ኢዴፓ የምርጫ ዝግጅቱን አጠናክሮ ቀጥሏል

ተወናብደው የነበሩ አባላቱም እየተመለሱ ነው

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመጪው ግንቦት ወር ለሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ሰባ አምስት በመቶ (75%) በሚሆነው አካባቢ ዕጩዎችን ለማቅረብ የጀመረውን ዝግጅት አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ ከምርጫ 97 በኋላ በሀገሪቱ በተፈጠረው ፖለቲካዊ ሁኔታና በፓርቲው ላይ በተነዛው መጠነ ሰፊ የአሉባልታ ዘመቻ ምክንያት ተወናብደው ከፓርቲያቸው ተነጥለው የነበሩ አባላትም በጊዜ ሂደት ሀቁን በመገንዘባቸው በጊዜአዊነት ተጠግተዋቸው ከነበሩ ፓርቲዎች በመልቀቅ ወደ እናት ፓርቲያቸው እየተመለሱ መሆኑን የኢዴፓ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባልና የድርጅት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሊቀ መንበር የሆኑት አቶ ነፃነት ደመላሽ አስታወቁ፡፡
ፓርቲው ካለፈው ሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም ጀምሮ ለግንቦቱ ምርጫ ዝግጅት እያደረገ መሆኑን አቶ ነፃነት አስታውሰው፤ በአማራ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተንቀሳቀሱ የልዑካን ቡድን አባላት የፓርቲውን ነባር አባላት በማሰባሰብና አዳዲስ አባላትን በመመልመል ለምርጫ ዝግጅቱ የሚረዳ ውጤታማ ሥራ በማከናወን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በዚሁ መሰረት፤ የኢዴፓ ማዕከላዊ ምክር ቤት አባል በሆኑት በአቶ ሙጬ አድማስ የተመራው ቡድን በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም እና ጎንደር ተንቀሳቅሷል፡፡ ቡድኑ በተለይም በሰሜን ጎንደር ባደረገው እንቅስቃሴ፤ በጎንደር ከተማ፣ በጭልጋ፣ በደባርቅ፣ በዳባት፣ በአምባ ጊዮርጊስ፣ በቆላ ድባ፣ በደልጊ እና በሻውራ ወረዳዎች በመዘዋወር ከነባርና ከአዳዲስ አባላት ጋር በመሆን ፓርቲውን ሲያደራጅና የምርጫ ዝግጅቱ እንዲሟላ ሲያደርግ ቆይቶ መመለሱን አቶ ነፃነት ገልጸዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በደቡብ ክልል የተንቀሳቀሰው በአቶ ገብሬ ቱቾ እና በአቶ ገብረመድህን ቴቃ የተመራ ቡድን በወላይታ፣ በዳውሮ፣ በጌዲዮና በሲዳማ ዞኖች በመዘዋወር ነባር አባላትን በማሰባሰብና አዳዲስ አባላትን በመመልመል ለምርጫ ዝግጅቱ የሚረዳ ሥራ ሲያከናውን መቆየቱን አቶ ነፃነት ጠቅሰው፤ በደቡብ ወሎ፣ በሰሜን ሸዋ፣ በድሬዳዋ፣ በምስራቅና በምዕራብ ሐረርጌ ተመሳሳይ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለምርጫው ዝግጅት ለማድረግና ፓርቲውን ለማጠናከር የተንቀሳቀሱት እነዚህ ቡድኖች በፈጠሩት መድረክ ላይ የተገኙ ወደ ሌላ ፓርቲ ሄደው የነበሩ ነባር የኢዴፓ አባላት፣ በተደረገላቸው ማብራሪያ ስለፓርቲው በቂ መረጃና ግንዛቤ በማግኘታቸው ወደ እናት ፓርቲያቸው እየተመለሱ መሆኑን አቶ ነፃነት ጠቅሰው፣ ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ በዳውሮ ዞን የሚገኙ አባላት የላኩትን ቃለ ጉባዔና ደብዳቤ በዋቢነት አቅርበዋል፡፡ (ቅጂው ከዚህ ዜና ጋር ተያይዞ ቀርቧል)

በአጠቃላይ፤ የኢዴፓ አመራር ባስቀመጠው አቀጣጫ መሰረት በማዕከልና በየክልሉ ባሉ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች አማካይነት የሚደረገው ዝግጅት ተጠናክሮ መቀጠሉን አቶ ነፃነት ገልጸው፣ በደሴ እና በጎንደር ተዘግተው የነበሩትን የኢዴፓ ጽ/ቤቶች እንደገና ለመክፈት አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት በመሟላት ላይ ነው ብለዋል፡፡

በዳውሮ ዞን ከሚገኙ የቀድሞ የኢዴፓ አባላት የተጻፈ ደብዳቤ

በዳውሮ ዞን ከሚገኙ የቀድሞ የኢዴፓ አባላት ለአንድነት ፓርቲ የተጻፈ የመልቀቂያ ደብዳቤ

በዳውሮ ዞን በሚገኙ የቀድሞ የኢዴፓ አባላትና በልዑካን ቡድኑ መካከል የተደረገ ውይይት ቃለ ጉባዔ

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter