ኢዴፓ ከተመሰረተ 10 ዓመት ሆነው

ጥቅምት 20 ቀን 1992 ዓ.ም የተመሰረተው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አስረኛ ዓመት በአባላቱ ታስቦ መዋሉን ከፓርቲው የውጭ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡ የዜና ምንጩ በላከልን ዘገባ መሰረት፣ በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ አባላት ዕሑድ ዕለት ባደረጉት ሳምንታዊ ስብሰባ ፓርቲው የተመሰረተበትን ዕለት ምክንያት በማድረግ ባለፉት አስር ዓመታት የታለፉ ውጣ ውረዶችንና አሁን የተደረሰበትን የትግል ሁኔታ በተመለከተ አጭር ትውስታና ቅኝት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
በተለይም የፓርቲው የምስረታ ዕለት ገዢው ፓርቲና ሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካደረጉት የፊርማ ሥነ-ስርዓት ጋር መገጣጠሙ እጅግ እንዳስገረማቸው የፓርቲው አባላት ገልጸዋል፡፡ “አስረኛ ዓመታችን የሀገሪቱን ፖለቲካ ወደ ላቀ ደረጃ ካሸጋገረው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት ጋር መገጣጠሙ ዕለቱን ታሪካዊ ያደርገዋል፡፡ በፊርማ የጸደቀው ሰነድ የትግላችን ውጤት በመሆኑም ኩራት ይሰማናል፡፡ ባለፉት አስር ዓመታት ባደረግነው ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ያጋጠሙ ፈተናዎችን አልፈን እዚህ መድረሳችንን እንደ ድል፣ ድክመቶቻችንን እንደ ትልቅ ትምህርት መውሰድና ጠንካራ ተግባራቶቻችንን ይበልጥ አጠናክረን ለመቀጠል ዳግም ቃል መግባት ይጠበቅብናል” የሚሉ አስተያየቶች በአባላቱ ውይይት ወቅት ተደጋግመው ይደመጡ እንደነበርም የዜና ምንጩ ገልጿል፡፡

ኢዴፓ፣ ጥቅምት 20 ቀን 1992 ዓ.ም ተመስርቶ በዚያው ዓመት በግንቦት ወር በተካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በመሳተፍ 2 የፓርላማና 14 የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማሸነፉ ይታወሳል፡፡

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸውና የኢዴፓ መስራችና በአሁኑ ወቅት የውጭ ግንኙነት ቋሚ ኮሚቴ ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመዲን፣ “ኢዴፓ፤ ታዋቂ ባልሆኑ፣ በቂ ልምድ ባላካበቱና በትምህርታቸው ባልገፉ ወጣቶች (በወቅቱ ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የሆነ የትምህርት ዝግጅት የነበራቸው መስራች አባላት 2 ብቻ ነበሩ) በተመሰረተ ሰባት ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ያገኘው 16 የምክር ቤት መቀመጫ ትልቅ ድል ነበር፡፡ ይሁን እንጂ፣ በዚያ የምርጫ ቅስቀሳ ወቅት ‘ገዢውን ፓርቲ፣ ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ለሰላማዊ ትግሉ እንቅፋት የሆኑ አስተሳሰቦችን እታገላለሁ’ የሚል ታይቶም ተሰምቶም የማያውቅ ሦስት የትግል አቅጣጫ እንዳለው መግለጹ፤ ገዥውን ፓርቲ ብቻ ሳይሆን በተቃዋሚው ጎራ ያሉ ሰፊ ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን ‘ጎምቱዎች’ ጭምር አስቆጥቷል፡፡ በፓርቲው ላይ እስከ አሁን ድረስ ያልተቋረጠ የአሉባልታ ዘመቻ እንዲከፈትበትም ምክንያት ሆኗል” በማለት ገልጸው፤ “ይሁን እንጂ፣ የዛሬ አስር ዓመት የተጀመረው ሦስት አቅጣጫዎች ያሉት ትግል ፓርቲው ለድል እስከሚበቃና የተፈለገው የሥርዓት ለውጥ እውን እስኪሆን ድረስ ለወቅቱ በሚመጥን የትግል ስልት እየተመራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት” የሚል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter