የኢዴፓ ማዕከላዊ ምክር ቤት ውሳኔዎችን አሳለፈ

የኢዴፓ ማዕከላዊ ምክር ቤት ሁለት ተከታታይ ስብሰባዎችን በማካሄድ በመጪው ግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫና በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማካሄድ ውሳኔዎች ማሳለፉን ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡

ማዕከላዊ ምክር ቤቱ በመጪው ግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ፓርቲው የሚኖረውን ሚና በተመለከተ ሰፊ የሃሳብ ልውውጥ ካደረገ በኋላ፤ በፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አማካይነት ስለ ምርጫው ዓላማ፣ ስለ ፓርቲው ተሳትፎና ግብ ግልጽ አቅጣጫ ተቀምጦ የአፈጻጸም ስትራቴጂና ስልት ተቀይሶ የውሳኔ ሃሳብ እንዲቀርብለት መመሪያ መስጠቱን የመረጃ ምንጫችን አመልክቷል፡፡

በሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በኩል መጪውን ምርጫ አስመልክቶ እስከ አሁን ድረስ ስለተከናወኑ ተግባራት አጭር ማብራሪያ መቅረቡንና ማዕከላዊ ምክር ቤቱም በቀረበው ማብራሪያ ላይ ሰፊ ውይይት ማድረጉን የመረጃ ምንጫችን አመልክቶ፤ የፓርቲው የገንዘብ፣ የሰው ኃይልና የቁሳቁስ አቅም ግምት ውስጥ ገብቶ የፓርቲው የምርጫ ተሳትፎ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ሰባ አምስት በመቶ የሚሆነውን (75%) አካባቢ ስለሚሸፍንበት ሁኔታና የምርጫውን ሂደት ተከታትሎ የሚያስፈጽም ግብረ ኃይል ስለሚቋቋምበት ሁኔታ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በሚያዘጋጀው የስትራቴጂ ሰነድ ላይ ትኩረት እንዲሰጠው ማዕከላዊ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል ሲል አክሎ ገልጿል፡፡

ማዕከላዊ ምክር ቤቱ በተለያዩ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሰፊና ጥልቅ ውይይት በማድረግ የጋራ ግንዛቤ የያዘ ሲሆን፤ የፓርቲው የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከገዥው ፓርቲና ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር የጀመረውን ድርድር በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ በመመስረት አጠናክሮ በመቀጠል በሀገሪቱ ለተጀመረው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታና ለመቻቻል ፖለቲካዊ ባህል መጎልበት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የበኩሉን ጥረት እንዲያደርግ አሳስቧል ፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter