የኢዴፓ አመራር አባላት በተለያዩ የምርጫ ክልሎች በዕጩነት እየተመዘገቡ ነው፤ አቶ ልደቱ ዛሬ ተመዘገቡ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ፣ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት ሰባ አምስት በመቶ በሚሆነው አካባቢ ዕጩ ተወዳዳሪዎችን ለማቅረብ ካለፈው ሐምሌ ወር 2001 ዓ.ም ጀምሮ ዝግጅት ሲያደርግና የማደራጀት ስራ ሲያከናውን ከርሞ ዕጩ ማስመዝገብ መጀመሩን ከፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ያገኘነው መረጃ አመለከተ።

በዚሁ መሰረት፣ እስከ አሁን ድረስ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ የኢዴፓ ዕጩዎች የተመዘገቡ መሆኑ ታውቋል። የፓርቲው አመራር አባላትም በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች እየተመዘገቡ ሲሆን፤ ሊቀ መንበሩ አቶ ልደቱ አያሌው በዛሬው ዕለት በሰሜን ወሎ ዞን በቡግና ወረዳ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው መመዝገባቸው ታውቋል። አቶ ልደቱ ወደተወለዱበት አካባቢ ሄደው መወዳደርን የመረጡት የአካባቢው ህብተሰብ “ኢህአዴግን መምረጥ ሰልችቶናል” በማለት ተወዳዳሪ ሆነው እንዲቀርቡ ባደረገላቸው ጥሪ ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ ለፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ ለአቶ መስፍን መንግስቱ የተወለዱበት የጋሞ ማህበረሰብ ባደረገላቸው ጥሪ መሰረት በደቡብ ክልል በአርባ ምንጭ ዙሪያ ወረዳ ለመወዳደር መመዝገባቸው ታውቋል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ የኢዴፓ ምክትል ሊቀ መንበር ወ/ሮ ሶፍያ ይልማ ዴሬሳ እና ዋና ፀሐፊው አቶ ሙሼ ሰሙ በአዲስ አበባ የሚመዘገቡ ሲሆን፤ የፓርቲው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት የሆኑት ወ/ሪት ፅጌ ጥበቡ በኦሮሚያ ክልል በዓለም ገና ወረዳ፣ አቶ ደረጀ ደበበ በድሬዳዋ፣ አቶ ሙጬ አድማስ በባህር ዳር፣ አቶ አለማየሁ ባልዳ በሐረሪ ክልል እንዲሁም መቶ አለቃ ቦጋለ አበበ በኦሮሚያ ክልል በአርሲ መመዝገባቸውን የዜና ምንጩ ገልፆ፤ በቀጣይ ቀናትም የዕጩዎች ምዝገባው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል።

አባላትን የማደራጀቱና የዕጩ ምልመላው ስራ በበርካታ መሰናክሎች የተተበተበና ፈታኝ እንደነበር የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ አስታውቆ፣ ይሁን እንጂ ፓርቲው ያስቀመጠውን ግብ ለማሳካት ብርቱ ጥረት ተደርጓል ብሏል። የኢዴፓ ዕጩዎች፣ የማስመዝገቢያው ዕለት መጠናቀቂያ ሲቃረብ እንዲመዘገቡ የተደረገውም በሂደቱ የታዩት ችግሮች ተባብሰው የከፋ ችግር እንዳያጋጥም ነው ሲል የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter