ኢዴፓ በላሊበላ ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ አካሄደ

ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም በሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ ኢዴፓን ወክለው በሰሜን ወሎ ዞን በቡግና ወረዳ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው የቀረቡት አቶ ልደቱ አያሌው፣ ወ/ሮ ዓለም ዘውዱ እና አቶ አስማማው ተሰማ በላሊበላ ከተማ ሕዝባዊ ስብሰባ ማካሄዳቸውን ከስፍራው የደረሰን መረጃ አመለከተ።
ማክሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2002 ዓ.ም ከቀኑ በ10፡00 ሰዓት ጀምሮ በወረዳው መስተዳድር አዳራሽ በተደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ በላሊበላ ከተማና በአካባቢዋ ነዋሪ የሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች ተካፋይ መሆናቸው ታውቋል። የስብሰባው ዓላማ፤ ሰሞኑን በአካባቢው “ልደቱ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ ሆኗል። ድርጅቱም የዚሁ እምንት አራማጅ ነው። እነዚህ ኃይሎች እምነታችሁን ለመቀየር የመጡ ኃይሎች ናቸው” ተብሎ በመናፈስ ላይ የነበረውን አሉባልታ ለመስበር እና በላሊበላ ከተማ ተለጥፎ የነበረው የሶስቱ የኢዴፓ ዕጩዎች ፖስተር እንዲቀደድ ተደርጎ ስለነበር እንዲህ ዓይነቱን ህገ ወጥ ተግባር ህዝቡ እንዴት መከላከል እንዳለበት ለመምከር መሆኑን ከስፍራው የደረሰን ዜና አስታውቋል።

ስብሰባው የተጠራው በስራ ቀንና በስራ ሰዓት ከመሆኑም በላይ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ በስብሰባው ላይ እንዳይገኝ ሰፊ የማሸማቀቅና የማስፈራራት ተግባር ቢከናወንም፣ ህዝቡ ይህንን ሁሉ ተጽእኖ ከምንም ባለመቁጠር የስብሰባ አዳራሹን ሞልቶታል። በተለይም የመንግስት ሰራተኞች ከፍተኛ ማስፈራራት ቢሰነዘርባቸውም የስራ ሰዓታቸውን እንደጨረሱ (ከ11፡30 ሰዓት በኋላ) ወደ ስብሰባ አዳራሹ በመጉረፋቸው ስብሰባው ለተወሰኑ ደቂቃዎች እንዲቋረጥ በማድረግ በአዳራሹ ውስጥ ያለውን ህዝብ አቀማመጥ በማሸጋሸግ ስብሰባው እንዲቀጥል ተደርጓል ሲል የዜና ምንጩ ገልጿል።

በስብሰባው ላይ የኢዴፓ የምርጫ ማንፌስቶ በንባብ የቀረበ ሲሆን፣ ከተሰብሳቢው ህብረተሰብ ለተነሱ ጥያቄዎችም በዕጩ ተወዳዳሪዎቹ ሰፊ ማብራሪያ ተሰጥቷል። ህዝቡ የአሉባልታ ሰለባ ሳይሆን፣ በኢዴፓ ላይ ያለውን ማንኛውንም ጥያቄ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ በማቅረብ ሀቁን እንዲረዳ ጥሪ ተደርጓል። በስብሰባው መጨረሻ፣ ህዝቡ በስብሰባው ሂደት ባገኘው መረጃ የተሰማውን እርካታ ገልጿል ሲል የዜና ምንጩ ጨምሮ አስታውቋል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter