የኢዴፓ ኘሬዚዳንት ከተለያዩ የኤምባሲ ተወካዮች ጋር ተወያዩ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ጥር 24 ቀን 2001 ዓ.ም ያካሄደው 4ኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ በተሣካ ሁኔታ መጠናቀቁን ተከትሎ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች፤ እንዲሁም ተቀማጭነታቸው አዲስ አበባ የሆኑ በርካታ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላት የተሰማቸውን አድናቆት እየገለፁ ይገኛሉ፡፡ ሰሞኑን ከፓርቲው ኘሬዝዳንት ጋር ተገናኝተው ውይይት ካደረጉት የኤምባሲ ተወካዮች መካከል በኢትዮጵያ የእንግሊዝና የጃፓን አምባሳደሮች ይገኙበታል፡፡ አምባሳደሮቹ እና የተለያዩ የኤምባሲ ተወካዮች ከኢዴፓ ኘሬዝዳንት ከአቶ ልደቱ አያሌው ጋር በመገናኘት ሰፊ የተናጠል ውይይት አድርገዋል፡፡ በውይይቱም ወቅት ለኤምባሲ ተወካዮቹ በጠቅላላ ጉባኤው ክንውን፣ በወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳዮች እንዲሁም በፓርቲው የወደፊት የትግል አቅጣጫ ዙሪያ ገለፃና ማብራራያ ተደርጐላቸዋል፡፡

የኤምባሲ ተወካዮቹ በየበኩላቸው በአቶ ልደቱ አያሌው በኩል የተደረገላቸውን ገለፃ ካዳመጡ በኋላ፤ በአሁኑ ወቅት ፓርቲው በየደረጃው በሚገኙ መድረኮች አማካይነት አቅሙ በፈቀደ መጠን በኢትዮጵያ ውስጥ የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት  ግንባታ ለማገዝ እያደረገ ያለውን ሁለንተናዊ ጥረት አድንቀዋል፡፡ ብዙዎቹ የኤምባሲ ተወካዮች በአጠቃላይ የፓርቲውን ራዕይና እየተከተለ ያለውን ስልት “አበረታችና ተስፋ ሰጭ” ሲሉ አወድሰውታል፡፡ ለወደፊቱ ቀጣይነት ያለው እና አስተማማኝ የሆነ ለውጥ ለማምጣት ይቻል ዘንድ ፓርቲው ከዚህ በበለጠ ጠንክሮ መስራት እንደሚጠበቅበትም አሳስበዋል፡፡

በውይይታቸው መጨረሻም፣ እንደዚህ ዓይነቱ የውስጥ የፖለቲካ ጉዳይ መሰራት ያለበት በዋናነት በራሱ በፓርቲው መሆን እንዳለበት የገለፁት የተለያዩ የኤምባሲ ተወካዮች፣ ለወደፊቱ ከፓርቲው ጋር በመቀራረብ አስፈላጊውን ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍና እገዛ ለማድረግ ያላቸውን ፍቃደኝነት ለፓርቲው ኘሬዝዳንት ለአቶ ልደቱ አያሌው ገልጸዋል፡፡

(በኢዴፓ የሕዝብ ግንኘነት ዘርፍ የተዘጋጀ)

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter