ኢዴፓ ያቀረበው አጀንዳ በምክር ቤት ክርክር ተደረገበት

የምክር ቤቱ ደንብ በወር አንድ ጊዜ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አጀንዳ አቅርበው ክርክር እንዲደረግበት በደነገገው መሰረት ኢዴፓ ያቀረበው አጀንዳ ሚያዝያ 22 ቀን 2001 ዓ.ም በነበረው የፓርላማ ስብሰባ ክርክር የተደረገበት መሆኑ ታውቋል። በዚሁ ወቅት፣ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች በአጀንዳው ላይ ያላቸውን አቋም ገልጸዋል። በኢህአዴግ በኩል የአጀንዳውን መቅረብ እንደማይቃወም ገልፆ፣ ነገር ግን “መንግስት ለፓርቲዎች ድጋፍ እንዳይደረግ የህጉን ተፈጻሚነት አጓትቷል” በሚል ከኢዴፓ የቀረበውን ሃሳብ በተመለከተ፣ “ህጉን ወደ ስራ በመተርጎም ዝርዝር ደንብ ማውጣትም ሆነ በጀት መደልደል የምርጫ ቦርድ እንጂ የመንግስት ስራ አይደለም። ምርጫ ቦርድ ደግሞ ተጠሪነቱ ለምክር ቤቱ እንጂ ለአስፈጻሚው አካል (ለመንግስት) ባለመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ መንግስት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም” የሚል መከራከሪያ አቅርቧል።

ኢዴፓ በበኩሉ፣ “አገሪቱ ከምትከተለው ፓርላማዊ አሰራር አኳያ ‘መንግስት’ ማለት አስፈጻሚው አካል ብቻ አይደለም። በጀትም የሚመደበው በመንግስት አማካይነት አንድ ቋት ላይ ከሚሰበሰበው ሀገራዊ ሀብት በመሆኑ መንግስት አያገባኝም ማለት አይችልም። ህጉ ከወጣ አንድ ዓመት ከሰባት ወር ገደማ ቢሆነውም ‘የእንግሊዝኛ ትርጉም አልተዘጋጀም’ በሚል ተገቢ ያልሆነ ሰበብ ህጉ በነጋሪት ጋዜጣ ሳይታተም እንዲዘገይ ተደርጓል። አለመታተሙ ደግሞ አዋጁ በስራ ላይ እንዳይውል ምክንያት ሆኗል። እናም፣ መንግስት ያቀረበው ‘ተጠያቂ አደለሁም’ የሚል መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም” የሚል ሙግት አቅርቧል።

አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች “አጀንዳውን አንቃወምም” የሚል ሃሳብ ቢያቀርቡም፤ ‘አጀንዳው በኢዴፓ በመቅረቡ’ ግን ደስተኛ አለመሆናቸውን አሳይተዋል። “በአጀንዳው ላይ እምነት ካላችሁ አጀንዳውን ከኢዴፓ ቀድማችሁ እንዳታቀርቡ ማን ከለከላችሁ? ስለሆነም፣ በአጀንዳው መቅረብ ላይ ካመናችሁ ‘ኢዴፓ የቤት ስራውን ለምን ሰራ’ የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ተገቢነት የለውም” የሚል ምላሽ ከኢዴፓ ተሰጥቷል።

በመጨረሻም፤ በመጪው ዓመት በጀት ውስጥ ለፓርቲዎች የሚሰጠው ድጎማ የሚካተት መሆኑና በምርጫ ቦርድ በኩል የበጀት ማከፋፈያ ቀመር እንዲወጣ በምክር ቤቱ ያለው የምርጫ ቦርድን ስራ የሚከታተል ቋሚ ኮሚቴ ክትትል እንደሚያደርግ መግባባት ላይ የተደረሰ ሲሆን፤ ኢዴፓ ይህንን አጀንዳ በማቅረብ ዓላማውን እንዳሳካና በመጪው የግንቦት ወር ስለሚያቀርበው አጀንዳ በመዘጋጀት ላይ እንደሆነም ታውቋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter