የሁለት አገር አምባሳደሮች የኢዴፓን አመራር አነጋገሩ

ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ የሆኑ የሁለት አገሮች አምባሳደሮች ከኢዴፓ ከፍተኛ አመራር ጋር ንግግር ማድረጋቸውን ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡ እንደ ዜና ምንጩ ከሆነ፣ የኢዴፓ አመራር ከጃፓን እና ከኖርዌይ አምባሳደሮች ጋር በተናጠል በተደረገ የምሣ ግብዣ ላይ ውይይቱን ማካሄዳቸው ታውቋል፡፡

ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ጨምሮ እንደገለጸው፣ ሐሙስ እና ዓርብ ዕለት ከሁለቱ አገሮች አምባሳደሮች ጋር በተደረገው በዚሁ ውይይት ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳ የነበረው ጉዳይ በመጪው ግንቦት ወር ስለሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ እና በኢህአዴግና በሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል ስለተደረገው ድርድር ነበር፡፡

በመጪው ግንቦት ወር በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ዙሪያ ኢዴፓ እያደረገው ስላለው ዝግጅት ለአምባሳደሮቹ ገለጻ የተደረገ ሲሆን፤ በኢህአዴግና በሦስቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተደረገውን ድርድር ሂደት፣ ውጤትና ተግዳሮት (Challenge) በተመለከተም ለአምባሳደሮቹ በቂ ማብራሪያ በመስጠት የኢዴፓን አቋም ለማስጨበጥ ጥረት መደረጉ ታውቋል፡፡

ከሁለቱ ሀገሮች አምባሳደሮች ጋር የተደረገው ውይይት በመግባባት መንፈስ የተካሄደ መሆኑና በሁለቱ ወገኖች መካከል የተጀመረው ይህ ግንኙነትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሃሳብ ልውውጥ የተደረገበት መሆኑም ታውቋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter