ዓርብ ዕለት በጤና ጉዳይ ላይ ክርክር ይደረጋል የኢዴፓ አባላት በፓርላማ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ አቀረቡ

ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ገዢው ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ክርክር ሊያደርጉ በጋራ ከተስማሙባቸው አስር አጀንዳዎች ውስጥ በአራተኛነት የተመረጠው የጤና ፖሊሲ ዓርብ መጋቢት 10 ቀን 2002 ዓ.ም ክርክር ሊደረግበት መሆኑ ታወቀ።

እስከ አሁን በተደረጉት ክርክሮች የሃሳብ የበላይነቱን እንዳረጋገጠ የሚናገረው ኢዴፓ በዚህኛውም የክርክር መድረክ በተለመደው መልኩ ለየት ያሉ አማራጭ ሃሳቦቹን በማቅረብና የገዢውን ፓርቲ የፖሊሲና የአፈጻጸም ችግሮች በማጋለጥ የነቃ ተሳትፎ እንደሚያደርግ ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመልክቷል።

በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬዲዮ ድርጅት ስቱዲዮ ዓርብ ዕለት በሚደረገው ክርክር በኢዴፓ በኩል የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ሙሼ ሰሙ እና አቶ አብዱራህማን አህመዲን እንደሚገኙ ታውቋል።

ይህ በዚህ እንዳለ፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሰራርና የአባላት ሥነ-ምግባር ደንብ ጠቅላይ ሚኒስትሩን በወር አንድ ጊዜ ለጥያቄ መጥራት እንደሚቻል በደነገገው መሰረት በምክር ቤት ያሉ የኢዴፓ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸው ታወቀ። ጠቅላይ ሚኒስትሩም ዛሬ በሚደረገው የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ተገኝተው መልስ እንደሚሰጡ ይጠበቃል።

በኢዴፓ አባላት የቀረቡት ጥያቄዎች በዋጋ ግሽበትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለመጣው የኑሮ ውድነት እና የመንግስት ሰራተኛውን የደመወዝ ሁኔታ እንዲሁም ለሕዝቡ ሳይገለጽ መብራት በፈረቃ የሚሰራጭበትን የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር በተመለከተ ተጠያቂው ማን ነው የሚል መሆኑም ታውቋል።

በኢዴፓ አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ የቀረቡ ጥያቄዎች

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter