ኢዴፓ በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚካሄደው ድርድር በመሳተፍ ላይ መሆኑ ታወቀ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በኢህአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል በሚካሄደው ድርድር በአራት ተወካዮቹ አማካይነት በመሳተፍ ላይ መሆኑን ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡ ኢዴፓን ወክለው በዚህ ድርድር ላይ የሚሳተፉት አቶ ሙሼ ሰሙ፣ አቶ አብዱራህማን አህመዲን፣ አቶ መስፍን መንግስቱ እና አቶ ደረጀ ደበበ መሆናቸውም ታውቋል፡፡

ድርድሩ ሰኞ ነሀሴ 25 ቀን 2001 ዓ.ም የተጀመረ ሲሆን፤ እስከ አሁን ድረስ የድርድሩን ሂደት ለመምራት በሚያስችለው የአሰራር ስርዓት (Modality) ላይ ውይይት ተደርጎ ስምምነት ላይ የተደረሰ መሆኑን የዜና ምንጫችን ገልጿል፡፡ ሀሙስ ነሀሴ 28 ቀን 2001 ዓ.ም በተደረገው ስብሰባ ደግሞ ዋናው የድርድር አጀንዳ ምን ይሁን? በሚለው ላይ ውይይት ተደርጎ ሦስት አጀንዳዎች በጋራ ስምምነት ተመርጠው ጸድቀዋል ሲል የዜና ምንጫችን አስታውቋል፡፡

በዚሁ መሰረት፤ የፓርቲዎች የሥነ-ምግባር ደንብ፣ የፓርቲዎች የሥነ-ምግባር ደንብ አፈጻጸም (Enforcement) እና በምርጫ ሂደት የሚያጋጥሙ ችግሮች (ፋይናንስ፣ የመገናኛ ብዙሃን አጠቃቀም፣ ወዘተ.) የሚሉት አጀንዳዎች የተመረጡ ሲሆን፤ በቀጣይ ቀናት በሚደረጉት ስብሰባዎች በነዚህ አጀንዳዎች ላይ ተራ በተራ ለመወያየት ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

ኢዴፓን በመወከል በድርድሩ ላይ የተገኙ ተወካዮች በሞዳሊቲው እና በአጀንዳ ቀረጻው ሂደት ላይ በተደረገው ስብሰባ ገንቢ ሚና እንደነበራቸው ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ ጨምሮ ገጿል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter