ኢዴፓ በወላይታ ሶዶ የ97ቱ የሕዝብ መንፈስ የታየበት ሕዝባዊ ስብሰባ አካሄደ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ዛሬ ሚያዝያ 16 ቀን 2002 ዓ.ም በደቡብ ክልል በወላይታ ሶዶ ከተማ ያካሄደው ሕዝባዊ ስብሰባ እጅግ ውጤታማ እንደነበር የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ሊቀ መንበር አቶ ደረጀ ደበበ ማምሻውን ከስፍራው የላኩልን ዜና አመለከተ።
ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን የመያዝ አቅም ባለው በሶዶ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አዳራሽ በተካሄደው በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከ3 ሺህ በላይ ሕዝብ መገኘቱን አቶ ደረጀ ገልጸው፣ መቀመጫ ያላገኙ የስብሰባው ተካፋዮች በአዳራሹ ዙሪያና በት/ቤቱ ግቢ ውስጥ ሆነው ሂደቱን መከታተላቸውን አብራርተዋል።

የዕለቱ ስብሰባ የተጀመረው ከቀኑ በ8፡00 ሰዓት ሲሆን፤ ስብሰባውን ለመምራት ወደ ስፍራው የሄዱት የኢዴፓ አመራር አባላት በአካባቢው የፓርቲው አባላትና ደጋፊዎች የተበረከተላቸውን የወላይታ ማህበረሰብ አልባሳት ለብሰው ገና ወደ መድረኩ ብቅ ሲሉ ለስብሰባው የታደመው ሕዝብ በፉጨት፣ በእልልታና ለረጅም ጊዜ በቆየ ጭብጨባ የተቀበላቸው መሆኑን አቶ ደረጀ ገልጸው፣ አንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች “የምርጫ 97 የሕዝብ ተሳትፎና መንፈስ ተደገመ። እውነትም ዛሬም ይቻላል” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን አስታውቀዋል።

የስብሰባውን ሂደት ለመጠበቅና ሰላምና ፀጥታን ለማስከበር የተመደቡ የፖሊስ አባላት ጭምር በስብሰባው ላይ በሚተላለፉት የኢዴፓ መልእክቶች በመመሰጥ ስሜታቸውን መቆጣጠር እንዳልቻሉ አቶ ደረጀ ጠቅሰው፤ የስብሰባውን ሂደት ለማወክ ተደራጅተው የገቡ ሰዎች የመናገር ዕድል አግኝተው ሃሳባቸውን “አገር መምራት አትችሉም፣ የማይተገበር ቃል ነው…” በማለት መናገር ሲጀምሩ፣ ሕዝቡ “ኢህአዴግን ማዳመጥ ሰልችቶናል” በሚል መንፈስ ንግግራቸውን እንዲያቆሙ በማድረጉ ስብሰባው ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መልኩ ውጤታማ ሆኖ ተጠናቋል ብለዋል። (የስብሰባውን ሂደት የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎች እንደደረሰን እናቀርባለን)

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter