ኢዴፓ ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ለምርጫው ያለውን ዝግጅት ገለጸ፤ መድረክ ከኢዴፓ ላይ እጁን እንዲሰበስብ አሳሰበ

Ethiopian Democratic Party Press Conferenceየኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ዛሬ ከቀትር በኋላ በግዮን ሆቴል በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ “ምርጫው የሕዝቡ ትክክለኛ ውሳኔ የሚከበርበት፣ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሊሆን ይገባል” ሲል አሳሰበ፡፡ ጋዜጣዊ መግለጫው በዋናነት ያተኮረው በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም የሚካሄደውን አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በተመለከተ ሲሆነ፤ ከገዥው ፓርቲ ጋር ስለተደረገው ድርድርና ስለተገኘው ውጤትም ጠቅሷል፡፡

በኢዴፓ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ በንባብ ከቀረበ በኋላ፤ ከመንግስት የመገናኛ ብዙሃንና ከግል ፕሬስ ጋዜጠኞች ለቀረቡ ጥያቄዎች የፓርቲው አመራር አባላት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በዚሁ ወቅት “መድረክ ሰሞኑን በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ኢዴፓ ‘የተቀዋሚዎች ተቃዋሚ ሆኖ እያጠቃን ነው’ ተብላችኋልና ምላሻችሁ ምንድን ነው?” የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦ፤ “መድረክ በአንድ በኩል ከኢህአዴግ ጋር የተፈራረሙት ፓርቲዎች ደካሞች ናቸው ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኢዴፓ አጠቃኝ የሚል ክስ በማቅረብ ከራሱ ጋር ሲቃረን ይታያል፡፡… የሆነ ሆኖ በኢዴፓ በኩል ከመድረክ ለሚሰነዘር ጥቃት ምላሽ ከመስጠት ውጪ እስከ አሁን ድረስ ምንም ዓይነት የትንኮሳ እርምጃ አልተወሰደም፡፡ እናም፤ መድረክ እራሱ ቀድሞ እየተነኮሰ ምላሽ ሲሰጠው ኢዴፓ አጠቃኝ የሚል ክስና ወቀሳ ማቅረቡ ‘እኔ ብቻ እንደፈለግኩ ልናገር፤ እናንተ ዝም በሉ’ የሚል ከዴሞክራሲ አስተሳሰብ ውጭ የሆነ አስተሳሰብ ነው፡፡… በኢዴፓ በኩል መድረክን አንደርስበትም፡፡ እርሱም እጁን እንዲሰበስብ ሊነገረው ይገባል” የሚል ምላሽ ተሰጥቷል፡፡

ለሦስት ሰዓታት ያህል በቆየው በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ በርካታ ጋዜጠኞች ተገኝተው የተለያዩ ጥያቄዎችን ማቅረባቸው ታውቋል፡፡

(የጋዜጣዊ መግለጫው ሙሉ ቃል ተያይዞ ቀርቧል)

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter