ኢዴፓ በ305 ወረዳዎች ዕጩዎችን አቀረበ

ከምርጫ 97 ወዲህ በሕዝብ እንደተጠላ፣ ዳግም ላያንሰራራ ሞቶ እንደተቀበረና አንድም አባል እንደሌለው አሉባልታ ሲወራበትና ሲሟረትበት የከረመው የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመጪው ግንቦት ወር 2002 ዓ.ም በሚደረገው አገር አቀፍ ምርጫ በሦስት መቶ አምስት ወረዳዎች እንደሚወዳደር ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።
የሶማሌ ክልልን ሳይጨምር በሚካሄደው በዘንድሮው ምርጫ፤ ኢዴፓ ከሀገሪቱ የቆዳ ስፋት 75% በሚሆነው አካባቢ (በ393 ወረዳዎች) እጩዎችን የማቅረብ ግብ እንደነበረው የዜና ምንጩ አስታውሶ፣ ካለፈው ሀምሌ ወር ጀምሮ ባደረገው መጠነ ሰፊ ዝግጅት በ305 ወረዳዎች የሚወዳደሩ ዕጩዎችን ለማቅረብ ችሏል ሲል አስታውቋል። ይህም ፓርቲው አሳካዋለሁ ብሎ ካስቀመጠው ግብ 78% እንደሆነ የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።

በእነዚህ የፓርቲው ዕጩዎች ላይ ከተመዘገቡበት ዕለት ጀምሮ እስከ አሁን ድረስ ያልተቋረጠ ማስፈራራት፣ ማዋከብና እጩነታቸውን እንዲሰርዙ ከፍተኛ ግፊት እየተደረገባቸው መሆኑን የዜና ምንጩ ጠቅሶ፣ “ገዥው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን አንዳንድ ተቃዋሚዎች ጭምር በፓርቲው ማንሰራራትና እንቅስቃሴ እጅግ ተደናግጠዋል” ሲል የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።

አንድ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር በበኩላቸው “መመዝገብ ብቻ ሳይሆን እነዚህ እጩዎች አሸናፊ እንዲሆኑ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን” ማለታቸውንም የዜና ምንጩ አስታውቋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter