ኢዴፓ የጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ በድል ተጠናቀቀ

EDP Addis Meetingኢዴፓ፤ ከምርጫ 97 ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሕዝብ ጋር የተገናኘበትን ሕዝባዊ ስብሰባ ዛሬ ግንቦት 8 ቀን 2001 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አካሄደ። ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ ከአዲስ አበባ ከተማ ብቻ ሳይሆን ከአዋሳ፣ ከሀረር፣ ከአዳማ፣ ከወላይታ ሶዶ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ ከሚገኙ ከተሞች የመጡ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተካፍለዋል።

ጥሪ የተደረገላቸው የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ተወካዮች፣ የሲቪክና የሙያ ማኅበራት መሪዎችና ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ታዋቂ ግለሰቦች፣ ጋዜጠኞች፣ በአብዛኛው ወጣቶችና ሴቶች በስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። በዕለቱ ከማለዳ ጀምሮ የአየር ሁኔታው ደመናማ ከመሆኑም በላይ ከቀትር በኋላ ኃይለኛ ዝናብ የጣለ ሲሆን፤ ሕዝቡ የስብሰባውን ሂደት ለመከታተል ሁሉንም ችግር በፅናት ተቋቁሟል። በዚሁም መሰረት፣ በስፋቱ የታወቀው የመብራት ኃይል አዳራሽ ሞልቶ ሕዝቡ በመስሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ ሆኖ በስፒከር የሚተላለፈውን መልዕክት በማዳመጥ የስብሰባውን ሂደት እስከመጨረሻው ሰዓት በፅሞና ተከታትሏል። በአጠቃላይ፤ እየመጣ ከሄደው ጭምር እስከ ሶስት ሺህ የሚደርስ ሕዝብ በስብሰባው ላይ እንደተገኘ ይገመታል።

በኢዴፓ ፕሬዚዳንት በአቶ ልደቱ አያሌው የመክፈቻ ንግግር በተጀመረው በዚሁ ስብሰባ ላይ ኢዴፓን የሚደግፉና የሚያሞግሱ ብቻ ሳይሆኑ፣ ኢዴፓን የሚተቹና የሚነቅፉ አስተሳሰቦችን የሚያንጸባርቁ ከሃምሳ በላይ አስተያየቶች፣ ጥያቄዎችና ልዩ ልዩ ሃሳቦች በሁለት ዙር ለሁለት ሰዓታት ያህል በነፃነት የተስተናገዱ ሲሆን፤ የፓርቲው አመራር አባላትም “ምላሽ ያስፈልጋቸዋል” ላሏቸው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ ሰጥተዋል።

ከስብሰባው ዕለት ቀደም ብሎ የመብራት ኃይል መስሪያ ቤት የፈቀደውንና ክፍያ የተቀበለበትን አዳራሽ “ለሌላ ጉዳይ እፈልገዋለሁ” በሚል ሰበብ ስብሰባውን ለመደናቀፍ ሙከራ ከማድረጉ በስተቀር፤ በስብሰባው ዝግጅትም ሆነ በሂደቱ ላይ ምንም ዓይነት የጎላ ችግር እንዳላጋጠመ ታውቋል።

ኢዴፓ የዚህን ስብሰባ ሂደት ገምግሞ ጠንካራና ደካማ ጎኖቹን በመለየት እስከ ሰኔ መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ በሀዋሳ፣ በድሬዳዋ፣ በባህር ዳርና በመቀሌ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችን በያዘው ዕቅድ መሰረት እንደሚያካሂድ ይጠበቃል።

ተያያዥ:

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter