የኢዴፓ ሕዝባዊ ስብሰባዎች፤

  • በአዲስ አበባና በደሴ ውጤታማ ስብሰባ አካሄደ፣
  • በሐረር፣ በድሬዳዋና በላሊበላ ስብሰባ ያካሂዳል፣
  • በቀሪዎቹ ቀናት በመቀሌና በሌሎች ከተሞች ተጨማሪ ስብሰባዎች ይካሄዳሉ፣

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የምረጡኝ ቅስቀሳውን አጠናክሮ በመቀጠል፤ ዛሬ ቅዳሜ ሚያዝያ 30 ቀን 2002 ዓ.ም በሐረር ከተማ፣ እንዲሁም ነገ ዕሑድ ደግሞ በድሬዳዋና በላሊበላ ከተሞች ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂድ ከፓርቲው የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ የተላከልን መረጃ አመለከተ።
የኢዴፓ የውጭ ጉዳይ ኮሚቴ በላከልን መረጃ መሰረት፣ የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ደረጀ ደበበ፣ የማዕከላዊ ምክር ቤት አባላት የሆኑት አቶ ነፃነት ደመላሽ እና አቶ አለማየሁ ባልዳ የስብሰባውን ሂደት ለመምራት ወደ ሐረር እና ድሬዳዋ መጓዛቸው ታውቋል። አቶ ልደቱ አያሌው፣ አቶ አስማማው ተሰማ እና ወ/ሮ ዓለም ዘውዱ ደግሞ በላሊበላ ከተማ የሚካሄደውን ስብሰባ ለመምራት ወደ ስፍራው መጓዛቸውን የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል።
ይህ በዚህ እንዳለ፣ ኢዴፓ ባለፈው ሳምንት በደሴ እና በአዲስ አበባ ያካሄዳቸው ስብሰባዎች ውጤታማ ሆነው መጠናቀቃቸውን ከስፍራው ዘግይቶ የደረሰን ዜና አመልክቷል። በተለይም በደሴ ከተማ የተካሄደው ስብሰባ በተገኘው የሕዝብ ብዛትም ይሁን በተሳትፎ ደረጃ በአካባቢው በሌሎች ፓርቲዎች ከተካሄዱ ስብሰባዎች እጅግ የላቀ እንደነበር የስብሰባውን ሂደት የተከታተሉ የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል።

ኢዴፓ የደሴውን ስብሰባ ካካሄደ ወዲህ ስብሰባ የጠራው መኢአድ ሲሆን፣ በወሎ ባህል አምባ በተካሄደው በዚሁ የመኢአድ ስብሰባ ላይ ከአምስት መቶ ያልበለጠ ሰው መገኘቱንና በስብሰባውም ላይ የመኢአድ አመራር አባላት ኢዴፓን እና መድረክን ለመዝለፍ ያደረጉት ሙከራ በስብሰባው ላይ በነበሩ የሁለቱ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች የአጸፋ ምላሽ ተሰጥቷል ሲሉ በደቡብ ወሎ የኢዴፓ ተጠሪ የሆኑት አቶ አስናቀው ድረስ እና አቶ የወንድወሰን አምዴ ከስፍራው የላኩልን መረጃ አመልክቷል።

ኢዴፓ በቀሪዎቹ የቅስቀሳ ቀናት ተጨማሪ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በአዲስ አበባ፣ በመቀሌ እና በሌሎች ከተሞች እንደሚያካሂድና መለስተኛ ስብሰባዎችም እጩዎቹ ባሉባቸው ወረዳዎች እየተካሄዱ መሆኑን የዜና ምንጫችን ጨምሮ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter