ፓርቲዎች የተደራደሩበት ሰነድ አዋጅ ሆኖ በፓርላማ ፀደቀ

በቅድሚያ በአራት ፓርቲዎች በኋላም በስልሳ አምስት ፓርቲዎች ድርድር ተደርጎበት የሀገሪቱ የምርጫ ህጎች አካል ይሆን ዘንድ በአዋጅ እንዲወጣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ሰነድ “የፖለቲካ ፓርቲዎችን የምርጫ ሥነ-ምግባር ለመደንገግ የወጣ አዋጅ” በሚል ርዕስ በምክር ቤቱ የፀደቀ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።
ይኸው ሰነድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ጽ/ቤት አማካይነት የህግ ቅርፅ ተሰጥቶትና የእንግሊዝኛ ትርጉም ተዘጋጅቶለት ህዳር 24 ቀን 2002 ዓ.ም ለመጀመሪያ ንባብ ለፓርላማ መቅረቡን የዜና ምንጩ አስታውሶ፤ በዕለቱ በምክር ቤቱ ውይይት ተደርጎበት ለዝርዝር እይታ ለሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ መመራቱን ገልጿል።

የምክር ቤቱ የሕግና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴም በተመራለት ረቂቅ ሕግ ላይ ባለው አሰራር መሰረት የሕዝብ አስተያየት መስጫ መድረክ በማዘጋጀት አስተያየቶችን ካሰባሰበ በኋላ ሰነዱን በጥልቀት በመመርመር መጠነኛ ማሻሻያዎችንና ማስተካከያዎችን በማድረግ የውሳኔ ሃሳቡን ለምክር ቤቱ አቅርቧል ሲል የዜና ምንጩ ዘግቧል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም ከቋሚ ኮሚቴው በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ በዛሬው ዕለት (ታህሳስ 13 ቀን 2002 ዓ.ም) ውይይት በማድረግ አዋጁን በአብላጫ ድምፅ ያፀደቀው መሆኑ ታውቋል። ይህ አዋጅ የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከፈረሙበትና በነጋሪት ጋዜጣ ከታተመበት ዕለት ጀምሮ በሥራ ላይ እንደሚውል ይጠበቃል።

በኢዴፓ በኩል፣ “ይህ አዋጅ ለረጅም ጊዜ ተደራድረን የተስማማንበት በመሆኑ፣ አዋጁ በጉልበት ስልጣን ላይ እወጣለሁ የሚልንም ሆነ የሕዝብን ድምፅ ወደ ጎን በመግፋት ከያዝኩት ሥልጣን አልወርድም የሚልን አካል የሚከላከል በመሆኑ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመከባበርና እውቅና (Recognition) በመሰጣጠት ለሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል ዋስትና የሚሰጥና የሀገሪቱንም ፖለቲካ ለዘመናት ጠፍሮ ከያዘው ፍጥጫ ወደ ድርድርና ውይይት ደረጃ ከፍ የሚያደርገው በመሆኑ፣… ይህንን አዋጅ የምንቀበለው ነው” የሚል አስተያየት በማቅረብ ለአዋጁ ያለውን ድጋፍ መግለጹን የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter