በሐረርና በድሬዳዋ የተሳካ ስብሰባ ተካሄደ፤ ዘፈንና ጭፈራ የታከለበት የህዝብ ማዕበል በላሊበላ መስቀል አደባባይ ተመመ

“የላሊበላ ሕዝብ ወጥቷል ማለት ይቻላል” (የአካባቢው ነዋሪዎች)

ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ኢዴፓ በተለያዩ አካባቢዎች ባካሄዳቸው ሕዝባዊ ስብሰባዎች የተሳካ ውጤት መገኘቱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ። ቅዳሜ ዕለት በሐረር ከተማ በአሚር አብዱላሂ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ ከሶስት መቶ በላይ የሆኑ የሐረር ከተማ ነዋሪዎች መገኘታቸውን አቶ አለማየሁ ባልዳ ከስፍራው የላኩልን መረጃ አመልክቷል። በዚሁ ወቅት የኢዴፓን የምርጫ ማንፌስቶ ለመራጩ ሕዝብ ለማስተዋወቅ ተችሏል። ከተሰብሳቢው ሕዝብ ለተነሱ ጥያቄዎችም ስብሰባውን በመሩት የፓርቲው አመራር አባላት ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል ሲሉ አቶ አለማየሁ ጨምረው ገልጸዋል።
ዕሑድ እለት በድሬዳዋ ከተማ በቀድሞው የማዘጋጃ ቤት አዳራሽ በተደረገው ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ከአምስት መቶ በላይ የድሬዳዋ ነዋሪዎች መገኘታቸውን አቶ ጌትነት ገነቱ እና አቶ ለማ ወ/ማሪያም (ሁለቱም በድሬዳዋ የኢዴፓ እጩዎች ናቸው) ከድሬዳዋ በላኩልን መረጃ አመልክተዋል።

በሁለቱ ከተማዎች እስከ አሁን ድረስ ከኢዴፓ ሌላ ምንም አይነት ሕዝባዊ ስብሰባ አለመካሄዱ ታውቋል። “የአካባቢው ሕዝብ በፍርሀት ተውጧል። የፖለቲካ ስሜቱም ቀዝቅዟል። ለዚህም ማረጋገጫ የሚሆነን ኢዴፓ በጠራው ስብሰባ ላይ የተገኘው ሕዝብ ቁጥር አነስተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ በፊልም ላለመቀረጽና ፎቶ ላለመነሳት ራሳቸውን ሲያሸሹ መስተዋላቸው ነው። ይባስ ብሎ እሁድ እለት (ከኢዴፓ ስብሰባ በኋላ) መኢአድ በሐረር ከተማ በጠራው ስብሰባ ላይ ሰው ባለመገኘቱ ስብሰባው ሊካሄድ አልቻለም” ሲሉ አቶ አለማየሁ ባልዳ አስተያየታቸውን ገልጸዋል።

በተያያዘ ዜና፣ ኢዴፓ በላሊበላ ከተማ በመስቀል አደባባይ በጠራው ሕዝባዊ ስብሰባ (Rally) ላይ በርካታ ቁጥር ያለው ሕዝብ መገኘቱን ከስፍራው የተላከልን መረጃ አመለከተ። እንደ ዜና ምንጩ ዘገባ ከሆነ የላሊበላ ከተማ ሕዝብ በታሪኩ እንደዚያ ዓይነት ስብሰባ አካሂዶ አያውቅም ተብሏል።

አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች “የላሊበላ ሕዝብ እንዳለ ወጥቷል ማለት ይቻላል” የሚል አስተያየት መስጠታቸውን የዜና ምንጩ አስታውቋል። በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ የተገኘው የላሊበላና አካባቢው ሕዝብ ከመኖሪያ አካባቢው እየዘፈነና እየጨፈረ ወደ መስቀል አደባባይ ይተም እንደነበር የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል። ሂደቱን የተመለከቱ አንዳንድ በስብሰባው ላይ የተገኙ ሰዎች “በምርጫ 97 በአዲስ አበባ የታየው የሕዝብ ማዕበል በአምስት ዓመቱ በላሊበላ ተደገመ” ሲሉ መደመጣቸውንም ከስፍራው ከደረሰን ተጨማሪ አስተያየት ለመገንዘብ ተችሏል። አቶ ልደቱ አያሌው በስፍራው ለተገኘው ሕዝብ ንግግር ማድረጋቸውም ታውቋል። (የስብሰባዎቹን ሂደት የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎች እንደ ደረሱን የምናቀርብ ይሆናል)

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter