ኢዴፓ ያካሄዳቸውን ስብሰባዎች ገምግሞ የዕቅድ ማስተካከያ አደረገ

– አቶ ልደቱ ወደ አውሮጳና አሜሪካ አቀኑ

በጥር ወር 2001 ዓ.ም የተካሄደው የኢዴፓ 4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረት፣ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2001 ዓ.ም ድረስ በአምስት ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ አቅዶ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል። በዚሁ ዕቅድ መሰረት በአዲስ አበባ፣ በሃዋሳና በባህር ዳር ከተሞች ውጤታማ ስብሰባዎችን አካሂዷል።

የኢዴፓ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የሦስቱን ስብሰባዎች ሂደትና ውጤት ከገመገመ በኋላ ቀሪዎቹ ስብሰባዎች መቼና የት መካሄድ እንዳለባቸው ውሳኔ አሳልፏል። በዚሁ መሰረት፤ ክረምቱ እየተጠናከረ በመምጣቱ በዝናቡ ምክንያት የስብሰባ ጥሪና ቅስቀሳ ለማካሄድ፣ ፖስተር ለመለጠፍና በራሪ ወረቀቶችን ለማሰራጨት አስቸጋሪ በመሆኑ፤ በክረምት ት/ቤቶች ስለሚዘጉና ተማሪዎችና መምህራን ለእረፍት ወደተለያዩ ቦታዎች ስለሚሄዱ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ አንድ ስብሰባ ለማካሄድ እስከ ሰላሳ ሺህ ብር የሚያስፈልግ በመሆኑና በዚህ ረገድ ፓርቲውን ከፍተኛ የፋይናንስ ችግር ስለገጠመው በመቀሌና በድሬዳዋ ሊካሄዱ የታቀዱት ህዝባዊ ስብሰባዎች ወደ መጪው ዓመት እንዲሸጋሩ መደረጉ ታውቋል።

ይህ በዚህ እንዳለ፣ የኢዴፓ ፕሬዚዳንት አቶ ልደቱ አያሌው በውጭ ሀገር ከሚገኙ የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች ጋር ለመነጋገር ከሐምሌ 2 ቀን 2001 ዓ.ም ጀምሮ ወደ አውሮጳና አሜሪካ መሄዳቸውን የፓርቲው የውጭ ግንኙነት አስታወቀ። በዚሁ መሰረት፣ በአሜሪካን ሀገር በአትላንታና በዋሺንግተን እንዲሁም ከተቻለ በአውሮጳ ደግሞ በለንደን ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ዕቅድ የተያዘ መሆኑን የውጭ ግንኙነቱ አስታውቋል።

በነዚህም ስብሰባዎች “ባለፉት ዓመታት በፓርቲውና በአመራሩ ላይ በተነዙት አሉባልታዎች ዙሪያ ማብራሪያ መስጠት፣ በኢዴፓ የ3ኛ አማራጭነት ዙሪያ ግንዛቤ ማስጨበጥ፣ በመጪው ዓመት በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ኢዴፓ ስለሚኖረው ተሳትፎ ማብራሪያ መስጠት” በሚሉ አጀንዳዎች ዙሪያ በውጭ ሀገር ከሚኖሩ ኢትዮጵያውን ጋር ውይይት እንደሚደረግ የውጭ ግንኙነቱ ጨምሮ ገልጿል።

ከዚሁ ጎን ለጎን ከኢትዮጵያውያን የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የሞራል፣ የፋይናንስና የቁሳቁስ ድጋፍ ለማሰባሰብ ጥረት እንደሚደረግ የዜና ምንጫችን አመልክቷል። በዚህ ረገድ ኢዴፓ የያዘውን ዓላማና ፕሮግራም የሚደግፉ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ከፓርቲው ጎን በመቆምና አስፈላጊውን ርብርብ በማድረግ ተጨባጭ ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ የፓርቲው የውጭ ጉዳይ ዘርፍ ጥሪውን አቅርቧል።

 

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter