የኢዴፓ የምርጫ ማንፌስቶ ማክሰኞ ይፋ ይሆናል

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ውድድር በዋናነት የሚያነሳቸውን የመከራከሪያ አጀንዳዎች፣ ፖሊሲዎችና ስልቶች የያዘ የምርጫ ማንፌስቶ በመጪው ማክሰኞ ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርግ ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ።
ከፓርቲው ጽ/ቤት ባገኘነው መረጃ መሰረት፣ በሃያ ሰባት ገፆች ተጠቃሎ የቀረበው የኢዴፓ የምርጫ ማንፌስቶ ማክሰኞ የካቲት 23 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀኑ በ9፡00 ሰዓት በግዮን ሆቴል በሚያካሂደው ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንደሚደረግ ታውቋል።

ኢዴፓ ባዘጋጀው ማንፌስቶ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የፓርቲው ቀዳሚ አጀንዳዎች መሆናቸውንና በዚህም ረገድ፤ የኑሮ ውድነት፣ የሥራ ዕድልና ድህነትን ቅነሳ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ታውቋል። ኢዴፓ በሁለተኛ ትኩረት የሰጠው ለማህበራዊ ጉዳዮች ሲሆን፤ በዚህም ዙሪያ ትምህርት፣ ጤና፣ መልካም አስተዳደር፣ ሙስናና የመኖሪያ ቤት ቀዳሚ ትኩረት ይሰጣቸዋል ተብሏል። በሦስተኛ ደረጃ ኢዴፓ ትኩረት የሰጠው ለፖለቲካዊ ጉዳዮች ሲሆን፤ በዚህም በኩል ሰላምና መረጋጋት፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ሰብአዊ መብትና ሕገ መንግስታዊ ማሻሻያን እንደሚጨምር የዜና ምንጩ አስታውቋል።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የምርጫ ማንፌስቶ አዘጋጅቶ ለምርጫ ውድድር የቀረበ ፓርቲ ኢዴፓ ሲሆን፤ ይህንንም ማንፌስቶ አባል ለሆነበት ለቅንጅት ሰጥቶ፣ በ1997 በተካሄደው ምርጫ ቅንጅት አግልግሎት ላይ ያዋለው መሆኑ ይታወቃል።

በአምስት ክፍሎችና በበርካታ ንዑሳን ክፍሎች የተዘጋጀው የኢዴፓ ማንፌስቶ እንደደረሰን በፓርቲው ዌብሳይት ላይ የምንጭነው መሆኑን ከወዲሁ እንገልጻለን።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter