ኢዴፓ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት የሚደረግበት አጀንዳ አቀረበ።

ኢዴፓ በሚያዚያ ወር 2001 ዓ.ም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት የሚደረግበት አጀንዳ አቀረበ። ይኸው በተቀዋሚዎች ቀን ውይይት የሚደረግበት አጀንዳ፣ ማክሰኞ ሚያዝያ 12 ቀን 2001 ዓ.ም እንደሚቀርብ ታውቋል። ኢዴፓ በዚህ ዓመት በተቀዋሚዎች ቀን ሦስተኛ አጀንዳውን ለውይይት ያቀረብ ሲሆን፤ ከኢዴፓ ሌላ እስከ አሁን አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ በምክር ቤቱ ደንብ መሰረት እድሉን ለመጠቀም አጀንዳ አቅርቦ አያውቅም።በኢፌዴሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
በሚያዝያ ወር 2001 ዓ.ም በተቃዋሚዎች ቀን በኢዴአፓ-መድህን ፓርቲ በኩል “ለፖለቲካ ፓርቲዎች በመንግሥት የሚሰጥ ድጋፍን” አስመልክቶ የቀረበ የመወያያ አጀንዳ

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 31 የተደነገገውን የመደራጀት መብት መሠረት በማድረግ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና የተሰጣቸው የፖለቲካ ድርጅቶች በአገራችን መኖራቸው ይታወቃል፡፡

እነዚህ ፓርቲዎች በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲተገበርና የተጀመረው የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ሂደት እንዲጐለብት የበኩላቸውን እገዛ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ ፓርቲዎቹ ለተለያየ ፖለቲካዊና ድርጅታዊ ሥራ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ የሚያመነጩት ከአባላት መዋጮ፣ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች ከሚደረግ መዋጮና እርዳታ ነው፡፡

ይሁን እንጂ አገራችን ድሃ ከመሆኗና ለፓርቲ ፖለቲካ አዲስ ከመሆንዋ አንፃር በሀገር ውስጥ ከሚገኙ አባላት የሚሰበሰበው የመዋጮ መጠን ስራው ከሚጠይቀው የገንዘብ ፍላጐት አንፃር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት በተለይም ተቃዋሚ ፓርቲዎች በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባላትና ደጋፊዎች የገንዘብ ድጋፍና እርዳታ መጠየቅ ግድ ሆኖባቸው ቆይቷል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አሠራር ወደፊት እየቀጠለ የሚሄድ ከሆነ በአገር ውስጥ በሚደረገው የፖለቲካ ትግል ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል እምነት በመፈጠሩም  ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች በጉዳዩ ላይ ተከታታይ ውይይትና ድርድር ካደረጉ በኋላ ፓርቲዎቹ ከመንግሥት ልዩ የበጀት ድጋፍ ማግኘት ይችሉ ዘንድ ባለፈው ዓመት መጀመሪያ ላይ  የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2000 በተከበረው ምክር  ተሻሽሎ እንዲወጣ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በዚህ አዋጅ አንቀጽ 42 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ “መንግሥት በፌዴራልና በክልል ምክር ቤቶች ውክልና ላላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የዕለት ተዕለት ሥራ ማከናወኛ ድጋፍ ይሰጣል” የሚል ድንጋጌ ተቀምጧል፡፡ ይህ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደረግ ድጋፍ ምንጩ   “ከመንግሥት የሚመደብ በጀት፣ ከዕርዳታና ከሌላ ከማንኛውም አካል የሚገኝ” እንደሆነም በአዋጁ አንቀጽ 43 ላይ ተቀምጧል፡፡ ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ ለፖለቲካ ፓርቲዎች የሚከፋፈልበት መሥፈርት ጭምር በአዋጁ ላይ ሠፍሯል፡፡ ነገር ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች ዙሪያ ያለው ችግር ምን ያህል አሳሳቢ እንደሆነ እየታወቀ እስከ አሁን ድረስ ሕጉ በተግባር ሊተረጐምና የማስፈፀሚያ ደንብም ሊወጣለት  አልቻለም፡፡

በ2002 ዓ.ም የሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ እየተቃረበ ባለበት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ መድረኮች ጥያቄውን ስናቀርብ የቆየን ቢሆንም መንግሥት አዋጁን በተግባር ከመተርጐም ይልቅ ላለፈው አንድ ዓመት ያህል ዝምታን መርጦ ቆይቷል፡፡

ስለሆነም ፡-

  1. የተከበረው ምክር ቤት የሚያወጣቸው አዋጆች በሥራ ላይ ስለመዋላቸው የመከታተልና የመቆጣጠር ኃላፊነት ያለበት በመሆኑ፣
  2. በመጪው ዓመት አገር አቀፍ ምርጫ የሚካሄድ በመሆኑና ፓርቲዎቹ ከወዲሁ በቂ ዝግጅት ማድረግ ይችሉ ዘንድ ከመንግሥት የሚደረገው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው በመሆኑ፣
  3. የመጪው 2002 ዓ.ም በጀት በያዝነው ዓመት በሠኔ ወር ስለሚፀድቅና ይህም ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት የሚደረግ ድጋፍ በበጀት ውስጥ ተካቶ መቅረብ የሚገባው በመሆኑ፣

የተከበረው ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ ሕጉ በአስቸኳይ በተግባር እንዲውል የሚያስችል ውሳኔ እንዲያሳልፍ ይህንን አጀንዳ ለውይይት አቅርበናል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter