ልዩ ዐቃቤ ሕግ የመጨረሻ ሪፖርቱን ሲያቀርብ ኢዴፓ “የነጭ ሽብርን” ጉዳይ አነሳ

የአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘውዳዊ አገዛዝ ከተገረሰሰ በኋላ እስከ ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም ድረስ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር የነበረው የደርግ ወታደራዊ ሥርዓት ባለስልጣናት የፈጸሟቸውን “የቀይ ሽብር” ወንጀሎች እንዲያጣራና ለፍርድ እንዲያቀርብ ኃላፊነት ተሰጥቶት በ1984 ዓ.ም በኢህአዴግ የሽግግር መንግስት ዘመን ተቋቁሞ የነበረው የልዩ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ሥራውን አጠናቆ የመጨረሻ ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማቅረቡን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።
ጽሕፈት ቤቱ ለፓርላማ ባቀረበው ሪፖርቱ፤ 5119 የደርግ ባለስልጣናት መከሰሳቸውን፣ ከእነዚህ ውስጥ 3583 ጥፋተኛ ተብለው በሞት በዕድሜ ልክና በተለያዩ ዓመታት የእስራት ቅጣት የተጣለባቸው መሆኑን፣ 656 ሰዎች ታስረው ሲከራከሩ ከቆዩ በኋላ በነፃ መሰናበታቸውን፣ በክሱም ሂደት 8047 የሰውና 15214 ገጽ ያለው የሰነድ ማስረጃ መቅረቡን ወዘተ. አብራቷል።

የደርግ ባለስልጣናቱ የፈጸሙት ወንጀል “የዘር ማጥፋት” (Genocide) መሆኑ በፍርድ ቤት መረጋገጡን የልዩ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ባቀረበው ሪፖርቱ ገልፆ፤ ጥፋተኛ ተብለው በተለያዩ ዓመታት ቅጣት ከተፈረደባቸው ውስጥ ሰማንያ በመቶ (80%) የሚሆኑት ቅጣታቸውን አጠናቀው ወደ ህብረተሰቡ ተቀላቅለው በሰላም በመኖር ላይ መሆናቸውን ገልጿል።

የኢህአፓ አባል የነበሩትና በደርግ ስርዓት ከፍተኛ ግፍ እንደተፈጸመባቸው የሚነገርላቸው የልዩ ዐቃቤ ሕግ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ግርማ ዋቅጅራ፣ ሪፖርቱን ካቀረቡ በኋላ በምክር ቤቱ መቀመጫ ያላቸው ፓርቲዎች አባላት አስተያየትና ጥያቄ አቅርበዋል። በዚሁ መሰረት በኢዴፓ በኩል፤ “… በሪፖርቱ ላይ 656 ያህል ሰዎች በቀይ ሽብር ወንጀል ተጠርጥረው ለአስርና ከዚያም በላይ ዓመታት ታስረው በነፃ መለቀቃቸው ተገልጿል። እነዚህ ሰዎች ለበርካታ ዓመታት መታሰራቸው አግባብ ነው ወይ? …ያለ ጥፋታቸው ለታሰሩበት የሚካሱት በምንድን ነው?… በሪፖርቱ ላይ ‘በቀይ ሽብር’ ወንጀለኞች ላይ መጣራት ተደርጎ በፍ/ቤት መቀጣታቸው ተገልጿል። በወቅቱ ግን ‘የነጭ ሽብር’ አራማጆች እንደነበሩም ይታወቃል። ‘የነጭ ሽብር’ ጥፋተኞችንስ ጉዳይ ለምን አላጣራችሁም? ይህስ በታሪክ ሚዛን ሲሰፈር ትልቅ የፍትህ መጓደል አይሆንም ወይ?… በሪፖርቱ ላይ ጽ/ቤቱ ባለፉት ዓመታት ያከናወናቸውን ተግባራትና የደረሰበትን ድምዳሜ የያዘ መጽሐፍ ተዘጋጅቶ ማተሚያ ቤት እንደገባ ተገልጿል። እርስዎ ደግሞ ‘የቀይ ሽብር’ ተጎጂ መሆንዎ ብቻ ሳይሆን ይህንን ሪፖርት ሲያቀርቡም ሆነ መልስ ሲሰጡ እጅግ ስሜታዊ ሆነው ታይተዋል። ታዲያ ይህ ስሜታዊነትዎ በስራዎ ሂደትም ሆነ ተዘጋጀ በተባለው መጽሐፍ ውስጥ ስላለመንጸባረቁ ምን ማረጋገጫ አለ?…” የሚሉ ጥያቄዎች ቀርበው እንደነበር ከስፍራው የደረሰን መረጃ ጨምሮ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter