የኢዴፓ አጀንዳ በፓርላማ እንዳይቀርብ ኢህአዴግና ህብረት ተቃወሙ

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ በመጣው የነዳጅ ዋጋና ከዚሁም ጋር ተያይዞ እየናረ በመጣው የኑሮ ውድነት ዙሪያ ፓርላማው “በተቀዋሚዎች ቀን” እንዲመክርበት ኢዴፓ አጀንዳ ማቅረቡ ይታወሳል። ይኸው አጀንዳ በምክር ቤቱ የአሰራር ደንብ መሰረት በጥር ወር የመጨረሻ ሳምንት ማክሰኞ በሚካሄደው የም/ቤቱ መደበኛ ስብሰባ እንደሚቀርብ ቀደም ሲል ቅንጅት ያቀረበው አጀንዳ በታህሳስ ወር እንዲቀርብ በተወሰነበት ወቅት ስምምነት የተደረሰበት ቢሆንም፤ ኢህአዴግና ህብረት ባቀረቡት ተቃውሞ የኢዴፓ አጀንዳ እንዳይቀርብ መደረጉን በፓርላማ የኢዴፓ ተጠሪ የሆኑት አቶ አብዱራህማን አህመዲን አስታውቀዋል።

ሰኞ ጥር 24 ቀን 2002 ዓ.ም በተካሄደው የምክር ቤት ጉዳዮች አማካሪ ኮሚቴ በኩል አጀንዳው ፀድቆ ቀደም ሲል በተደረገው ስምምነት መሰረት በም/ቤቱ ውይይቱ እንዲካሄድ ጥያቄ ማቅረባቸውን አቶ አብዱራህማን ገልጸው፤ ይሁን እንጂ በኢህአዴግ በኩል “በአሁኑ ወቅት በርካታ የኢህአዴግ አባላት በተለያዩ ስራዎች የተጠመዱ በመሆኑና አጀንዳው የሚቀርብ መሆኑ በም/ቤቱ ደንብ መሰረት ከ48 ሰዓታት ቀድሞ ስላልተነገረን ዝግጅት አላደረግንም” በሚል ሰበብ ተቃውሞ መቅረቡን አስታውዋል።

በፓርላማ የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ህብረት) ተጠሪ የሆኑት አቶ ገብሩ ገ/ማሪያም በበኩላቸው “ባለፉት ወራት ኢህአዴግ በነዳጅ ዙሪያ በርካታ ማስተካከያዎችን ስላደረገ ችግሩ ተቀርፏል። የኑሮ ውድነቱም በመንግስትና በኢህአዴግ ጥረት እየተወገደ ስለሆነ ይህ አጀንዳ ‘irrelevant’ (አላስፈላጊ) ነው። የተቃዋሚ አጀንዳ ሆኖ ሊቀርብ አይገባውም” የሚል አስተያየት ሰጥተው የኢዴፓ አጀንዳ እንዳይቀርብ ከኢህአዴግ ጋር ወግነው መቃወማቸውን አቶ አብዱራህማን አብራርተዋል።

በኢዴፓ በኩል ይህ አጀንዳ የቀረበው ህዳር 1 ቀን 2002 ዓ.ም ቢሆንም፤ የተለያዩ ምክንያቶች እየቀረቡ እስከ አሁን ድረስ መጓተቱ ተገቢ አለመሆኑንና አጀንዳው “አላስፈላጊ ነው” የሚሉ ወገኖችም ቢሆኑ ይህንኑ ሃሳባቸውን ውይይት በሚደረግበት ወቅት ማቅረብ እንጂ “አጀንዳው ለውይይት አይቅረብ” ማለት የማይገባቸው መሆኑን በመጥቀስ መከራከራቸውን አቶ አብዱራህማን ገልጸዋል።

“በመንግስት በኩል ባለፉት ወራት ተከታታይ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ በማድረጉ የኑሮ ውድነቱ በተገቢው መጠን ሊረጋጋ አልቻለም። ይባስ ብሎ ሰሞኑን የዶላርና የብር የምንዛሬ መጠን ማስተካከያ በመደረጉ ይህም ለኢኮኖሚ አለመረጋጋቱ ተጨማሪ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው ይገመታል። እናም በኢህአዴግ በኩል በጉዳዩ ላይ መክሮ ተገቢውን የመፍትሄ እርምጃ ከመውሰድ ይልቅ አጀንዳውን መሸሽን እንደ ጠቃሚ ስልት እየተጠቀመበት ነው” በማለት አቶ አብዱራህማን አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። አያይዘውም፤ “ኢህአዴግና የመድረክ አባል ድርጅት የሆነው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ህብረት (ህብረት) ይህ አንገብጋቢ የህዝብ አጀንዳ በፓርላማው ውይይት እንዳይደረግበት መቃወማቸው ለሕዝብ ጥያቄና ብሶት ያላቸውን ንቀት ያሳያል” ብለዋል። “ኢዴፓ ሕዝባዊ አጀንዳዎችን እየፈለፈለ በማውጣት የታወቀ ስለሆነ ‘የአጀንዳ ድርቅ’ የለበትም። ይህንንም ይሁን ሌሎች አጀንዳዎችን ቀርፀን በቀጣይ ወራት ለፓርላማው እናቀርባለን” በማለት አቶ አብዱራህማን ጨምረው ገልጸዋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter