የመጀመሪያው የፓርቲዎች ክርክር ሳይቆራረጥ መቅረቡ ታወቀ

በመጪው ግንቦት ወር አጋማሽ ላይ ለሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ፣ የካቲት 5 ቀን 2002 ዓ.ም በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስቱዲዮ ተቀርፆ የተላለፈው የፓርቲዎች ክርክር ምንም ዓይነት ሳንሱር ሳይደረግበት የቀረበ መሆኑን ከኢዴፓ ጸ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው፤ “ክርክሩን በስቱዲዮ ቀርፆ በሌላ ጊዜ ማሰራጨት የቀጥታ (Live) ስርጭቱን የሚተካ ባይሆንም፤ የመጀመሪያው ክርክር ምንም ዓይነት መቆራረጥ ሳይደረግበት እንዳለ ቀርቧል” ሲሉ ገልጸዋል። አያይዘውም፤ በኢህአዴግ በኩል ክርክሩ በቀጥታ ስርጭት እንዳይተላለፍ የፈለገበት ምክንያት፣ ‘በክርክሩ ሂደት ዘለፋ፣ ስድብና ትንኮሳን የመሳሰሉ አላስፈላጊ ቃላት ሊሰነዘሩ ይችላል’ በሚል ስጋት ቢሆንም፤ በመጀመሪያው የክርክር መድረክ ግን እንዲህ ያለ ሁኔታ አለመከሰቱንና ሁሉም ፓርቲዎች ጨዋነት በተሞላው አኳኋን ሃሳባቸውን ሲያቀርቡ ማስተዋላቸውን አቶ ልደቱ ገልጸዋል።

“ይህም ሁኔታ የሀገራችን ፖለቲካ በሰከነና በሰለጠነ መንፈስ መከናወን መጀመሩን የሚያሳይ በጎ ጅምር ነው” ያሉት አቶ ልደቱ፣ ኢዴፓ በዚህ የመጀመሪያ የክርክር መድረክ የነበረውንም ሚና አብራርተዋል። “ኢዴፓ በክርክር የሚያምን የሀሳብ ጥሬ ሃብት የማያልቅበት ፓርቲ ነው። እናም በእኛ በኩል ለዚህ ምርጫ የክርክር መድረኮች የሚሆን በቂ ዝግጅት አድርገናል። በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ መራጩ ሕዝብ ሃሳባችንን እንዲገዛን አማራጭ ፖሊሲያችንን እናቀርባለን። በመጀመሪያው የክርክር መድረክም በአግባቡ ለመጠቀም ጥረት አድርገናል። ሂደቱን እየገመገምንና ከህብረተሰቡ የሚሰጠንን አስተያየቶች እንደግብዓት እየተጠቀምን በቀጣይ መድረኮችም የበለጠ ለመስራት ጥረት እናደርጋለን” ብለዋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter