በመቀሌና በአዳማ የታሰበው ስብሰባ ሊሳካ አልቻለም

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ)  በሳምንቱ መጨረሻ በአዳማ እና በመቀሌ ሊያደርጋቸው የነበሩት ሁለት የምርጫ ዘመቻው ማጠናቀቂያ ስብስባዎች ሊሳኩ አለመቻሉን ከፓርቲው ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመለከተ፡፡
የፓርቲው ጽ/ቤት በላከልን መረጃ መሰረት በኦሮሚያ ክልል በአዳማ እና በትግራይ ክልል በመቀሌ ከተሞች ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማካሄድ ላለፉት ሁለት ሳምንታት ያህል ጥረት ሲደረግ መቆየቱ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ እስከ ዕሁድ ዕለት ድረስ የስብሰባ አዳራሾች ሁሉ ተይዘዋል በመባሉ ምክንያት ስብሰባዎቹን ለማካሄድ እንዳልተቻለ ጽ/ቤቱ አመልክቷል፡፡

በተለይ በመቀሌ ዓርብ ዕለት ስብሰባውን ለማካሄዳ የቅስቀሳ ሥራ የሚያካሂድ ቡድን ተልኮ እንደነበር የዜና ምንጩ ጠቅሶ፣ ይሁን እንጂ አለ የተባለው የከተማው ማዘጋጃ ቤት አዳራሽ ለሌላ ስብሰባ የተያዘ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አካላት በጉዳዩ ላይ ጣልቃ ገብተው ከክልሉ የመንግስት አካላት ጋር ቢነጋገሩም መፍትሄ ሊገኝ አለመቻሉን የዜና ምንጩ ጨምሮ ገልጿል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ በአዳማ ከተማ ሊካሄድ የነበረውም ህዝባዊ ስብሰባ አዳራሾች ሁሉ ቀድመው ተይዘዋል በመባሉ ምክንያት ሊሳካ አለመቻሉ ታውቋል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ለኢዴፓ አዳራሾቹ ሁሉ በሌሎች ፓርቲዎች ቀድመው ተይዘዋል ቢባልም በተባሉት ቀናት ግን ምንም ዓይነት ስብሰባ አለመካሄዱ ታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ኢዴፓ ቅዳሜና ዕሁድ በአዲስ አበባ ሶስት ሕዝባዊ ስብሰባዎችን እንደሚያካሂድ ከስፍራው የደረሰን ተጨማሪ ዜና አመልክቷል። በዚህም መሰረት ሕዝባዊ ዝብሰባዎቹ በመብራት ኃይል አዳራሽ፣ ካዛንችስ አካባቢ በሚገኘው የቀበሌ 18/18 መሰብሰቢያ አዳራሽ እና በቀድሞው መነን በአሁኑ የካቲት 12 የመሰናዶ ት/ቤት እንደሚካሄዱ የዜና ምንጩ አክሎ ገልጿል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter