ኢዴፓ በባህርዳርና በጐንደር ውጤታማ ስብሰባ አካሄደ

የኢትዮጵያውን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም ለሚካሄደው አገር አቀፍ ምርጫ የሚያደርገውን የምረጡኝ ቅስቀሳ አጠናክሮ በመቀጠል፤ በአማራ ክልል በባህርዳር እና በጐንደር ከተሞች እጅግ ውጤታማ የሆነ ስብሰባ ማካሄዱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ፡፡
የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሊቀመንበር የተከበሩ አቶ ደረጀ ደበበ ከስፍራው በላኩልን መረጃ መሰረት፣ ቅዳሜ ሚያዝያ 9 ቀን 2002 ዓ.ም በባህርዳር ከተማ በሙሉዓለም የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ የባህርዳርና የአካባቢው ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡ በዕለቱ በስብሰባው የተገኘው ህዝብ ከ1500 በላይ መቀመጫ ያለው የሙሉ ዓለም አዳራሽ በመሙላቱ በግቢው ውስጥ ሆኖ ስብሰባውን ሲከታተል እንደነበር አቶ ደረጀ አስታውቀዋል፡፡ “በምርጫ 97 ከነበረው የበለጠ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት ነው” ሲሉ አቶ ደረጀ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ ዕሁድ ሚያዝያ 10 ቀን 2002 ዓ.ም በጐንደር ከተማ የሲኒማ አዳራሽ ኢዴፓ በጠራው ህዝባዊ ስብሰባ፣ በጐንደር ከተማና አካባቢው ነዋሪ የሆኑ በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎች መገኘታቸውን አቶ ደረጀ ደበበ ገልፀዋል፡፡

ኢዴፓ በሁለቱ ከተሞች ባደረገው ህዝባዊ ስብሰባ የተገኘው ህዝብ በንባብ የቀረበውን የኢዴፓን ማንፌስቶ ካዳመጠ በኋላ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በማቅረብ ከኢዴፓ አመራር ምላሽ ተሰጥቶታል፡፡ በመጨረሻም ህዝቡ ለኢዴፓ ያለውን ድጋፍ ገልጾ፣ “ኢዴፓ የዛሬውም የወደፊቱም ፓርቲ ስለሆነ ብቸኛ አማራጫችን ነው” የሚል አስተያየት መስጠቱን አቶ ደረጀ ጨምረው ገልፀዋል፡፡ (የስብሰባውን ሂደት የሚያሳዩ ፎቶግራፎች እንደደረሱን እናቀርባለን)

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter