ኢዴፓ የስም ለውጥ ሰርተፊኬቱን ከምርጫ ቦርድ ተቀበለ

ቀደም ሲል “ኢዴአፓ – መድህን” በሚል ስያሜ ይጠራ የነበረው ፓርቲ ባለፈው ዓመት በጥር ወር ባካሄደው አራተኛ ድርጅታዊ ጠቅላላ ጉባዔ የመተዳደሪያ ደንብ ማሻሻያ በማድረግ ፓርቲው፤ “የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)” በሚል ስያሜ እንዲጠራ የስም ለውጥ ውሳኔ ማሳለፉ ይታወቃል።
የፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ባሳለፈው ውሳኔ መሰረትም፣ ቀደም ሲል የነበረው የፓርቲው የሕጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ተመላሽ ሆኖ በአዲሱ ስያሜ የህጋዊ ሰውነት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲሰጠው የፓርቲው ጽ/ቤት ለቦርዱ ጽ/ቤት ጥያቄ አቅርቦ ጉዳዩን ሲከታተል እንደነበር ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመልክቷል።

የስም ለውጥ ምዝገባ ጥያቄው ባለፈው ዓመት በየካቲት ወር መቅረቡን የመረጃ ምንጩ አስታውሶ፣ የቦርዱ ጽ/ቤት የቀረበለትን ጥያቄ አይቶ ተለዋጭ ሰርተፊኬቱን ለመስጠት በአዲሱ የፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ መሰረት መሟላት የሚገባቸው ሰነዶች እንዲቀርቡ በደብዳቤ ማስታወቁን ገልጿል።

የስም ለውጥ ጥያቄው በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት ቆይቶ ታህሳስ 6 ቀን 2002 ዓ.ም ከቦርዱ ጽ/ቤት የተሰጠ መሆኑም ታውቋል። ስለሆነም፣ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ “ኢዴፓ” የሚለው ስያሜ ሕጋዊ እውቅና ያገኘ በመሆኑ “ኢዴአፓ – መድህን” የሚለው ስም በታሪክ ማህደር ውስጥ ሰፍሮ የሚቀመጥ ይሆናል ሲል ከስፍራው የተላከልን መረጃ አመልክቶ፣ ከዚህ ጊዜ በኋላ ከፓርቲው ጋር ማንኛውንም ግንኙነት የሚያደርግ አካልም “ኢዴፓ” በሚለው ስም እንዲጠቀም አሳስቧል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter