ኢዴፓ በአዲስ አበባ 3 ስብሰባዎችን አካሄደ፤ በጐዳናዎች ለአራት ቀናት የማጠቃለያ ቅስቀሳ ማድረግ ጀመረ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በሳምንቱ ማጠናቀቂያ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ሦስት ህዝባዊ ስብሰባዎችን ማድረጉን ከስፍራው የተላከልን መረጃ አመለከተ፡፡ በዚሁ መሰረት፣ ቅዳሜ ዕለት ከሰዓት በኋላ በመብራት ኃይል አዳራሽና በካዛንቺስ በወረዳ 15 ቀበሌ 17/18 አዳራሽ፤ እንዲሁም ዕሁድ ዕለት በቀድሞው መነን በአሁኑ የካቲት 12 የመሰናዶ ት/ቤት ህዝባዊ ስብሰባዎችን በማድረግ የምርጫ ማንፌስቶውን ማስተዋወቁን የዜና ምንጩ ዘግቧል፡፡በመብራት ኃይል አዳራሽ የተካሄደውን ስብሰባ የፓርቲው ሊቀመንበር አቶ ልደቱ አያሌው የመሩት ሲሆን፣ ዕሁድ ዕለት በየካቲት 12 ት/ቤት የተካሄደው ስብሰባ ደግሞ በዋና ፀሐፊው በአቶ ሙሼ ሰሙ እንደተመራ ከስፍራው የደረሰን ዜና ጨምሮ ገልጿል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ፣ ኢዴፓ በአዲስ አበባ ከተማ ጐዳናዎች ለተከታታይ አራት ቀናት የመኪና ላይ ቅስቀሳ እንደሚያደርግ የፓርቲው የድርጅት ጉዳይ ምክትል ሊቀመንበር የሆኑት አቶ ነፃነት ደመላሽ አስታወቁ፡፡

አቶ ነፃነት እንደገለፁት ከሆነ ከዛሬ ሰኞ ግንቦት 9 ቀን ጀምሮ የምርጫ ቅስቀሳው እስከሚጠናቀቅበት ሀሙስ ዕለት ድረስ በአምስት ተሽከርካሪዎች የታጀበ የጐዳና ላይ ቅስቀሳ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter