መጽሐፉ ተመረቀ፤ “መድሎት” ማለት “መመዘኛ፣ ሚዛን” ማለት ነው

የኢዴፓ ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው “መድሎት” በሚል ርዕስ ያዘጋጁት የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮች የሚዳስስ መጽሐፍ ረቡዕ የካቲት 10 ቀን 2002 ዓ.ም በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል መመረቁን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።

ባለፈው ሳምንት መጠናቀቂያ አካባቢ የወጡ የአገር ውስጥ ጋዜጦች “አወዛጋቢው አቶ ልደቱ አነጋጋሪ መጽሐፍ ጻፉ” በሚል ርዕስ ጭምር በፊት ለፊት ገፆቻቸው የተለያዩ ዘገባዎችንና አስተያየቶችን መጻፋቸውን የዜና ምንጩ ጠቅሶ፤ በመጽሐፉ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በርካታ ጋዜጠኞች፣ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ታዋቂ ግለሰቦች መገኘታቸውን አስታውቋል።

አቶ ልደቱ መጽሐፉን ባስተዋወቁበት የመጽሐፉ መግቢያ ላይ፤ “አብዛኛዎቹ በመጽሐፉ ውስጥ ተብራርተው የቀረቡት አቋሞችና ትንታኔዎች ኢዴፓ በ4ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔው በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያስተላለፋቸውን ውሳኔዎች ከሞላ ጎደል መነሻ በማድረግ የቀረቡ ናቸው። ኢዴፓ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያዘጋጃቸውን ሰነዶችም በምንጭነት” አቶ ልደቱ መጠቀማቸውን የዜና ምንጩ ጠቅሶ፤ ይሁን እንጂ “በአጠቃላይ በአገራዊ አጀንዳዎች ላይም ሆነ በፖለቲካ ጉዳዮች ላይ የሚኖረኝ ግምገማ ከኢዴፓ አቋም ጋር ቁርኝት ያለው ቢሆንም፤ ነገር ግን ፓርቲው አቋም ባልወሰደባቸው የተለያዩ ጉዳዮች ላይ የራሴን አቋሞች የገለጽኩበት ሁኔታ ስላለና አንባቢም የእኔንና የፓርቲውን አቋሞች ለያይቶ ለማወቅ ስለሚቸገር በመጽሐፉ ውስጥ ለሰፈሩት ሃሳቦች በሙሉ ተጠያቂ የምሆነው እኔ እንጂ ኢዴፓ አይደለም” ማለታቸውንም አብራርቷል።

በምረቃው ስነ ስርዓት ላይ የኢትዮጵያ ደራስያን ማህበር ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው በለጠ፣ የፎርቹን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ታምራት ገ/ጊዮርጊስ፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር መሐመድ ሐቢብ፣ የሕግ ባለሙያው አቶ ሞላ ዘገዬ እና የታሪክ ተመራማሪው ዶ/ር ላጲሶ ጌታሁን ዴሌቦ በየተራ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አቶ ልደቱ ባሰሙት የማጠቃለያ ንግግር “እኔ ዛሬ የምናገረው ነገር አይኖረኝም። ያሰብኩትንና መናገር የሚገባኝን ሁሉ በመጽሐፉ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል። በመጽሐፉ ውስጥ በርካታ አከራካሪ ጉዳዮች የተነሱ በመሆኑ ከአንባብያን አሉታዊም አዎንታዊም አስተያየቶች መምጣታቸው የሚጠበቅ ነው። የእኔ ፍላጎት ሁሉም ዜጋ በሰከነና በሰለጠነ መንፈስ ራሱን እንዲፈትሽ፣ እንዲነጋገርበትና እንዲወያይበት መነሻ የሚሆን ሃሳብ ማቅረብ ነው” ብለዋል።

ኢዴፓ አቋም በያዘባቸው ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ከአቶ ልደቱ መጽሐፍ አለፍ አለፍ እያልን እየቆነጠርን በዚህ ዌብሳይት ላይ ለማቅረብ ጥረት የምናደርግ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ ለመግለጽ እንወዳለን።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter