በኢዴፓ ሊቀመንበር የተዘጋጀ መጽሐፍ ታተመ

በኢዴፓ ሊቀመንበር በአቶ ልደቱ አያሌው የተዘጋጀ መጽሐፍ ታትሞ የካቲት 11 ቀን 2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል የሚመረቅ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ። በሁለት ዋና ዋና ክፍሎችና በበርካታ ምዕራፎች የተዘጋጀው ይኸው መጸሐፍ፣ ከአምስት መቶ በላይ ገፆች ያሉት መሆኑን የዜና ምንጩ ገልጿል።

መጸሐፉ “መድሎት” በሚል ርዕስ የተዘጋጀ መሆኑን የዜና ምንጩ ጠቅሶ፣ ህትመቱ የተጠናቀቀ በመሆኑ በመጪው ረቡዕ በሚደረገው የምረቃ ሥነ-ስርዓት ላይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንደሚገኙ ይጠበቃል ሲል አስታውቋል።
በአዲስ አበባና አካባቢዋ የሚገኙ የኢዴፓ አባላት ከሐምሌ ወር 2000 ዓ.ም እስከ ታህሳስ ወር 2001 ዓ.ም ድረስ በየሳምንቱ ዕሑድ እየተገናኙ ከ14 በላይ በሆኑ አጀንዳዎች ዙሪያ ተወያይተው የጋራ ግንዛቤ የያዙባቸውንና የተስማሙባቸውን ዋና ዋና ፍሬ ሃሳቦች አቶ ልደቱ አስፋፍተውና በራሳቸው ተነሳሽነት አንዳንድ ተጨማሪ ሃሳቦችን አካተው መጽሐፉን  እንዳዘጋጁት የዜና ምንጩ ገልጿል።

የመጽሐፉ ረቂቅ በሐምሌ ወር መጀመሪያ ለኢዴፓ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት እንደተሰጠና አባላቱ፣ መጽሐፉ አሁን ያለውን ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ ሰፊ አስተያየትና ማሻሻያ እንዳቀረቡ የዜና ምንጩ ጠቅሶ፤ መጽሐፉ የሀገሪቱን አጠቃላይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች በመዳሰስ ኢዴፓ ከሚከተለው የሊበራል ዴሞክራሲ ርዕዮተ-ዓለም አኳያ በመቃኘት አማራጭ አቅጣጫዎችን ማስቅመጡንም የዜና ምንጩ አስታውቋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter