የዘንድሮው ምርጫ ግንቦት 15 ቀን ይካሄዳል ተባለ

በሀገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች የምርጫውን የአፈጻጸም ሂደት በያዘው የጊዜ ሰሌዳ ላይ ያላቸውን አስተያየት እንዲሰጡ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በኩል በተደረገው ጥሪ መሰረት የኢዴፓ ተወካዮች በቦርዱ ጽ/ቤት በመገኘት አስተያየት ማቅረባቸውን የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ደረጀ ደበበ አስታወቁ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ባቀረበው የጊዜ ሰሌዳ ላይ፤ የዕጩዎች ምዝገባ ከታህሳስ 16 ቀን 2002 እስከ ጥር 15 ቀን 2002፣ የመራጮች ምዝገባ ከጥር 1 እስከ ጥር 30 ቀን 2002 ድረስ እንደሚካሄድ አቶ ደረጀ ጠቅስው፣ የምረጡኝ ቅስቀሳው ደግሞ ከየካቲት 1 ቀን ጀምሮ የድምፅ መስጫው ዕለት 48 ሰዓታት እስከሚቀሩ ድረስ እንደሚካሄድ አብራርተዋል፡፡ አቶ ደረጀ ባደረሱን መረጃ መሰረት የዘንድሮው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የክልል ምክር ቤቶች አባላት ምርጫ ዕሑድ ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም እንደሚካሄድም ታውቋል፡፡

የበርካታ ፓርቲዎች አመራር አባላት በስብሰባው ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን፤ በኢዴፓ በኩል “ካለፉት ምርጫዎች ለማወቅ እንደተቻለው ብዙዎቹ መራጮች የሚመዘገቡት ፓርቲዎች የምርጫ ቅስቀሳ ሲያካሂዱና ክርክሩ ሲጧጧፍ በመሆኑና አሁን በቀረበው የጊዜ ሰሌዳ መሰረት ቅስቀሳው የሚጀመረው ደግሞ የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ በመሆኑ በርካታ መራጮች ላለመመዝገባቸው ምክንያት ሊሆን እንደሚችል” ያለውን ስጋት መግለጹን አቶ ደረጀ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter