ኢዴፓ አንድም ተቃዋሚ ፓርቲ ስብሰባ አድርጐበት በማያውቀው በአለታ ወንዶ ከተማ ደማቅ ስብሰባ አደረገ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ትናንት ዕሁድ ሚያዝያ 17 ቀን 2002 ዓ.ም በደቡብ ክልል ሦስት ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማካሄዱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ፡፡ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ነፃነት ደመላሽ እና የኢዴፓ የሃዋሳ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ገብሬ ቱቾ በላኩልን መረጃ መሰረት፣ ዕሁድ ከጥዋቱ 3፡30 እስከ 8፡00 ሰዓት ድረስ ሃዋሳ ከተማ ከ2000 በላይ ሰዎችን መያዝ በሚችለው የሲዳማ የባህል አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ከ3000 በላይ የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡
በዚሁ ስብሰባ ላይ የኢዴፓ ሊቀ መንበር አቶ ልደቱ አያሌውና ሌሎች የፓርቲው አመራር አባላት የተገኙ መሆናቸውን የዜና ምንጩ ጠቅሶ፣ በወቅቱ የኢዴፓ ማንፌስቶ በንባብ ቀርቦ ከስብሰባው ተካፋዮች ጋር ውይይት የተደረገበት መሆኑን አስታውቋል፡፡

በዚሁ ዕለት ከሰዓት በኋላ ከቀኑ 9፡00 ሰዓት እስከ 12፡30 ሰዓት በአለታ ወንዶ ከተማ በአለታ ሚሊኒየም አዳራሽ በተደረገው ስብሰባ ላይ ከ4500 ያላነሰ ህዝብ የተገኘ መሆኑንና የስብሰባ አዳራሹ ሞልቶ የአካባቢው ነዋሪ በአዳራሹ ግቢ ውስጥ ሆኖ ስብሰባውን ይከታተል እንደነበር የዜና ምንጩ ገልጿል፡፡

ይህንን የህዝብ ብዛት የተመለከቱ አንድ የስብሰባው ታዳሚ “በአለታ ወንዶ ከተማ እንኳን የፓርቲ መሪዎች የተገኙበት ስብሰባ ሊካሄድ በብሄር የተደራጁ ተቃዋሚዎች እንኳ ስብሰባ ጠርተውን አያውቁም፡፡ ኢዴፓ ይህንን በማድረጉ እጅግ ተደስተናል፡፡ እንግዲህ ይህንን ስብሰባ “ስም የማደስ ስብሰባ ብለነዋል” ማለታቸውን የዜና ምንጫችን አብራርቷል፡፡ ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው “በምርጫ 97 ሚያዝያ 30 ቀን በአዲስ አበባ የታየው ዓይነት የህዝብ ማዕበል አለታ ወንዶን አጥለቀለቃት” ማለታቸውንም አቶ ገብሬ ቱቾ ገልፀዋል፡፡

ከሃዋሳ ከተማ በ65 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በአለታ ወንዶ ከተማ በተደረገው ህዝባዊ ስብሰባ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌውና ሌሎች አመራር አባላት መገኘታቸው ታውቋል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ፣ ዕሁድ ዕለት ጥዋት በአርባ ምንጭ ከተማ የፖሊስ ክበብ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውጤታማ ስብሰባ መካሄዱን የኢዴፓ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደረጀ ደበበ ከስፍራው ከላኩልን መረጃ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይ በርካታ የአርባ ምንጭ ከተማ ወጣቶች መገኘታቸውን አቶ ደረጀ ገልፀው፣ የስብሰባውን ሂደት የኢዴፓ የድርጅት ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት አቶ መስፍን መንግሥቱ እንደመሩት አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ፣ ኢዴፓ በደቡብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ያደረጋቸው አራት ህዝባዊ ስብሰባዎች ውጤታማ ሆነው መጠናቀቃቸውን የዜና ምንጫችን አስታውቋል፡፡ “እነዚህ ስብሰባዎች የኢዴፓን ማንሰራራት የሚያመላክቱ ሆነው ተገኝተዋል” ሲል የዜና ምንጩ አክሎ ገልጿል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter