የኢዴፓ አመራር ከአውሮጳ አምባሳደሮች ቡድን ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተወያየ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) አመራር አባላት ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ከሆኑ የአውሮጳ አገራት አምባሳደሮች የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ቡድን ጋር ህዳር 4 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀትር በኋላ መነጋገራቸውን ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡
ከምዕራባውያኑ አምባሳደሮች የሰብአዊ መብትና የዴሞክራሲ ቡድን ጋር ኢዴፓን በመወከል የተወያዩት የፓርቲው ፕሬዝዳንት አቶ ልደቱ አያሌው እና ምክትል ፕሬዝዳንቷ ወ/ሮ ሶፍያ ይልማ ሲሆኑ፤ ከምዕራባውያኑ ወገን የስድስት አገሮች አምባሳደሮች መሆናቸው ታውቋል፡፡

የኢዴፓ አመራርና የምዕራባውያኑ ዲፕሎማቶች የሰብአዊ መብትና የዴሞከራሲ ቡድን የተነጋገሩበት አጀንዳ፤ አራቱ ፓርቲዎች ስለተፈራረሙበት ሰነድ የድርድር ሂደት፣ መድረክ የተሰኘው የፓርቲዎች ስብስብ በድርድሩ ያልተሳተፈበትን ምክንያት በተመለከተ ኢዴፓ ያለውን እይታ እና በመጪው ግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገራዊና ክልላዊ የምክር ቤቶች ምርጫ ኢዴፓ እያደረገው ያለውን ዝግጅትና ያጋጠሙ ችግሮችን በተመለከተ እንደነበር ጽ/ቤቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በኢዴፓና በምእራባውያኑ ዲፕሎማቶች መካከል የተደረገው ግንኙነትና ውይይት ገንቢና በመግባባት መንፈስ የተካሄደ እንደነበር ጽ/ቤቱ ገልፆ፣ በቀጣይም ግንኙነቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል መግባባት ላይ መደረሱን አታውቋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter