አራቱ ፓርቲዎች በፖለቲካ አመለካከታቸው ስለታሰሩ ዜጎች ድርድር ጀመሩ

ለሁለት ወራት ያህል ተደራድረው የሥምምነት ሰነዶችን በፊርማቸው ያጸደቁት አራቱ ፓርቲዎች (ማለትም፤ ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ መኢአድና ኢህአዴግ) በቀጣይነት ሊደራደሩባቸው ከመረጧቸው አጀንዳዎች መካከል፤ “በፖለቲካ አመለካከታቸው ምክንያት የታሰሩ፣ ከሥራና ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ፣ ዛቻ ማስፈራራትና እገታ የደረሰባቸው እና በተለያዩ ክሶች በየፍርድ ቤቱ የሚመላለሱ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ደጋፊዎችን በተመለከተ” በሚለው አጀንዳ ላይ ቀጣይ ድርድር መጀመራቸውን ከኢዴፓ የውጭ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡

የኢዴፓ የውጭ ግንኙነት በላከልን መረጃ መሰረት፣ ቅዳሜ ጥቅምት 28 ቀን 2002 ዓ.ም ፓርቲዎቹ ባደረጉት ቀጣይ ድርድር ኢዴፓ፣ ቅንጅትና መኢአድ “አሉ” ያሏቸውን ችግሮች ማቅረባቸው ታውቋል፡፡ በኢዴፓ በኩል፤ ከቀድሞው ቅንጅት ጋር በተያያዘ በተከፈቱ የክስ መዝገቦች በሰሜን እና በደቡብ ወሎ በሚገኙ አባላቱ ላይ እስከ አሁን ድረስ እልባት ያላገኘ መጉላላት እየደረሰባቸው መሆኑን፤ በአርሲ ኢተያ አካባቢ ያሉ አባላቱ የኢዴፓ አባል በመሆናቸው ምክንያት ከህግ አግባብ ውጭ ቤታቸው ተበርብሮ ማስፈራሪያና ዛቻ እንደደረሰባቸውና አንድ አባሉ በዚሁ ምክንያት ወደ አዲስ አበባ መሰደዳቸውን፣ በኢሉባቦር ዞን የሚገኙ አንድ አባሉ በአካባቢው የመንግስት አካላት ሞባይል ስልካቸውን ተቀምተው ዛቻና ማስፈራሪያ እንደደረሰባቸው፣ በደቡብ ክልል በአለታ ወንዶ የሚገኙ አባላት በራሳቸው ተነሳሽነት ለከፈቱት ቢሮ “በአለታ ወንዶ ወረዳ የኢዴፓ ጽ/ቤት” የሚል የማስታወቂያ ሰሌዳ እንዳይሰቅሉ መከልከላቸውንና ዛቻና ማስፈራሪያ የደረሰባቸው መሆኑን፣… ወዘተ. ለአብነት ያህል በመጥቀስ በፓርቲው ላይ የደረሱ ችግሮችን በማስረጃ አስደግፎ አቅርቧል፡፡

ተደራዳሪዎቹ፤ በቀረቡት ጉዳዮች ላይ በሰፊው ከተወያዩ በኋላ ችግሮቹ “የሉም” ሊባሉ እንደማይችሉ መግባባት ላይ በመድረስ፣ ቀደም ሲል በደረሱበት ስምምነት መሰረት ችግሮቹን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት ተስማምተዋል፡፡ በዚሁ መሰረት፣ እያንዳንዱ ፓርቲ “ደረሱ” የሚላቸውን ችግሮች በመዘርዘር ከኢህአዴግ ጋር የሁለትዮሽ (bilateral) ውይይት በማድረግ በጋራ ለመፍታት፣ ችግሩ በሁለቱ ፓርቲዎች የሁለትዮሽ ውይይት ሊፈታ ካልቻለ ደግሞ ጉዳዩ ለአራቱ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት የሚል የአሰራር ሥርዓት ላይ ተስማምተዋል፡፡

ኢዴፓ፣ ቅንጅት፣ መኢአድና ኢህአዴግ አሁን የጀመሩት ቀጣይ ድርድር ቀደም ሲል ተስማምተው የፈረሙበትን ሰነድ ወደ ተግባር ያሸጋገረ መሆኑን ከኢዴፓ የውጭ ግንኙነት ያገኘነው መረጃ አመልክቶ፤ በቀጣይ ጊዜአት በመንግስት ይዞታ ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃንን መጠቀም ስለሚቻልበት ሁኔታ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግስት የሚደረግ የበጀት ድጎማን በተመለከተ፣ በምርጫ ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን የሚያይ ልዩ ችሎት ማቋቋምን በተመለከተ፣ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ምርጫ ታዛቢዎችን በተመለከተ፣ በምርጫው ሂደት የመከላከያ ሰራዊት ፖሊስና የአካባቢ ሚሊሻዎች ስለሚኖራቸው ሚና፣ የክልል መስተዳድሮች ቀደም ሲል የተፈረመውን ሰነድ በመፈጸምና በማስፈጸም ረገድ የሚኖራቸውን ሚና በተመለከተ፣… ወዘተ. በሚሉት አጀንዳዎች ዙሪያ ውይይቱ እንደሚቀጥል የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter