ኢዴፓ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን ሊያካሂድ ነው

ኢዴፓ የ2002 የምርጫ ዘመቻውን በመቀጠል ከሕዝቡ ጋር ለመወያየት በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች ተከታታይ ስብሰባዎችን እንደሚያደርግ ተገለጸ። በዚህም መሠረት አርብ ጠዋት መጋቢት 25 ቀን 2002 ዓ.ም. በሜክሲኮ አደባባይ አጠገብ በሚገኘው የተግባረ ዕድ ቴክኒክ ትምሕርት ቤት የስብሰባ አዳራሽ ከአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ለመወያየት ጥሪ አድርጓል።

የዚህ ሕዝባዊ ስብሰባ ማረጋገጫ ደብዳቤ ከከተማው አስተዳደር ስለደረሰ ስብሰባው በታቀደው ቀንና ሰዓት መሠረት ይካሄዳል። ፓርቲው ስብሰባውን በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በትጋት በማስተዋዎቅ ላይ የሚገኝ ሲሆን በርካታ መራጮች ተገኝተው በውይይቱ እንደሚካፈሉ ይጠበቃል።

የዚህ ስብሰባ ዋና የመነጋገሪያ ትኩረት የሚሆኑት፡ ኢዴፓ ለመጪው ምርጫ እስካሁን ድረስ ያደረጋቸው ዝግጅቶች ምን እንደሆኑና ወደፊትም ምን መደረግ እንዳለበት፤ ከአባላትና ደጋፊዎች የሚጠበቀው ምን እንደሆነ እንዲሁም፤ አጠቃላይ የፖለቲካ አየሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ምን ምን ናቸው የሚሉት ናቸው። ፓርቲው በተጨማሪም ማንኛውም የወቅቱን ፖለቲካ የሚመለከቱ የሕዝብ ጥያቄዎችና አስተያየቶችን ለማስተናገድ ዝግጁ እንደሆነና ለአዲስ አበባ ፌደራላዊ መቀመጫ የሚወዳደሩ እጩዎችን በዚሁ ወቅት ከሕዝቡ ጋር እንደሚያስተዋውቅ ከፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ያገኝነው መረጃ አስታውቋል።

የአዲስ አበባው ስብሰባ ቀጥሎ ባሉት ቀናት በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በሃዋሳ፣ በአርባ ምንጭ፣ በአሰበ ተፈሪ (ጪሮ)፣ እንዲሁም በሐረርና በሌሎች ከተሞች የሚደረጉት የኢዴፓ የምርጫ ዘመቻ ስብሰባዎች አካል መሆኑን የመረጃ ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter