ኢዴፓ በአዲስ አበባ ሕዝባዊ ስብሰባ አካሄደ፤ በባህር ዳርና በጎንደር ይቀጥላል ተባለ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የሚያደርገውን ቅስቀሳ አጠናክሮ መቀጠሉንና በዚሁ መሰረትም ከሕዝብ ጋር የሚያደርገውን ስብሰባ ቅዳሜ መጋቢት 25 ቀን 2002 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ መጀመሩን ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ።

የፓርቲው ጽ/ቤት በላከልን መረጃ መሰረት፤ ቁጥራቸው እስከ አምስት መቶ የሚሆን በልደታ፣ በቀራንዮና በሳር ቤት አካባቢዎች የሚኖሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በዚሁ ስብሰባ ላይ መገኘታቸው ታውቋል። ቅዳሜ ዕለት ከጥዋቱ 3፡00 ሰዓት እስከ 7፡00 ሰዓት ድረስ በተግባረ-ዕድ ት/ቤት አዳራሽ የተደረገው ስብሰባ፣ ፓርቲው በአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች ሊያደርጋቸው በዕቅድ ከያዛቸው አራት ዋና ዋና ሕዝባዊ ስብሰባዎች ውስጥ አንዱ መሆኑም የመረጃ ምንጩ አስታውቋል።

ኢዴፓ በዚሁ ስብሰባ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎቹን ለሕዝብ ያስተዋወቀና ከተሰብሳቢዎች ለቀረቡ ልዩ ልዩ ጥያቄዎችም ምላሽ መስጠቱን ከፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ያገኘነው ተጨማሪ መረጃ አመልክቷል።

ፓርቲው በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚያደርገውን የምረጡኝ ቅስቀሳ እስከ ምርጫው ዕለት ድረስ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የዜና ምንጩ አስታውቆ፣ በዚሁ መሰረት በመጪዎቹ ቅዳሜና ዕሑድ በባህር ዳርና እና በጎንደር ከተሞች ተከታታይ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂድ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter