ኢዴፓ ባቀረበው ሃሳብ መነሻነት ለፓርላማው የቀረበ የሕግ ረቂቅ ውድቅ ተደረገ

ሰኔ 11 ቀን 2001 ዓ.ም በተደረገው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ በቀረበ የሕግ ረቂቅ ላይ ኢዴፓ ባቀረበው አስተያየት መነሻነት የቀረበው ረቂቅ ሕግ ውድቅ ተደርጎ፣ ረቂቁን ያዘጋጀው አካል እንደገና አይቶ እንዲያቀርበው ተመላሽ መደረጉን የደረሰን ዜና አመለከተ።
እንደ ዜና ምንጫችን ከሆነ፣ በዕለቱ የቀረበው ረቂቅ ሕግ የሀገሪቱን ሰንደቅ ዓላማና የሰንደቅ ዓላማ ቀንን የተመለከተ ሲሆን፤ ረቂቅ ሕጉ ተዘጋጅቶ የቀረበው በምክር ቤቱ የማስታወቂያና ባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ነበር። በኢዴፓ በኩል በዚህ ረቂቅ ሕግ ላይ የተሰጠው አስተያየት፤

“የማስታወቂያና ባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በምክር ቤቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ረቂቅ ሕግ አዘጋጅቶ በማቅረቡ ሊመሰገን ይገባዋል። ረቂቅ ሕጉም፣ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ በተለያዩ ክልሎችና በመንግስት መስሪያ ቤቶች ስርዓትና ክብር ባለው መልኩ እንዲውለበለብ የሚያደርግ በመሆኑ የምንቃወመው አይሆንም። ይሁን እንጂ፤ ይህ ረቂቅ ሕግ ሁለት መሰረታዊ ችግሮች ይታዩበታል። አንደኛ፤ የምክር ቤቱ ደንብ እና የህግ አወጣጥ መመሪያ በሚያዘው መሰረት ረቂቁ የቀረበው በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ተዘጋጅቶ አይደለም። ሁለተኛ፤ ይህ ረቂቅ ሕግ የተዘጋጀው ቀደም ሲል በ1988ዓ.ም እና በ1989ዓ.ም የወጡ ህጎችን ለማሻሻል ሆኖ ሳለ አቀራረቡ የሕግ አቀራረጽና አዘገጃጀት ስርዓትን ተከትሎ የቀረበ አይደለም። ስለሆነም፣ ይህ ሕግ ለአዘጋጀው አካል ተመልሶ ተስተካክሎ ሊቀርብ ይገባዋል። ኢህአዴግ፣ የምክር ቤቱን ደንብና መመሪያ ጥሶ ባለው አብላጫ ድምፅ ይህንን ህግ እንዲጸድቅ ቢያደርግ በኛ በኩል የምንቃወመው መሆኑን እንገልጻለን”

የሚል ነበር። ሌሎች በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች በዚህ አጀንዳ ላይ አስተያየት ያልሰጡ ሲሆን፤ በኢህአዴግ በኩል የመንግስት ረዳት ተጠሪው ኢዴፓ ያቀረበው አስተያየት ትክክል መሆኑን በመግለጽ ረቂቅ ህጉ ለኮሚቴው እንዲመለስና ተስተካክሎ እንዲቀርብ ባቀረቡት ሃሳብ መሰረት፣ የኢህአዴግ አባላትም በፓርቲያቸው የቀረበን ረቂቅ ህግ ለመጀመሪያ ጊዜ በተቃውሞ ድምፅ ውድቅ አድርገው ረቂቅ ህጉ ለአመንጪው አካል እንዲመለስ ተደርጓል።

ባለፉት አራት ዓመታት ለምክር ቤቱ የቀረበ ህግ፣ ደንብና መመሪያ ተጥሶም ቢሆን እንዲጸድቅ ይደረጋል እንጂ ለአመንጪው የተመለሰበት አንድም አጋጣሚ አልነበረም። በመሆኑም፤ ይህ አጋጣሚ የኢዴፓ የትግል ውጤት የፈጠረው መሆኑ በምክር ቤቱ የታሪክ መዝገብ ሊሰፍር እንደሚገባው አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።

 

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter