ኢዴፓ የምረጡኝ ቅስቀሳውን በሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት አጠናቀቀ

የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ላለፉት ሦስት ወራት ሲያካሂደው የነበረውን የምረጡኝ ቅስቀሳ ማምሻውን በተደረገ የሻማ ማብራት ሥነ-ስርዓት ማጠናቀቁን የምርጫ ዘመቻ ማስተባበሪያ ግብረ ኃይል አባል የሆኑት አቶ ነፃነት ደመላሽ አስታወቁ።

ከሰኞ ዕለት ጀምሮ እስከ ዛሬ ሐሙስ ግንቦት 12 ቀን 2002 ዓ.ም ድረስ በመቀሌ፣ በባህር ዳር፣ በሃዋሳና በአዲስ አበባ ከተሞች በመኪና የታጀበ የምረጡኝ ቅስቀሳ መካሄዱን አቶ ነፃነት አስረድተው፣ በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በነዚህ ቀናት በተካሄደው ቅስቀሳ ወደ 400 ሺህ ገደማ በራሪ ወረቀቶችመበተናቸውን ገልጸዋል። በዚህም የቅስቀሳ ሂደት አብዛኛውን መራጭ ለማግኘት ተችሏል የሚል እምነት እንዳላቸው አስታውቀዋል።

እስከ አሁን ድረስ በኢዴፓ በኩል አስር ሚሊዮን በራሪ ወረቀቶችና ፖስተሮች ታትመው መሰራጨታቸውንና በአጠቃላይ የቅስቀሳው ሂደት ውጤታማ እንደነበር አቶ ነፃነት ገልጸው፣ “በእኛ በኩል አማራጭ ፖሊሲያችንን ለሕዝቡ አቅርበናል። በቂ ቅስቀሳም አድርገናል። ከእንግዲህ ሁሉንም መዝኖ ውሳኔ መስጠት የሕዝቡ ድርሻ ይሆናል። ያንንም የሕዝብ ውሳኔ ለመቀበል በኛ በኩል ዝግጁዎች ነን” ብለዋል።

ኢዴፓ ሲያካሂደው የነበረው የምረጡኝ ቅስቀሳ ዛሬ ማምሻውን በፓርቲው ጽ/ቤት በተደረገ የሻማ ማብራት ሥነ-ስርአት መደምደሙን ከስፍራው የተላከልን ዜና አመልክቷል።

Share this...
Share on Facebook
Facebook
Tweet about this on Twitter
Twitter