ሦስተኛው ዙር የፓርቲዎች ክርክር መጋቢት 3 ይካሄዳል ተባለ

ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ በገዢው ፓርቲ እና በተቀዋሚ ፓርቲዎች መካከል የሚደረገው ሦስተኛ ዙር ክርክር ዓርብ መጋቢት 3 ቀን 2002 ዓ.ም እንደሚካሄድ ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።
ይኸው ክርክር “ሰብአዊ መብት፣ መልካም አስተዳደርና የሕግ የበላይነት” በሚል ርዕስ ዙሪያ እንደሚካሄድ የዜና ምንጩ ገልጿል። ይህ ክርክር በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ስቱዲዮ ተቀርፆ እንደሚተላለፍ ታውቋል።

በፓርቲዎች መካከል ክርክር ሊደረግባቸው የተመረጡት ርዕሶች አስር ናቸው። እነሱም፤

•    ምርጫና የመድብለ ፓርቲ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ፣
•    የኢኮኖሚ ዕድገት በኢትዮጵያ ባለፉት 18 ዓመታት፣
•    የግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት ከየት ወደየት፣
•    ባለፉት 18 ዓመታት የከተሞችና የኢንዱስትሪ ልማት፣
•    የመሰረተ ልማት ግንባታ በኢትዮጵያ፣
•    ትምህርትና ልማት በኢትዮጵያ ባለፉት 18 ዓመታት፣
•    የጤና አገልግሎት በኢትዮጵያ ባለፉት 18 ዓመታት፣
•    መልካም አስተዳደርና ሰብአዊ መብት በኢትዮጵያ፣
•    የፌዴራል ስርዓት ግንባታ በኢትዮጵያ፣
•    ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ፣ በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ግንኙነት፣የሚሉ ናቸው።

እስከ አሁን ድረስ በሁለቱ አጀንዳዎች ዙሪያ ክርክር የተደረገ ሲሆን፣ በቀሪዎቹ ላይ በቀጣይ ጊዜአት ክርክር እንደሚደረግ ታውቋል። ይሁን እንጂ፣ በየትኛው ርእስ ላይ የሚደረገው ክርክር በቀጥታ ስርጭት እንደሚተላለፍ እስከ አሁን ድረስ አልታወቀም።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter