ኢዴፓ በባህር ዳር ያካሄደው ስብሰባ ውጤታማ ሆኖ ተጠናቀቀ

Ethiopian Democratic Party - Bahirdar Public Meetingየኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሰኔ 28 ቀን 2001 ዓ.ም በአማራ ክልል በባህር ዳር ከተማ ያካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ በተሳካ ሁኔታ መጠናቀቁን ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ዘርፍ ያገኘነው መረጃ አመለከተ። ይህ ህዝባዊ ስብሰባ፤ ኢዴፓ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ አካሂዳቸዋለሁ ብሎ በዕቅድ ከያዛቸው ስብሰባዎች ውስጥ ሶስተኛው ሲሆን፣ ቀደም ሲል በአዲስ አበባና በሃዋሳ ከተካሄዱት ስብሰባዎች የባህር ዳሩም ስብሰባ ውጤታማ ሆኖ በድል መጠናቀቁ ታውቋል።
በባህር ዳር ከተማ በሙሉ ዓለም የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ ስብሰባ ላይ ጎንደርና ደብረ ማርቆስን ጨምሮ በባህር ዳር ከተማ ዙሪያ ከሚገኙ አነስተኛ ከተሞችና ቀበሌዎች የመጡ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተካፋይ እንደነበሩ ተገልጿል። የሙሉ ዓለም የስብሰባ አዳራሽ እስከ 1300 ሰዎችን መያዝ እንደሚችል የታወቀ ሲሆን፤ ኢዴፓ በጠራው በዚሁ ስብሰባ ላይ ከ1100 እስከ 1200 የሚሆን ህዝብ ስብሰባው ላይ የተገኘ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ጨምሮ አስታውቋል።

የባህር ዳሩን ስብሰባ ኢዴፓ ካካሄዳቸው የአዲስ አበባና የሃዋሳ ስብሰባዎች የተለየ የሚያደርገው፤ የስብሰባው ተካፋዮች ለኢዴፓ አመራር አባላት ያቀረቧቸው አስተያየቶችና ጥያቄዎች ባለፉት ዓመታት በፓርቲው ላይ የተነዙትን አሉባልታዎች ወደ ጎን በመተው “ባለፈው የፖለቲካ ሂደት ጥፋት እንደተፈጸመና አጥፊዎቹም እነማን እንደሆኑ በጊዜ ሂደት ጠንቅቀን ተረድተናል።እናም ወደ ኋላ ተመልሰን የምናጠፋው ጊዜ የለንም። አሁን የሚያሳስበን መጪው ጊዜ ነው” በሚል የቁጭት መንፈስ በመነሳሳት “ኢዴፓ እስከ አሁን የት ነበር? በጣም በመዘግየታችሁ ልትወቀሱ ይገባል። አሁንም ወደ ህዝቡ ገብታችሁ ማደራጀት ይጠበቅባችኋል” በማለት ገንቢ አስተያየት የቀረበበት መሆኑ ነው ሲል የዜና ምንጫችን አስረድቷል።
Ethiopian Democratic Party - Bahirdar Public Meeting 2
አንድ በስብሰባው ላይ የተካፈሉ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባል በበኩላቸው “ይህ ስብሰባ ከአዲስ አበባና ከሃዋሳው ለየት ባለ መልኩ የሰከነ፣ ብስለት የታየበትና በመግባባት መንፈስ የተጠናቀቀ ነው” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

የስብሰባው ተሳታፊዎች በአብዛኛው ወጣቶች ሲሆኑ፤ ስብጥሩን በተመለከተ የከተማው ነዋሪዎች፣ የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ማህበረሰብ አባላት፣ ሴቶችና አርሶ አደሮች ጭምር የተገኙበት በመሆኑ “ከእረኛ እስከ ምሁር የተሳተፈበት ስብሰባ ነበር” ብሎ ማጠቃለል እንደሚቻል ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል።

Ethiopian Democratic Party - Bahirdar Public Meeting 3

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter