በመቀሌ የሚገኙ አባላቱ መልቀቃቸውን እንደማያውቅ ኢዴፓ አስታወቀ

በመቀሌ የሚገኙ የኢዴፓ አባላት ከፓርቲው መልቀቃቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ የአማርኛው ዝግጅት ክፍል በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል ፡፡ ይህንን ጉዳይ አስመልክቶ የፓርቲው ጽ/ቤት በሰጠው ማብራሪያ፤ “ፓርቲው ባለው ደንብ መሰረት አንድ አባል የሚለቅበትም ሆነ አባል የሚሆንበት የአሰራር ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ በዚህ የአሰራር ሥርዓት መሰረት ‘ለቀቁ’ የተባሉት አባላቱ መልቀቃቸውን ማስታወቅ የሚገባቸው ለፓርቲው እንጂ ለቪኦኤ አይደለም” በማለት የፓርቲው ጽ/ቤት ገልፆ፤ “አንድ ለሕዝብ መብትና ጥቅም እታገላለሁ የሚል ሰው በቅድሚያ የሚጠበቅበት ነገር የፓርቲ ዲስፕሊን መርሆዎችን ማክበር መሆን አለበት፡፡ ዛሬ የወጡበትን ፓርቲ ዲስፕሊን ካላከበሩ ነገ አባል የሚሆኑበትን ፓርቲ ደንቦች ስለማክበራቸው እርግጠኛ መሆን አይቻልም” በማለት አብራርቷል፡፡
በፓርቲው የዲስፕሊንና የአሰራር ሥርዓት መሰረት በመቀሌ የሚገኙ የኢዴፓ አባላት መልቀቃቸውን የሚገልጽ መረጃ ያልደረሰው መሆኑን ጽ/ቤቱ አስታውቆ፣ “ቪኦኤ ባቀረበው መሰረት አባላቱ ኢዴፓን ለቀውም ከሆነ፣ ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ሊያቆመው የማይቻለው መብታቸው ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት የአባላት ከአንዱ ፓርቲ ወደ ሌላው የመሸጋገር ሁኔታም በምርጫ ወቅት ተደጋግሞ የታየ ነው” ብሏል፡፡

የአባላት መውጣትና መግባት ሕይወት ባለው ፓርቲ ውስጥ የሚጠበቅ መሆኑንና ወደፊትም ከኢዴፓ የሚለቁም ሆነ ወደ ኢዴፓ የሚቀላቀሉ አባላት የመኖራቸው ሁኔታ “አይቀሬ” መሆኑን ጽ/ቤቱ አስታውቆ፤ “ይህ ማለት ግን አባላት ከፓርቲው ስለለቀቁ የፓርቲው እንቅስቃሴ በትግራይ ክልል ቆሟል ማለት እንዳልሆነ” አስገንዝቧል፡፡

ኢዴፓ በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰፊ የምርጫ ዝግጅትና የዕጩዎች ምልመላ እያደረገ ሲሆን፣ የዓላማ ጽናት ያጡ አንዳንድ አባላቱ መውጣትም የፓርቲውን እንቅስቃሴ የማይገታውና የበለጠ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን የኢዴፓ ጽ/ቤት ጨምሮ ገልጿል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter