማረጋገጥ ሂደት ውስጥ ምን አይነት ሚና እንዳላቸው በጥንቃቄና በጥልቀት መረመር ይገባል፡፡ ተግዳሮቶችም ካሉ ተግዳሮቶቹን የሌሎችን መብት በማይጻረር መልኩ በሕጋዊና ሰላማዊ መንገድ ጠንክሮ መታገል ያስፈልጋል፡፡ አመሰግናለሁ፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter